በኢትዮጵያ የፍልሰት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተካሔደ

Discussion on Ethiopia's Civil Policy Held with Stakeholders

የፍልሰተኞች ጉዳይ ከሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች እና ከፍተኛ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸው አማካሪዎች የተሳተፉበት ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ ላይ የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ ተካሄዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የፖሊሲውን አስፈላጊነት እና የረቂቅ ሰነድ ዝግጅቱን ሂደት አስመልከተው ንግግር ያደረጉት ማብራሪያ የሰጡት በፍትሕ ሚንስቴር የብሔራዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈቲያ ሰይድ ናቸው፡፡ ኃላፊዋ እንደገለጹት ሀገራችን የፍልሰተኞች መነሻና መዳረሻ ሀገር እንደመሆኗ ፍልሰትን የምትመራበት ፖሊሲ መዘጋጀቱ ፍልሰትን በአግባቡ ለመምራት የሚያስችል መሆኑን ገልጸው ዜጎች ሰብዓዊ መብታቸው ተከብሮ በህጋዊነትና በነጻነት ተንቀሳቅሰው የሚሰሩበትና የሚኖሩበት እድልንን ከመፍጠር አንጻር ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡ አሁን ላይ በፍትሕ ሚንስተር የሚመራው እና ከተለያዩ አካላት የተዋቀረው ግብረ-ሃይልም ፍልሰትን በአግባቡ ለመምራት በሚያስችሉ ሁኔታዎች ላይ ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያየት ከውይይቱ በተገኙ የተቀመሩ ሀሳቦች በመነሳት የፍልሰት ፖሊሲ አስፈላጊነት እሙን ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ፖሊሲውን ማዘጋጀት ተችሏል ብለዋል፡፡

ኃላፊዋ መልዕክታውን ቀጥለው በዚህ መድረክ ከሚደረገው ውይይት በተጨማሪ የተለያዩ ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት እንዲወያዩበት ተደርጎ በሚገኝ ግብዓት ዳብሮ እንዲጸድቅ የሚደረገው የፍልሰት ፖሊሲ በአማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንደተዘጋጀ አብራርተው በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎችም እንደ አስፈላጊነቱ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ ፈቲያ ንግግራቸውን ሲያጠቃልሉም ረቂቅ ፖሊሲ ሰነዱ አሁን የደረሰበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ አስተዋጾ ላበረከቱ የቴክኒካል ኮሚቴ አባላቶችና የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ ለቆየው ለአለማቀፉ የፍልሰተኞች ድርጅት (IOM) ያላቸውን የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በመቀጠልም በፍልሰት ፖሊሲው ረቂ ሰነድ ውስጥ የተካተቱ ቁልፍ ጉዳዮች፣ ስትራቴጂዎች እንዲሁም ዓላማና ግቦችን አስመልክቶ ለተሳታፊዎች ማብራሪያ የቀረበ ሲሆን ከስራና ክህሎት ሚንስቴር አቶ አምሳሉ በሾ ኢሜግሬሽን እና የድንበር አስተዳደር፣ የፍልሰት ተጊጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም፣ አስገዳጅ ፍልሰት፣ ትብብርና አጋርነት አስመልክቶ በፖሊሲው በተካተቱ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን የስራ ስምሪትና የስራ ፍልሰት አስተዳደር፣ የዲያስፖራ ተሳትፎና ልማት፣ ፍልሰትና መረጃ አስተዳደር፣ የተቋምና ባለድርሻ አካላት ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ አጋርነትን አስመልክቶ ደግሞ አቶ ዘሪሁን የሺጥላ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በፍትሕ ሚንስቴር የብሔራዊ ፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ዐቃቤ ሕግ የሆኑት አቶ አቤል ገ/እግዚሃብሄር በበኩላቸው ፍልሰትና የአየር ንብረት፣ ፍለሰትና ስርዓተ ጾታ፣ ፍልሰትና ጤና፣ ፍልሰትና የሰዎች ቀጠናዊ እና አህጉራዊ ነጻ እንቅስቃሴ የሚሉ ቁልፍ ጉዳዮች አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆም ሌሎችም ፖሊሲው ውስጥ የተካተቱ አበይት ጉዳዮች ለተሳታፊዎች ቀርበዋል፡፡

ተሳታፊዎችም የተሰጠውን ማብራሪያ መነሻ በማድረግ ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን በማንሳት ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን በፖሊሲው አጠቃላይ ሁኔታና ዝርዝር ጉዳዮች ላይ የተሰጡ አስተያየቶችን በግብዓትነት ጥቅም ላይ እንደሚውሉ ተገልጾ የእለቱ የውይይቱ መድረክ ተጠናቋል፡፡

Relevant Departments and People
Tagged Under: Legal Reforms Policy Development
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች

No data was found