ቀን: ታህሳስ 2017 ዓ.ም.
ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
Ministry of Industry

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈፃፀም የክትትል ሪፖርት

የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ተቋማት በሕግ በተሰጣቸው መመሪያ የማውጣት ስልጣንና የአስተዳደራዊ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በዕለት ተዕለት ተግባሮቻቸው ውሳኔ በሚያስተላልፉበት ጊዜ የዘፈቀደ አሰራር እንዳይኖር ለመከላከልና የተገልጋዮች መብት ያለአግባብ እንዳይጣስ ለመከላከል በማለም የወጣ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንደአስተዳደር ተቋም በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ የተመለከቱ የመመሪያ አወጣጥ ሂደቶችንና የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን ተግባራዊ ከማድረግ አንጻር ክትትል በማድረግ የቀረበ ሪፖርት ነው።

ለዚህ ክትትል ጥቅም ላይ የዋለው የመረጃ ምንጭ ለተቋሙ በአዋጅ 1263/2014 እና በሌሎች ሕጎች ስልጣንና ተግባራት የሚሰጡ የሕጎች ዳሰሳ፣ ከመመሪያ አወጣጥና አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የተቋሙን የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ቃለ-መጠይቅ በማድረግ እና በተቋሙ የሚሰጡ የአስተዳደራዊ ውሳኔ ናሙናዎችንና ሌሎች ተያያዥ ሰነዶች ናቸው።

ከመመሪያ አወጣጥና አመዘጋገብ ጋር በተያያዘ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አዋጁ ከወጣ በኋላ አዲስ ያወጣ መመሪያ በይኖርም በቀድሞ አጠራር የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር በነበረው አወቃቀር አሁን በመሻሻል ላይ ያሉ ሁለት መመሪያዎችን ጨምሮ 39 የሚደርሱ መመሪያዎችን በፍትህ ሚኒስቴር ማስመዝገቡ በአዎንታዊነት የሚወሰድ ነው። ይሁን እንጂ ለመስሪያ ቤቱ ስልጣን ሰጪ ሕጎች ሲቀየሩ ተከታትሎ በተገቢው ጊዜ መመሪያን ከማውጣትና ማሻሻል አንጻር፣ የረቂቅ መመሪያዎች አወጣጥ የተደረጀ መዝገብ አለመኖር፣ የረቂቅ መመሪያዎቹን ቢያንስ በሁለት ቅጂዎች አለመዘጋጀት፣ የመመሪያዎችን ማብራሪያ አለማዘጋጀት የመሳሰሉ ክፍተቶች ታይተዋል።

ከአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥና ቅሬታ አፈታት ጋር በተያያዘ የአስተዳደር ውሳኔ ይሰጠኝ አቤቱታ በጽሁፍ እንዲቀርብ ከማድረግ አንጻር በአንዳንድ ክፍሎች የተዘጋጁ ቅጾች መኖራቸው፣ የሚቀርብ አቤቱታ በመ/ቤት ገቢ ስለመደረጉ የሚመዘገብና ስለመቀበሉ በቀሪው ላይ የሚፈረም መሆኑ፣ ተገልጋዮች የሚያቀርቡት የሰነድ ማስረጃ የሚታይ መሆኑ እና የአስተዳደር ውሳኔ በጽሁፍ ለተገልጋዩ የሚሰጥ አንጻር ያለው አሰራር የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ መርሆዎች ጋር የሚጣጣም ሆኖ በመገኘቱ በጥንካሬ የሚወሰድ ነው። ይሁን እንጂ ከውሳኔው ይዘት አንጻር ውሳኔው ያረፈበትን የሕግ ድንጋጌ አለመጥቀስ እና የቀረበውን ማስረጃ በውሳኔው ውስጥ ከማስፈርና ከመተንተን አንጻር፣ በተቋሙ የተቋቋመ የቅሬታ ማስተናገጃ አካል አለመኖር እና በተቋሙ ግልጽ እና ወጥ የሆነ የቅሬታ አቀራረብ ሥነ-ሥርዓት ይፋ አለማድረግ ክፍተት የታየባቸው ናቸው። በዚሁ መነሻ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የበላይ አመራር ለአዋጁ አፈጻጸም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ክትትል እንዲያደርግ፣ የሕግ አገልግሎት ክፍል የመመሪያ አወጣጥ ሂደቶችንና የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎችን ሁሉም የስራ ክፍሎች አካተው ተግባራዊ እንዲያደርጉ እንዲያስተባብርና ክትትል እንዲያደርግ፣ አዋጁ በሚያዘው መሰረት ወጥ የሆነ የቅሬታ ሰሚ ወይም ማስተናገጃ አካል ማቋቋም እና የቅሬታ አቀራረብ ስርዓት ይፋ ማድረግ እንደሚገባ ምክረ-ሀሳብ ተሰጥቷል።

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች