ቀን: ጥር 2014 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን
Ethiopian Revenue and Customs Authority

የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈፃፀም ክትትል ሪፖርት በጉምሩክ ኮሚሽን

በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 (ከዚህ በኋላ በጽሁፉ ውስጥ አዋጁ እየተባለ የተገለጸው) መጋቢት 29 ቀን 2012 ዓ/ም የወጣ መሆኑ ይታወቃል። የፍትህ ሚኒስቴር (በቀድሞ ስያሜው ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) ከዩኤስኤይድ ፍትህ አክቲቪቲ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ ለፌዴራል መንግስቱ አስተዳደር ተቋማት የበላይ አመራሮች በስልጠና መልክ አዋጁን የማስተዋወቅ ተግባር ያከናወነ መሆኑ ይታወሳል።

ለአዋጁ መውጣት መሰረታዊ የሆኑ ምክንያቶችና ዓላማዎች በመግቢያው ላይ እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፦

  • በሕገ መንግስቱ ላይ የተቀመጠውን መንግስታዊ አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት የተደነገገውን ለማስፈጸም ይረዳ ዘንድ፤
  • ማናቸውም የመንግስት ባለስልጣን ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ እንደሚሆን በሕገ መንግስቱ የተደነገገውን ለማስፈጸም ይረዳ ዘንድ፤
  • የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብትና ጥቅም ላይ የሚያስከትለውን ጣልቃ ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ለማረጋገጥ፤
  • የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ መርሆዎችና ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የተሰኘ ሰው በፍርድ ቤት የሚያስመረምርበት ስርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትህ ማስፈን የሚሉት ናቸው።

የፍትሕ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ከተሰጠው ስልጣን መካከል በአዋጁ አንቀጽ 6(6) ላይ በፌዴራል መንግስቱ የሚወጡ ሕጎች ወጥነት ባለው መልኩ ተግባራዊ መደረጋቸውንና አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶችም ስራቸውን በሕግ መሰረት መስራታቸውን የመቆጣጠርና የማረጋገጥ ኃላፊነት ተሰጥቶታል። በዚህ መሰረት በተመረጡ ተቋማትና ሕጎች ላይ የተለያዩ የአፈጻጸም ጥናቶችን በመስራት ሪፖርት ሲያቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ይህ ስራ ከዚሁ የቀጠለ የተቋሙ የ2014 በጀት ዓመት መደበኛ ስራ አካል ነው።

በዚህ የሕግ አፈጻጸም ክትትል በጉምሩክ ኮሚሽን የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈጻጸም በተለይም ከአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ እና ቅሬታ አቀራረብ ስርዓት እና ሕጋዊነት ጋር በተያያዘ ዳሰሳ ተደርጓል።

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች