ቀን: ሰኔ 2015 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
Ethiopian Investment Commission

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈፃፀም ሪፖርት

ይህ የክትትል ሪፖርት በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን (ከዚህ በኋላ ተቋሙ እያልን የምንጠራው) የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈጻጸም መመሪያዎች ከማውጣትና ከማስመዝገብ፣ አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥና ቅሬታ ከማስተናገድ የተቀመጡትን ሂደቶችና መርሆዎችን ከማክበር ያለውን አፈጻጸም ለመገምገም በተዘጋጀ ቼክ-ሊስት መሰረት እንደሚከተለው ተመልክተናል፡፡

የመረጃ አሰባሰብ ዘዴን በተመለከተ የመጀመሪያ ደረጃ ምንጭ በመጠቀም የሕግ ዳሰሳ፣ ቃለ-መጠይቅና ምልከታ በማድረግ፤ በሁለተኛ ደረጃ የመረጃ ምንጭነት ከክትትሉ ጋር ቀጥተኛና ተዘዋዋሪ ጠቀሜታ/ግንኙነት ያላቸው ሰነዶችን በማሰባሰብ ይህ የክትትል ሪፖርት የተዘጋጀ ነው፡፡ በክትትሉ የሚሳተፉ ባለሙያዎችና ኃላፊዎችን ለቃለ-መጠይቅ የመረጥነው ዓላማ መር (purposive sampling) ዘዴን የተከተልን ሲሆን የአስተዳደራዊ ውሳኔ እና ቅሬታ አፈታት ሂደትን ለመገምገም የዘፈቀደ ናሙና አወሳሰድ ዘዴ (Random sampling) ተከትለናል፡፡

መመሪያ አወጣጥ ሂደት አፈጻጸምን ስንመለከት የተዘጋጀው ረቂቅ መመሪያ በሁለቱ ቋንቋ የተዘጋጀ መሆኑን፣ ረቂቅ መመሪያው በፍትህ ሚኒስቴር ከመጸደቁ በፊት ከነማብራሪያው ጋር በማያያዝ እንዲመዘገብ መደረጉ እና ነባር መመሪያዎች እንዲመዘገቡ መደረጉ፣ ነባር እና አዲስ መመሪያ በተቋሙ ድረ-ገጽ እንዲጫኑ በማድረግ ተደራሽ እንዲሆኑ በመደረጉ በጥንካሬ የሚወሰዱ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል መመሪያ ሲወጣ ሕግ አውጪው አካል በሚሰጠው የውክልና ሥልጣን መሰረት በአስተዳደር ተቋም የሚወጣ በሰዎች መብት ወይም ጥቅም ላይ ውጤት የሚያስከትል የሕግ ሰነድ ሲሆን በስራ ላይ ያለ መመሪያን የሚያሻሽል ወይም የሚሽር የሕግ ሰነድንም እንደሚጨምር በአዋጁ አንቀጽ 2/2/ ላይ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ ተቋሙ መመሪያ የማውጣት ሥልጣን በአዋጅና በደንብ ሥልጣን የተሰጠው ሲሆን አስገዳጅ በሆነ እና አስገዳጅ ባልሆነ ሁኔታ የተደነገጉ ሆነው መውጣት የሚገባቸው መመሪያ የወጡ እንዳሉና ገና ያልወጡ እንዳሉም ተመልክተናል፡፡ ከአዋጁ መውጣት በኋላ አንድ መመሪያ አዘጋጅተው በስራ ላይ ያዋሉ ሲሆን ይህ መመሪያ ሲወጣ መዝገብ ያልተደራጀ መሆኑን፣ ማስታወቂያ የማውጣት አሰራር ያልተተገበረ መሆኑ፣ የውይይት መድረክ ለማንኛውም ሰው አሳታፊ በሆነ መንገድ ያልተዘጋጀ መሆኑ፣ አስተያየቶችን ስለመቀበል አስመልክቶ ከባለድርሻ አካላት እና ከተገልጋዮች የተሰጡ አስተያየቶች በግብአትነት ስለመወሰዳቸው፣ የትኞቹን ደግሞ ተቀባይነት እንዳላገኙ የሚያሳይ የሰነድ መረጃ ወይም ቃለ-ጉባኤ የሌለ መሆኑን፣ ለፍትህ ሚኒስቴር ረቂቅ መመሪያው ከመጸደቁ በፊት ሲላክ የተሰጡ አስተያየቶችና የተወሰዱ እርምት እርምጃዎችን አጠቃሎ የያዘ የመመሪያው ማብራሪያ ያላካተተ መሆኑ በድክመት የታዩ ናቸው፡፡

ከአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ አኳያ በርካታ ጥያቄዎች በጽሑፍ እና በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በመጠቀም የሚቀርቡ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ አብዛኛው ጥያቄዎች ከሰነድ ጋር የተያያዙና በጽሑፍ ምላሽ የሚሰጥባቸው ናቸው ፤ ውሳኔውም በጽሑፍ ለተገልጋዩ እንዲደርሰው የሚደረግ መሆኑን፣ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት አግባብነት ያላቸውን የሰነድ ማስረጃዎች በተገልጋዮች እንዲያቀርቡ የሚደረግበት አግባብ እንዳለና የውሳኔ ይዘት ገላጭ በሆነ መንገድ የሚሰጥ መሆኑን ከተሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ለመረዳት ችለናል፡፡ እነዚህ በጥንካሬ የሚገለጹ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ተገልጋዮች የአስተዳደር ጥያቄ በጽሑፍ ሲያቀርቡ ለቀረቡት ጥያቄ ስለማቅረባቸው የጽሑፍ ማረጋገጫ የማይሰጣቸው መሆኑን በክፍተት የታየ ነው፡፡

በሌላ በኩል ቅሬታን በይግባኝ ከማየት አንፃር የተመለከትን ሲሆን በተቋሙ የአቤቱታና የቅሬታ ማስተናገጃ ቡድን በሚል በስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና ዳይሬክቶሬት ስር የተቋቋመ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ ይህም በጥሩ ጅምሮ የሚወሰድ ቢሆንም በአዋጁ በሚጠበቀው መልኩ ራሱን የቻለ ቅሬታ ማስተናገጃ አካል ያልተቋቋመ መሆኑን አይተናል፡፡ ለቅሬታ ማቅረቢያ የሚሆን ፎርም በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተዘጋጀ መኖሩን ተመልክተናል፡፡ ይህም የሚበረታታ ልምድ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ እንዲሁም በተቋሙ ህንጻ የተለዩ ቦታዎች ላይ ወዴት መሄድ ይፈልጋሉ የሚል አቅጣጫ ጠቋሚ (outlook billboard) ተዘጋጅቶ እያንዳንዱ የስራ ክፍል የት እንደሚገኝ የሚያሳይ ሲሆን በዚሁ ላይ የቅሬታ ማስተናገጃ ክፍል ተገልጾ ይገኛል፡፡ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በየደረጃው ባለ ኃላፊዎች የሚታይበት የህግ እና የአሰራር ስርዓት መኖሩ ተመልክተናል፡፡ እንዲሁም በተቋሙ የበላይ ኃላፊ የተሰጠ ውሳኔ የመጨረሻ ሲሆን በተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ተገልጋይ ለቦርድ ማቅረብ እንደሚችል፤ በቦርድ የተሰጠ ውሳኔ ለተቋሙ የመጨረሻ ውሳኔ መሆኑን ተመልክተናል፡፡ በተጨማሪ ለቅሬታ አቅራቢው በተቋሙ የበላይ አመራር ወይም በቦርድ የተሰጠ ውሳኔ በጽሑፍ የሚሰጥ መሆኑን፡፡

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች