ቀን: ታህሳስ 2015 ዓ.ም.
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ
Addis Ababa City Administration Bureau of Finance

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈፃፀም ክትትል ሪፖርት

በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1996 መሠረት የተቋቋመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በቻርተሩ አንቀጽ 13 (1) (ሀ) በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የተሻሻለውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 74/2014 አውጥቶ ሥራ ላይ እንዲውል አድርጓል፡፡ በዚሁ አዋጅ ከተቋቋሙት አስፈጻሚ አካላት አንዱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ ሲሆን ሥልጣንና ተግባሩም በአዋጁ በአንቀጽ 18 ላይ ተዘርዝሯል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ የፌዴራል አስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012ን የአስተዳደር ተቋማት እንዴት እየተገበሩት እንደሆነ በክትትል ለማረጋገጥ ከተመረጡት አንዱ ሆኖ በመገኘቱ በተቋሙ ላይ ይህ ክትትል ሊካሄድ ችሏል፡፡

በዚሁ መሠረት በፋይናንስ ቢሮው፣ ወካይ ሆነው ለናሙና በተመረጡ ሁለት ክፍለ ከተሞችና በአምስት ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤቶች በአካል በመገኘት ለክትትሉ ግብአት ሊሰጡ የሚችሉ የሚመለከታቸውን ሠራተኞችና ኃላፊዎች ቃለ መጠይቅ ተደርጓል፣ የሰነድ ማስረጃዎች ተሰብስበዋል፣ ምልከታም ተካሂዷል፡፡

በክትትሉ የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ከፌዴራል አስተዳደር ሥነሥርዓት አዋጁ ጋር ተገናዝበው ሲታዩ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ በተሰጠው የውክልና ሥልጣን መሠረት ለሥራው አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎችን አውጥቶ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረጉን ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ነባር መመሪያዎችን ለፍትሕ ሚኒስትር ልኮ ማስመዝገብ ሲገባው አለማስመዝገቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ ባሻገር በቢሮው፣ በክፍለ ከተሞችና በወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤቶች፤ ተገልጋዮች መብቴ ወይም ጥቅሜ ተነክቷል ብለው በሚያቀርቡት አስተዳደራዊ ውሳኔ ይሰጥልኝ አቤቱታ ላይ በተገቢው ጊዜ አስተዳደራዊ ውሳኔ በመስጠትና በተሰጠ አስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ተገልጋዮች የሚያቀርቡትን ቅሬታ ተቀብሎ በማስተናገድ ረገድ ለናሙናነት የተሰበሰቡ ውሳኔዎች ከአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ ጋር የተጣጣሙ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

በአጠቃላይ በዚህ የክትትል ሪፖርት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፣ በሁለት ክፍለ ከተሞችና በአምስት ወረዳዎች በመዘዋወር የተሰበሰቡ ማስረጃዎች ከፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ ጋር በማገናዘብ በዝርዝር ለማየት ተሞክሯል፡፡ በመጨረሻም የታዩ ጥንካሬዎች እንዲቀጥሉ የታዩ ክፍተቶች ደግሞ እንዲታረሙ ምክረ ሀሳብ ቀርቦበታል፡፡

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች