መንግስት ለሕዝብ አገልግሎት ለሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች መሬትን መጠቀም አስፈላጊ ስለሆነ፤
የአገሪቱ ከተሞች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደጉና የነዋሪዎቹም ቁጥር እየጨመረ በመሄዱ በከተሞች ፕላን መሠረት ለመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ ለመሠረተ ልማት፣ ለኢንቨስትመንትና ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውል የከተማ መሬትን መልሶ ማልማት አስፈላጊ በመሆኑ፣እንዲሁም በገጠር ለሚከናወኑ የልማት ሥራዎች መሬት አዘጋጅቶ ማቅረብ በማስፈለጉ፤
የመሬት ይዞታ እንዲለቅ ለተደረገ ባለይዞታ ተገቢና ተመጣጣኝ ካሣና የተነሽ ድጋፍ ለመክፈል ግምት ውስጥ መግባት የሚገባቸውን መሠረታዊ መርሆዎችን ለይቶ መወሰን በማስፈለጉ፤
ካሣውን የመተመን፣ የመክፈል እና ተነሺዎችን መልሶ የማቋቋም ሥልጣንና ኃላፊነት ያለባቸውን አካላት በግልጽ ለይቶ ለመወሰን በማስፈለጉ፤
በነባሩ ሕግ ያጋጠሙ የሕግ ክፍተቶችን ሌሎች የመሬት ይዞታ ለማስተካከልና የሚለቀቅበትን እና ካሣ የሚከፈልበት ሥርዓቱን ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ ድንጋጌዎችን ማካተት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
ከይዞታ መነሳትና ካሳ ክፍያ ጋር ተያይዞ ስለሚኖር የቅሬታ አቀራረብና ውሳኔ አሰጣጥ ስርዓት በግልጽ መወሰን አስፈላጊ በመሆኑ፤
የፌደራል መንግሥት የመሬት አጠቃቀም ሕግ የማውጣት ሥልጣን እንዳለው በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 51(5) በመደንገጉ፣ ለህዝብ ጥቅም ሲባል የሚለቀቅ ንብረትን በሚመለከት ተመጣጣኝ ካሣ በቅድሚያ እንዲከፈል በአንቀጽ (8) በመደንገጉ እንዲሁም ተነሺዎች በመንግስት ዕርዳታ እንዲቋቋሙ በአንቀጽ 44(2) የተቀመጠውን መሠረተ ሀሳብ በዝርዝር መደንገግ በማስፈለጉ፤
በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 55 (2)(ሀ) መሠረት የሚከተለው ታውጇል።
•
•