የሚወጡ ሕጎች ተግባራዊ የሚሆኑት በሰዎች ላይ በመሆኑ ከመውጣታቸው በፊት ተገቢውን የሕግ አረቃቀቅ ዘዴዎችን እና ሂደቶችን ተከትለው የተዘጋጁ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ከሚያስችሉ ሥርዓቶች አንዱ በመሆኑ እና ለዚህም የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የሕጎችን ጥራት በማረጋገጥ የወጡበትን ዓላማ በአግባቡ ማሳካት እንዲችሉ እና አፈፃፀማቸውም ውጤታማ እንዲሆን ለምርመራ ለፍትሕ ሚኒስቴር የሚላኩ ረቂቅ ሕጎችን ወጥነት ባለው እና ጥራቱን በጠበቀ መልኩ ለመመርመር የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ፤
የኢፌዲሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በመንግሥት ተቋማት የሚዘጋጁ ረቂቅ ሕጎች የሕግ ማርቀቅ መርሆዎችን የተከተሉ እና ከሕገ-መንግሥቱ፣ ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች፣ ከሌሎች በሥራ ላይ ካሉ ሕጎች፣ ከሕግ ሥርዓቱ እና ሌሎች መሰል መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ መሆኑን ለማረጋገጥ የሚያስችል ረቂቅ ሕጎች ስለሚቀርቡበት እና ስለሚመረመሩበት አግባብ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤
የፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 21(2) መሠረት ይህን መመሪያ አውጥቷል፡፡