መድኃኒት ከሰው ልጅ ጤናና ደኅንነት ጋር በቀጥታ የተገናኘ በተፈጥሮውም የመርዛማነት ባሕርይ ያለውና ከጥሬ ዕቃ ዝግጅት ጀምሮ በምርት ማጓጓዝ፤ በክምችት፤ አያያዝ እና እደላ ሃደት አስፈላጊውን ጥንቃቄ ካልተደረገለት የጥራት ደረጃዉን፤ ፈዋሽነቱንና ደህንነቱን ሊያጣ ወይም ሊለወጥ ስለሚችል ከአካል ጉዳት እስከ ሕይወት ማጣት ችግር የሚያስከትል በመሆኑ ደረጃውን በጠበቀና አግባብነት ባለዉ ባለሙያ ኃላፊነት ስራውን እንዲከናወን በማድረግ የህብረተሰቡን ጤና መጠበቅ አስፈላጊ በመሆኑ፤
የህብረተሰቡን ጤና ደህንነቱ፣ ፈዋሽነቱና ጥራቱ ካልተረጋገጠ እና ምንጩ ከማይታወቅ መድኃኒት በመጠበቅ ሊደርስ ከሚችለውን የጤና ችግር መከላከል አስፈላጊ በመሆኑ፤
በመድኃኒት ችርቻሮ ንግድ ስራ ላይ የሚሰማሩ ድርጅቶች ከሚሰጡት አገልግሎት፣ መስሪያ ቦታ፣ የሰው ኃይልና አስፈላጊ ግብአቶች እንዲሁም እያያዝ፤ እጓጓዝ፤ ክምችትና ዕደላ አንፃር ማሟላት ያለባቸውን መስፈርቶች በማሟላት የጥራት ደረጃው፣ ፈዋሽነቱንና ደህንነቱ የተረጋገጠ መድኃኒት እንዲያቀርቡ ማድረግና አግባባዊ የመድኃኒት አጠቃቀም ማስፈን በማስፈለጉ፤
ሕብረተሰቡን ደረጃውን በጠበቀ የመድኃኒት ችርቻሮ ንግድ ድርጅት፡ በሙያው በሰለጥነና ሙያዊ ስነ-ምግባር በተላበሰ የመድኃኒት ባለሙያ አማካኝነት ተገቢውን የመድኃኒት አገልግሎት ማግኘት ያለበት በመሆኑ፣
ህጋዊ የሆኑ የመድኃኒት አገልግሎት የሚሰጡ የችርቻሮ ድርጅቶችን ለመጠበቅና ከሕግ ውጪ በመሥራት የህበረተሰብ ጤና ሊጎዱ የሚችሉትን አካላት በመከላከል ጥራት ያለው የመድኃኒት አገልግሎት ተደራሽነት ማረጋገጥ በማስፈለጉ፤
በመሆኑም የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን መድኃኒት ጥራት፣ ደኅንነትና ፈዋሽነት በማረጋገጥ ረገድ የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት በአዋጅ ቁጥር 661/2002 አንቀጽ 55(3) መሠረት ይህን ሞዴል መመሪያ አውጥቷል፡፡