የግድያ ወንጀል የሚያስከትለው ተጠያቂነት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የወንጀል ድርጊት የማህበረሰቡን ሰላም እና ደኅንነት ከማወኩም በላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስን ያስከትላል። ወንጀል በተለያየ ምክንያት ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት ሊፈፀም ይችላል። በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ መሠረት የወንጀል ተግባር ናቸው ተብለው ከተቀመጡት መካከል አንዱ የግድያ ወንጀል ነው። የግድያ ወንጀል ወንጀሉ የተፈፀመበትን ሰው ህይወት የሚቀጥፍ የወንጀል ተግባር ሲሆን በዚህ ጽሁፍ የመግደል ወንጀልን ምንነት እና የሚያስከትለውን ተጠያቂነት እንመለከታለን።

በህይወት የመኖር መብት

የሰው ልጅ ሰው በመሆኑ ብቻ ሰብዓዊ መብቱ ሊከበርለት ይገባል። ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች የሰው ልጅ ሰብዓዊ መብቱ ሊከበርለትና በምንም መንገድ ሊገረሰስ እንደማይገባ አስፍረዋል። ከእነዚህ እውቅና ከተሰጣቸው ሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ በህይወት የመኖር መብት ሲሆን ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መግለጫ (UDHR) በአንቀጽ 3 ስር እንዲሁም ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR) በአንቀጽ 6 ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር እንዳለው የደነገጉ ሲሆን በተለይም ዓለም ዓቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (ICCPR) የሞት ቅጣትን ቀሪ ባላደረጉ ሀገራት ቅጣቱ ሊወሰን የሚገባው ሕግን ተከትሎ ለከባድ ወንጀሎች ብቻ መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

ሀገራችን ኢትዮጵያም ከላይ ተጠቀሱትን ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች በመፈረም አፅድቃ የህጓ አካል አድርጋዋለች። ይህን መሠረት በማድረግም በ1987 ዓ.ም በወጣው ህገ-መንግሥት ላይ በህይወት የመኖር መብት እንዲካተት ተደርጓል። በመሆኑም በኢ.ፌ.ድ.ሪ ህገ-መንግሥት አንቀጽ 15 መሠረት ማንም ሰው በህይወት የመኖር መብት እንዳለው የተቀመጠ ሲሆን በሕግ በተደነገገ ከባድ የወንጀል ቅጣት ካልሆነ በስተቀር ማንኛውም ሰው ህይወቱን ሊያጣ እንደማይችል በዚሁ አንቀጽ ስር ተቀምጦ ይገኛል።

ከዚህ መረዳት የሚቻለው አንድ ሰው በህይወት የመኖር መብቱን ሊያጣ የሚችለው በሕግ በተደነገገው መሠረት በፍርድ ቤት ውሳኔ ብቻ እንደሆነ ነው። በመሆኑም ማንም ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት በማናቸውም አይነት መሳሪያ ወይም ዘዴ ሰውን የገደለ እንደሆነ ነፍሰ ገዳይ እንደሚሆን በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 538 ላይ ተደንግጎ ይገኛል።

የግድያ ወንጀል አፈፃፀም ሁኔታዎች

በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ሕግ መሠረት ግድያ ከአፈፃፀም ሁኔታው አንፃር ከባድ የሰው ግድያ፣ ተራ የሆነ የሰው ግድያ፣ ቀላል የሆነ የሰው ግድያ እና በቸልተኝነት ሰውን መግደል በሚል ተለይቶ የተቀመጠ ሲሆን የወንጀል ህጉን መሠረት በማድረግ እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታቸዋለን።

ከባድ የሰው ግድያ

በወንጀል ህጉ አንቀጽ 539 በተደነገገው መሠረት አንድ ሰው ከባድ የሰው ግድያ ወንጀል ፈፅሟል ለማለት በአንቀጹ ላይ ከተቀመጡት ፍሬ ነገሮች መካከል ቢያንስ አንዱ መሟላት ይኖርበታል። በዚህም ማንም ሰው ግድያውን የተፈፀመው ፡-

ሰውን ለመግደል አስቀድሞ በነበረው አሳብ ወይም ምክንያት፣

ለመግደል የተጠቀመበት መሳሪያ ወይም ዘዴ፣ ያገዳደሉ ሁኔታ ወይም ግድያው የተፈፀመበት ቅጣትን የሚያከብድ ጠቅላላ ወይም ልዩ ምክንያት ሲታይ ገዳዩ በተለየ ጨካኝ፣ ነውረኛ ወይም አደገኛ መሆኑን በሚገልጽ ሁኔታ ሲሆን ወይም

  • ሰውን ለመግደል ወይም የውንብድና ወንጀልን ለመፈፀም የተደራጀ የወንበዴ ቡድን አባል በመሆን ሲሆን ወይም
  • ሌላ ወንጀል ለመፈፀም እንዲመቸው ወይም የተፈፀመ ወንጀል እንዳይገለፅ ለማድረግ ሲል ከሆነ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል በመፈፀም ተጠያቂ እንደሚሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 539(1) ስር ተደንግጎ ይገኛል። በመሆኑም ከላይ በተገለፀው ሁኔታ ከባድ የሰው መግደል ወንጀል የፈፀመ ሰው በእድሜ ልክ ጽኑ እስራት ወይም በሞት ይቀጣል። በተጨማሪም አንድ ወንጀለኛ የእድሜልክ ጽኑ እስራት ተፈርዶበት ቅጣቱን በመፈፀም ላይ ሳለ ከላይ በተገለፀው ሁኔታ ወንጀሉን የፈፀመ እንደሆነ በሞት እንደሚቀጣ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 539(2) ስር ተደንግጎ ይገኛል።

ተራ የሰው ግድያ

በወንጀል ህጉ አንቀጽ 540 ላይ እንደተቀመጠው ተራ የሆነ የሰው ግድያ ተፈጽሟል የሚባለው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 539 በተመለከተው አግባብ ከባድ ባልሆነ ወይም በወንጅል ህጉ አንቀጽ 541 ላይ በተመለከተው አግባብ ቀላል ባልሆነ ሁኔታ አስቦ ሰውን የገደለ እንደሆነ ነው። እዚህ ላይ በደንብ ልንገነዘብ የሚገባን ሰውን መግደል በምንም አይነት መመዘኛ ትክክል ባይሆንም ተራ የሰው ግድያ የተባለው ግድያ የተፈፀመበትን ሁኔታና መሳሪያ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ ነው። ስለሆነም ተራ የሰው ግድያ በአብዛኛው በድንገት በሚፈጠር አለመግባባት መሀል ሊከሰት የሚችል ድርጊት እንደሆነ መረዳት ይቻላል።

ቅጣትን በተመለከተ ተራ የሆነ የሰው ግድያ የፈፀመ ማንም ሰው ከአምስት ዓመት እስከ ሀያ ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል በዚሁ አንቀጽ ላይ ተደንግጎ ይገኛል።

ቀላል የሆነ የሰው ግድያ

አንድ የተፈፀመን የግድያ ወንጀል ቀላል የሆነ የሰው መግደል ወንጀል ነው የሚባለው ወንጀል ፈፃሚው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 75 ላይ የተቀመጠውን የአስገዳጅ ሁኔታ (እራሱን ወይም ሌላ ሰውን በቅርብ ከሚደርስ አደጋ ለመጠበቅ ሊወስድ የሚገባውን እርምጃ) ወሰንን በመተላለፍ ወይም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 78 ላይ የተቀመጠውን ህጋዊ መከላከል (የተቃጣበትን ጥቃት ወይም የገጠመውን ለህይወት አስጊ ሁኔታ ለማስወገድ የሚወስደውን እርምጃ) ከመጠን በማሳለፍ ወይም ከፍ ባለ ደም በሚያፈላ ምክንያት ወይም ባልተጠበቀ ሕሊናን በሚያውክ ድንገተኛ ምክንያት ወይም በከፍተኛ ስሜት ወይም በብርቱ ዝንባሌ የተነሳ በአእምሮ ግምት ይህንን ለማድረግ በሚያደርሱና በከፊል ይቅርታን በሚያሰጡ ሁኔታዎች አስቦ ሌላ ሰውን የገደለ እንደሆነ ነው። በመሆኑም ከላይ በተቀመጠው ሁኔታ ቀላል የሆነ የሰው ግድያ ወንጀል ፈፅሞ የተገኘ ማንኛውም ሰው ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 541 ስር በግልጽ ተደንግጎ ይገኛል።

በቸልተኝነት ሰውን መግደል

ከስሙ መረዳት እንደሚቻለው በቸልተኝነት ሰው መግደልን ፈፃሚው አስቦ የሚያደርገው ሳይሆን ማድረግ ያለበትን ጥነቃቄ ባለማድረግ በሚፈፅመው ቸልተኝነት የሚፈፀም ነው፡፡ በዚህ መልኩ ግድያ ተፈፅሞ ሲገኝ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 543(1) መሠረት ፈፃሚው ከስድስት ወር እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት ወይም ከብር ሁለት ሺ እስከ አራት ሺ በሚደርስ መቀጮ ሊቀጣ ይችላል፡፡

በተጨማሪም በቸልተኝነት ግድያ የፈፀመው የሌላ ሰውን ህይወት፣ ጤንነት ወይም ደኅንነት የመጠበቅ የሞያ ወይም ሌላ ግዴታ ያለበት እንደ ህክምና ባለሙያ ወይም አሽከርካሪ ያለ ሰው እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 543(2) መሠረት ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ሊደርስ የሚችል ቀላል እስራት እና ከብር ሶስት ሺ እስከ ብር ስድስት ሺ ሊደርስ የሚችል የገንዘብ መቀጮ ይሆናል፡፡

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሶስት ላይ እንደተቀመጠው በቸልተኝነት ሰው መግድል ወንጀል የፈፀመው ሰው ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን ከገደለ ወይም ወንጀሉን የፈፀመው ግልጽ የሆነ ደንብ ወይም መመሪያን ተላልፎ እንደሆነ ወይም የሚያሰክሩ ወይም የሚያፈዙ ንጥረ ነገሮችን ወይም መጠጦችን በመውሰድ እራሱን ከኃላፊነት ነፃ በሚያወጣ ሁኔታ ውስጥ አድርጎ ቢሆንም እንኳን በወንጀል ተጠያቂ የሚሆን ሲሆን ቅጣቱም ከአምስት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እና ከብር አስር ሺ እሰከ ብር አስራ አምስት ሺ የሚደርስ መቀጮ ይሆናል።

ልላ ሰው ራሱን እንዲገድል ማነሳሳትና መርዳት

በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ ሰውን መግደል የተከለከለ እና የገደለም በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆነ የደነገገ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ማንም ሰው ሌላውን ሰው እራሱን እንዲገድል ያነሳሳ ወይም የረዳ እንደሆነ በወንጀል እንደሚጠየቅ ደንግጓል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ራስን የመግደል ሙከራው በተደረገ ጊዜ በቀላል እስራት እንዲሁም እራስን የመግደል ተግባሩ በተፈፀመ ጊዜ ደግሞ ከአምስት ዓመት የማይበልጥ ጽኑ እስራት ቅጣት በአነሳሹ ወይም በረጂው ላይ ሊወሰንበት እንደሚችል በወንጀል ህጉ አንቀጽ 542(1) ላይ ተደንግጎ ይገኛል።

በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ቁጥር ሁለት ላይ በተቀመጠው መሠረት ደግሞ እራሱን እንዲገድል የተነሳሳው ወይም እርዳታ የተደረገለት ለአካለመጠን ያላደረሰ ልጅ ማለትም 18 ዓመት ያልሞላው ልጅ ወይም በአእምሮ ህመም ወይም በእድሜ መግፋት የተነሳ ችሎታ ያልነበረው ሰው ሲሆን በአነሳሹ ወይም በረጂው ላይ የሚጣለው ቅጣት የሚከብድ ይሆናል። በዚህ መሠረትም የተነሳሳው ወይም የተረዳው ሰው ራሱን ለመግደል የፈፀመው ተግባር በሙከራ ደረጃ ቀርቶ ከሆነ ከአምስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እንዲሁም ራሱን ገድሎ ከሆነ ደግሞ ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ይሆናል።

ህጻንን መግደል

ሌላው በወንጀል ህጉ ላይ የተቀመጠው ህጻንን መግደል የተመለከተ ሲሆን አንዲት እናት ለመውለድ ምጥ በተያዘች ጊዜ ወይም የምጥ ስሜቷ ሳያልፍ አስባ ልጇን የገደለች እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ትቀጣለች። ወንጀሉ ሲሞከር በህጻኑ ላይ ምንም አይነት ጉዳት ያልደረሰ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 180 መሠረት ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን በመሰለው አቅሎ ውሳኔ ሊሰጥ እንደሚችል በወንጀል ህጉ አንቀጽ 544(1) ስር ተደንግጎ ይገኛል። በዚህ በተገለፀው ሁኔታ አንዲት እናት በምጥ ወቅት ወይም ደግሞ የምጥ ስሜቷ ሳያልፍ አስባ ልጇን እንድተገድል በዋና ወንጀል አድራጊነት፣ በአነሳሽነት ወይም በአባሪነት ተካፋይ የሆነ ሌላ ሰው እንደነገሩ ሁኔታና እንደጥፋቱ መጠን ሰው ስለመግደል በተመለከቱት መደበኛ ህጎች መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆን በወንጀል ህጉ አንቀጽ 544(3) ላይ በግልጽ ተቀምጦ ይገኛል።

ሌላው በወንጀል ህጉ አንቀጽ 544(2) ላይ እንደተደነገገው ከላይ በንዑስ አንቀጽ አንድ ከተመለከተው ውጪ አንዲት እናት አስባ ወይም በቸልተኝነት ልጇን የገደለች እንደሆነ ግድያን የሚመለከቱ መደበኛ የህጉ ድንጋጌዎች ተፈፃሚ የሚሆኑ ይሆናል፡፡

ማጠቃለያ

በአጠቃላይ ሰውን ያለፍርድ መግደል በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች እና በህገ-መንግስቱ የተረጋገጠውን በህይወት የመኖር መብት መጣስ እና ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት ማጥፋት ከመሆኑ በላይ በፈፃሚው ላይ የወንጀል ተጠያቂነት የሚያስከትል በመሆኑ ይህን ወንጀል ከመፈፀም መቆጠብ ይገባል።

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ