በመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስና የሚያስከትለው የወንጀል ተጠያቂነት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

መሠረተ ልማት የሚለው አገላለፅ ለአንድ ማኅበረሰብ የተረጋጋ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ በርካታ የአገልግሎት መስጫ ጉዳዮችን የሚያጠቃልል የልማት አውታር ነው። መሰረተ-ልማቶች ግዙፍነት ያላቸው ወሳኝ ግንባታዎች ሆነው ለምሳሌ እንደ መንገድ፣ ቴሌኮም፣ የኃይል መስመሮች የመሳሰሉትን ሊያካትት የሚችል ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የማይዳሰሱ እንደ የትምህርት ስርዓት፣ የኢኮኖሚና የአስተዳደር ስርዓቶችን የሚመለከት ሊሆኑ ይችላሉ።

መሰረተ-ልማቶች በአንድ አገር ውስጥ ዘላቂነት ያለው እድገት፣ ፍትሃዊ ሃብት አጠቃቀምና አስተማማኝ ሰላም የሰፈነበት ማኅበረሰብ ለመፍጠር ከሚኖራቸው ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ የተነሳ በዋነኛነት የመንግሥትን ልዩ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው። ይሁንና የአገራትን አስተዳደራዊ ሁኔታ መሠረት በማድረግ በእኛም አገር አልፎ-አልፎ እንደሚስተዋለው መሰረተ-ልማቶች በግሉ ዘርፍም ሊለሙ ይችላሉ።

በአገራችን በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእነዚህ የሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ መሰረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ ጉዳት፣ ዘረፋና ውድመት እየተባባሰ ስለመምጣቱ በተለያዩ ተቋማት እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ። ለዚህ እንደምሳሌም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ንብረቶች በሆኑ በተለያዩ የኃይል ማስተላለፊያዎች (Transformers) እና ምሰሶዎች ላይ በሚፈፀም ስርቆት የተነሳ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የኃይል መቋረጥ ሲገጥም በተደጋጋሚ የምንመለከተው ጉዳይ ነው። ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በቀን 03/10/17 ባካሄደው የአጋር አካላት የውድድር መድረክ ላይ በ2017 ዓ.ም 10 ወራት ብቻ ወደ 200 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ (199.5 ሚሊዮን) ሃብት በዘረፋ ስለማጣቱ በሪፖርት አመላክቷል።

የእነዚህ መሰረተ-ልማቶች መጎዳት ደግሞ የሚያስከትለው አገራዊ ጫና ቀላል አይሆንም። በመሆኑም እነዚህ የሀገር ወሳኝ መሠረተ ልማቶች የሚጠበቅባቸውን የአገልግሎት ዘመን ያህል ጥራት ያለው አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ጠንካራ የሕግ ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። የዚህ አጭር የንቃተ-ሕግ ዓላማም በመሰረተ-ልማት ጥበቃ ዙሪያ ያሉ የሕግ ማዕቀፎችን እንዲሁም በእነዚህ ሃብቶች ላይ ጉዳት ማድረስ የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነት በማሳየት ማህበረሰቡ ከጉዳት እንዲከላከላቸው ማስገንዘብ ነው።

የመሰረተ-ልማት ምንነት

መሰረተ ልማት በውስጡ በርካታ ዘርፎችን አቅፎ የሚይዝ ከመሆኑ የተነሳ አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም መስጠት አስቸጋሪ ነው። እያንዳንዱ የመሰረተ-ልማት አውታር እንደሚሰጠው የአገልግሎት ዓይነት፣ እንደተቋቋመበት ዓላማና የአገልግሎቱ ተጠቃሚ አይነት በርካታ ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ ትርጉማቸውም ይህንኑ ሁኔታ ያገናዘበ ነው፣ እንደምሳሌ ለንግዱ ማኅበረሰብ የሃብት ምንጭ (Capital goods) ተደርገው ሊወሰዱ ሲችሉ ለጠቅላላው ማኅበረሰብ ደግሞ የህልውናው መሠረት (Self-realizing goods) ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም ጠቅለል ያለ ትርጉም ከመስጠት ይልቅ በተናጠል ሊሳካ ከታለመው ዓላማ ጋር ግንኙነት ያለው ትርጉም መስጠት በብዙ ተቋማት የተለመደ አሠራር ነው።

በዚህ መሠረት የአገራችንን ሕግ ስንመለከት አሁን ላይ በአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 31(2) ሥልጣንና ተግባሩ ወደ ከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የተላለፈው የፌደራል የተቀናጀ መሰረተ ልማት ማስተባበሪያ ኤጀንሲ በተቋቋመበት አዋጅ ቁጥር 857/2006 አንቀጽ 2(1) ስር “መሰረተ ልማት ማለት ከመሬት በላይ ወይም ከመሬት በታች ያለ መንገድ፣ የባቡር ሀዲድ፣ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ የኤሌክተሪክ ኃይል፣ መስኖ፣ የውሀ መስመር ወይም የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ሲሆን ሌሎች ተያያዥ ግንባታዎችንም ይጨምራል” የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ ሕግ አተረጓጎም መሠረት “…ሌሎች ግንባታዎችንም ይጨምራል” የሚለው አገላለፅ የሚያሳየን በትርጉሙ ላይ የተካተቱት ብቻ ሳይሆኑ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ለሕዝብ መገልገያነት የተሰሩ ስራዎችም በመሰረተ ልማትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆናቸውን ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ትርጓሜ በራሱ በቀድሞው አዋጅ ቁጥር 857/2006 ወይም በአስፈፃሚ አካላት ሥልጣን መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 አንቀጽ 31 ላይ ለከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር ከተሰጠው ሥልጣን አንፃር የተሰጠ ትርጓሜ በመሆኑ ምክንያት የተሟላ አይሆንም። ከዚህ ባለፈ ሌሎች የመሰረተ-ልማት አገልግሎት ሰጭ ተቋማትም እንደየተቋቋሙበት የስራ ኃላፊነት የሚስማማ ትርጓሜ የሚያስቀምጡ መሆናቸው የሚታወቅ ነው።

የመሠረተ ልማት አይነቶች

ከፍ ብሎ እንደተመላከተው “መሰረተ ልማት” በርካታ ቁልፍ ነገሮችን አካቶ የሚይዝ ሰፊ አገራዊ መገለጫ ያለው ነገር ነው። ከዚህ በተጨማሪ ሀገራትም ለህዝባቸው የሚሰሯቸው መሰረተ ልማት ብለው የሚጠሯቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ የሚታወቅ ነው። እነዚህ መሰረተ-ልማቶች በዋናነት ከአገልግሎት ዘርፍ፣ መዋቅራዊ አሠራርና ቁጥጥር አንፃር በሚከተለው ሁኔታ ለይቶ ማስቀመጥ ይቻላል።

  • የኃይል መሰረተ ልማቶች– እንደሚታወቀው በዚህ ባለንበት ዘመን ከኃይል ውጪ ሊከወኑ የሚችሉ ተግባራት በእጅጉ እየቀነሱ ይገኛል። ከዚህ አንፃር የኃይል መሰረተ-ልማቶች እጅግ አስፈላጊ ከሆኑት ውስጥ ዋነኞቹ ሲሆኑ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፣ የኃይል ማመንጫዎች ፣ተሸካሚ ምሶሶዎች ፣ማከፋፈያዎች ፣ትራንስፎርመሮች ኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመሮች፣ ማከማቻዎች ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ የተለያዩ ከሰሎችን ማምረቻዎች፣ ማከማቻ፣ ማጓጓዣዎች፣ ፍል-ዉሃና የስቲም ምርቶችን ያጠቃልላል።
  • የትራንስፖርት መሠረተ ልማቶች፣- በመንገድ መሰረተ ልማት ዉስጥ በርካታ ነገሮች ተካተዉ ይገኛሉ፣ በዚህም መንገዶችና ተያያዥነት ያላቸዉ መዋቅሮች ለምሳሌ ድልድዮች ፣ የዉሃ መዉረጃ ቦዮች፣ የመንገድ ምልክቶች፣የኤሌክትሪክ ሲስተሞች የጎዳና መብራቶች፣ የመንገድ መብራቶች፣ የመንገድ ጥገና ተቋማት፣ የባቡር መንገዶች የተለያዩ ለባቡር ትራንስፖርት የሚጠቅሙ ግንባታዎች፣ የባህር ትራንስፖርት አየር መንገድና የኤርፖርቶች ድርጅት ይገኙበታል።
  • የግንኙነት መሠረተ-ልማቶች (Communication Infrastructures) – በእነዚህ ስር ደግሞ የፖስታ አገልግሎት፣ የቴሌፎን አገልግሎት፣ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት፣ የቴሌቪዥንና ሬዲዮ አገልግሎት፣ ማስተላለፊያዎች፣ የፋይበር ኬብሎች፣ ምሶሶዎች፣ የብሮድካስትንግ ቁጥጥር ስርዓት፣ የኔትዎርክ (ዳታ) ማዕከላት፣ የመገናኛ ሳተላይቶች የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ናቸዉ፡፡
  • የውሃና ፍሳሽ መሠረተ-ልማቶች – የመጠጥ ዉሃ አቅርቦት መስጫ ግድቦች (Reservoirs)፡-ማስተላለፊያ መስመሮች ፣የውሃ ማከማቻዎች ፣ማጣሪያ ጣቢያዎች፣ ማከሚያ ቁሳቁሶች፣ ፍሳሽ ማስወገጃዎች፣ የውሃ ማስተላለፊያ ቦዮች፣ የተለያዩ የመስኖ ግንባታዎች፣ ጎርፍ መቆጣጠሪያዎች ወዘተ በውሃ መሠረተ-ልማቶች ስር ይመደባሉ።

ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ተቋማትና አጥኝዎች ግዙፍነት የሌላቸው (Soft Infrastructures) ብለው የሚከፍሏቸው ለምሳሌ የትምህርት ስርዓት፣ የኢኮኖሚና የጤና ስርዓት፣ አጠቃላይ የአገልግሎት ዘርፉ፣ የመዝናኛና ስፖርት መሰረተ-ልማቶች፣ የባህልና ቱሪዝም መሰረተ-ልማቶችና የመሳሰሉትን ሁሉ የሚይዝ ሰፊ ዘርፍ መሆኑ ግንዛቤ ያሻዋል።

በመሠረተ-ልማቶች ላይ ጉዳት ማድረስና የወንጀል ተጠያቂነቱ

በሀገራችን በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት ላይ የሚገኘውን መሰረተ ልማት ጥበቃ የመስጠቱ ጉዳይ ከሚካሄደው ፈጣን ግንባታ ጋር በእኩል ደረጃ ሊታሰብ የሚገባው እንደሆነ ከፍ ብሎ የተመለከትነው ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በእነዚህ ወሳኝ ሀብቶች ላይ ጉዳት ማድረስ የሚያስከትለውን የወንጀል ተጠያቂነት ቀጥለን የምናይ ይሆናል።

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ወንጀል ሕግ

በወንጀል ሕጉ በክፍል ስድስት “ለሕዝብ ጥቅም በተቋቋሙ ግዙፍ ስራዎችና አገልግሎቶች ላይ ጉዳት ማድረስ” በሚል ርዕስ ስር በአንቀጽ 505 ላይ የሚከተለውን ሰፍሮ እናገኛለን። ማንም ሰው

  • ሀ. ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ወይም ስራ ላይ የዋሉ የየብስ፣ የውሃ፣ የባህር፣ ወይም የአየር ማመላለሻዎች ወይም መገናኛዎች እንዲሁም እነዚህን ለማደስ፣ ለመጠገን፣ እንደገና ለመሥራት ወይም አገልግሎት ላይ ለማዋል የሚጠቅሙ የግንባታ ስራዎችን ጭምር አስቦ መደበኛ አሠራር መከልከል፣ ማወክ ወይም ማሰናከል በቀላል እስራትና በመቀጮ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜም ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡
  • ለ. ለፖስታ፣ ለቴሌግራፍ፣ ለስልክ ግንኙነት ወይም ለቴሌኮሙኒኬሽን በጠቅላላው ወይም የውሃ፣ የመብራት፣ የጋዝ፣ የኃይል ወይም የሙቀት አገልግሎት ለሕዝብ ለማቅረብ የተቋቋሙ ተቋማትን መደበኛ አሠራር መከልከል፣ ማወክ ወይም ማሰናከል በ”ሀ” ስር ከሰፈረው ተመሳሳይ ቅጣት የሚያስቀጣ ነው፡፡ በዚሁ ድንጋጌ ንዑስ 2 ላይ ድርጊቱ የተፈፀመው የውል ግንኙነት ባለው ሰው በሆነ ጊዜና አገልግሎቱም የተቋረጠው ከአቅም በላይ ባልሆነ ወይም በሕግ ከተፈቀደው ሁኔታ ውጪ ሆኖ ሲገኝ ቅጣቱ ከ3 ወር የማያንስ ቀላል እስራትና መቀጮ ወይም ነገሩ ከባድ በሆነ ጊዜ ከ7 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ደንግጓል።

አንቀጽ 506፣

ማንኛውም ሰው በመንገድ፣ በባቡር ሀዲድ፣ በውሃ ወይም በአየር ላይ የሚደረግ የሕዝብ ወይም የዕቃ ማጓጓዝ አገልግሎትን ለግጭት፣ ከሀዲድ ለማስወጣት፣ ለማስጠም ወይም ለማንኛውም ሌላ አደጋ ለማጋለጥ አስቦ ድልድይን፣ ግድብን፣ የማዕበል ማገጃን፣ የተቋቋመ ግዙፍ ስራን ወይም የመቆጣጠሪያ ምልክት ማሳያና የመሳሰሉትን ያበላሸ፣ ከቦታው ያዛወረ፣ ያፈረሰ ወይም እንዳያገለግል ያደረገ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይቀጣል፡፡

ይህ ድርጊት የሰውን ሕይወት፣ አካል ወይም ጤንነት አደጋ ላይ ከጣለ ወይም በንብረት ላይ እጅግ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ከሆነ ወይም ድርጊቱን የፈፀመው ፈፃሚው የሙያ ወይም የውል ግዴታውን በመጣስ ከሆነ ቅጣቱ ከብዶ እስከ 10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ይሆናል፡፡ እንዲሁም ድርጊቱ ለበረራ ወይም ለባህር ላይ ጉዞ ደኅንነት የሚያገለግሉ ተቋማት ወይም መሳሪያዎች ላይ ጉዳት በማድረስ በበረራ ላይ ያለ አውሮፕላንን ወይም በጉዞ ላይ ያለ መርከብን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ቅጣቱ ከ15 እስከ 25 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚሆን ከወንጀል ህጉ አንቀጽ 506(5) መረዳት ይቻላል፡፡

የእነዚህ ድንጋጌዎች የቅጣት ማክበጃ ደግሞ አንቀጽ 512 ላይ የተመለከተ ሲሆን ከላይ የሰፈሩት ድርጊቶች ሲፈፀሙ የሰው ሕይወት፣ አካል ወይም ጤንነት ላይ ጉዳት ከደረሰ ቅጣቱ ከ10 እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት ብሎም ነገሩ ከባድ ከሆነ በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ሊያስቀጣ ይችላል፡፡ እንዲሁም እነዚህ ወንጀሎች ሆን ተብሎም ሆነ በቸልተኝነት ቢፈፀሙ የቅጣት መጠናቸው ይለያይ እንጅ የሚስጠይቁ ስለመሆናቸው በድንጋጌው ተካቷል፡፡

በሌላ በኩል ማንም ሰው በሰዎች ወይም በንብረት ላይ አደጋ ለማድረስ አስቦ ኤሌክትሪክን ወይም ውሃን የሚመለከቱ ህንፃዎችን፣ የተፈጥሮ ኃይልን ለመከላከል የተሰሩ ስራዎችን፣ በተለይም ቧንቧዎችን፣ ቦዮችን፣ ማጠራቀሚያዎችን፣ የውሃ ማገጃዎችን፣ መልቀቂያዎችን ወይም ማዕበል ማገጃዎችን ያበላሸ ወይም ያፈረሰ እንደሆነ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ የመሰረተ ልማት ላይ ጉዳት ከማድረስና ከማውደም በመለስ እንደስርቆት ዓይነት ወንጀሎችም ሲፈፀሙ በወንጀል ሕጉ በከባድ ሁኔታ ታይቶ በአንቀጽ 669(1) (ለ) ቅጣት ተቀምጦለታል፡፡

እንዲሁም የማይገባውን ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ ለቴሌኮሚኒኬሽን፣ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ለውሃና ፍሳሽ ወይም ለማንኛውም ሌላ ድርጅት አገልግሎት የሚውል ጠባቂ የሌለውን መሳሪያ ወይም ዕቃ የሰረቀ ሰው ከ1 ዓመት የማያንስ ቀላል እስራት ወይም ከ15 ዓመት የማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ እንደሚቀጣ(የተደገመ) በወንጀል ሕግ አንቀጽ 496 እና 494 ላይ ተደንግጓል፡፡

ሌሎች አዋጆች

የባቡር ትራንስፖርት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር

ከመደበኛው የወንጀል ሕግ በተጨማሪ ልዩ ልዩ የቅጣት አይነቶችን የያዙ ህጎች የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የባቡር ትራንስፖርት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1048/2009 አንዱ ነው። በዚህ መሠረት በሕግ የተደነገጉትን የጥንቃቄ ደንቦች በመተላለፍ በተለይም በባቡር መሠረት ልማቶች አቅራቢያ የሚከናወኑ የግንባታ፣ የቁፋሮ ወይም ተመሳሳይ ሥራዎችን፣ ወይም የባቡር መሰረተ-ልማቶችን ከላይ ወይም ከስር አቋርጠው ወይም በትይዩ የሚከናወኑ መሰረተ-ልማቶችን በተመለከተ የወጡ ሕጎችን በመተላለፍ በባቡር ትራንስፖርት ላይ የደኅንነት ስጋት እንዲፈጠር ያደረገ ሰው ከ5 ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት እና ከብር 100,000 በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ በአዋጁ አንቀጽ 41 በግልፅ ሰፍሯል፡፡

በተያያዘ የተፈፀመው የወንጀል ድርጊት የባቡር አደጋ እንዲደርስ በማድረግ ሞትን ወይም ከባድ የአካል ጉዳትን አስከትሎ እንደሆነ ወይም ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የንብረት ጉዳትን አስከትሎ እንደሆነ የእስራት ቅጣቱ እስከ 20 ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚሆን ድንጋጌው ያመለክታል፡፡

የቴሌኮምና የኤሌክትሪክ አውታሮችን ደኅንነት ለመጠበቅ የወጣ አዋጅ

የቴሌኮምንኬሽንና የኤሌክትሪክ አውታሮችን ከሚኖራቸው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ፣ ለማስፋፋት ከሚጠይቁት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አኳያ እንዲሁም በመላ ሀገሪቱ ተሰራጭተው የሚገኙና ለጥቃት የተጋለጡ በመሆናቸው ልዩ ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።

በመሆኑም ለእነዚህ መሰረተ-ልማቶች የተለየ ጥበቃ ለመስጠት በማሰብ የፈደራልና የክልል መንግስታት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዲኖርባቸዉ ያደረገው አዋጅ ቁጥር 464/1997 ሌላኛው አግባብነት ያለው ሕግ ነው፡፡ በዚህ አዋጅ ውስጥ የሀገር ደኅንነትን ወይም ኢኮኖሚን በሚጎዳ ሁኔታ በቴሌኮምንኬሽን ወይም በኤሌክትሪክ አውታር ላይ የስርቆት ተግባር የፈጸመ ወይም ሆነ ብሎ ጉዳት ያደረሰ ወይም አገልግሎቱ እንዲቋረጥ ያደረገ ማንኛዉም ሰው አግባብ ባለዉ የወንጀል ሕግ የበለጠ የሚቀጣ ካልሆነ በቀር ከ5 ዓመት እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት የሚቀጣ ሲሆን ድርጊቱ የተፈፀመው በቸልተኝነት ከሆነ ከ6 ወር እስከ 5 ዓመት በሚደርስ እስራት እንደሚቀጣ በአንቀጽ 4 ላይ ተደንግጓል፡፡

ማጠቃለያ

ከፍ ሲል እንደተመላከተው የመሰረተ-ልማቶች የአንድ ማኅበረሰብ ህልውና መሰረቶች ናቸው። እንዚህ ወሳኝነት ያላቸው ሀብቶች በትኩረት ተጠብቀው ለማህበረሰቡ የታለመላቸውን ግልጋሎት ይሰጡ ዘንድ በዋናነት ከሚያስፈልጉት ጉዳዮች አንዱ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ መኖር ነው። በዚህ ጽሑፍ እንደተመለከትነው የመሰረተ-ልማቶችን ጥበቃ የሚመለከቱ ህጎች በተበታተነ ሁኔታ የሚገኙ ናቸው። እነዚህ ዝርዝር ህጎች በየድንጋጌዎቻቸው ስር በግልፅ አስፍረው እንደሚገኙት የቅጣት ተፈፃሚነታቸው በወንጀል ህጉ ከተቀመጠው የበለጠ ከሆነ ብቻ ነው።

በመሆኑም በዚህ ጽሑፍ ያልተካተቱ መሰል ህጎች ያሉ መሆናቸውን መረዳት ያስፈልጋል። በአጠቃላይ የመሰረተ-ልማት አውታሮችን በቂ ህጋዊ ከለላ ከመስጠትና የፍትሕ አካላት ከሚኖራቸው ሚና ባሻገር ያሉትን የሕግ ማዕቀፎችና የሚያስከትሉትን ተጠያቂነት በማህበረሰቡ ዘንድ በተገቢው ማስረፅ ያስፈልጋል። በዚህም ማህበረሰቡ ራሱ ዘብ ሆኖ ከጉዳትና ከዘረፋ ሊጠብቃቸው ይገባል።

በመጨረሻም በተለያየ ምክንያት ከዚህ በላይ በተገለፁት ህጎችና ድንጋጌዎች ስር ሊካተቱ የማይችሉ ጥሰቶች ቢኖሩ እንደምሳሌ “በሕዝቡ ጠባቂነት በመተማመን ያለጠባቂ የሚኖር ሕንፃ፣ ሐውልት፣ ታሪካዊ የሆነ ስፍራ፣ ወይም ለሕዝብ አገልግሎት፣ ለአገር ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ የተተከለ የመሳሪያ ተቋም፣ የተዘረጋ የቴሌ ወይም የመብራት ኃይል መስመር ወይም እርሻ ያወደመ ወይም ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሰው ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ወይም ነገሩ ከባድ በሚሆን ጊዜ ከ10 እስከ 20 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በወንጀል ህጉ 690(2) ስር የተደነገገ ስለሆነ አጥፊው ከህጋዊ ተጠያቂነት ሊያመልጥ የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡