የፀረ-አበረታች እጾች የሕግ ስርዓት በኢትዮጵያ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበትን አትሌቲክስ ጨምሮ በበርካታ አይነት ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎች በስፋት ከሚስተዋሉባቸው የክስ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ከጸረ-አበረታች ቅመሞች ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው። በዚህ ምክንያትም ኢትዮጵያዊያን አትሌቶችን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርተኞች ለተወሰነ ጊዜ ከውድድር ማራቅ እስከ የእድሜ ዘመን እገዳ የሚደርስ ቅጣት ሲተላለፍባቸው እናስተውላለን።

የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ይህንን በስፋት የሚስተዋል የስፖርታዊ ማጭበርበር ችግር ለመቆጣጠር በማሰብ በመጀመሪያ እ.ኤ.አ. በ2003 ዓለም ዓቀፍ ጸረ-ዶፒንግ ኮድ (world anti-doping Code as last amended in 2021) በመቀጠልም በ2005 ዓለም ዓቀፍ የስፖርታዊ ጸረ-ዶፒንግ ስምምነት (International Convention against Doping in Sport) የተሰኙ ወሳኝ ሰነዶችን አውጥቷል። ኢትዮጵያም የእነዚህ ስምምነቶች ፈራሚ አገር ስትሆን በስምምነቱ መሠረት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ጽ/ቤት የተሰኘ ተቋም በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 ተቋቁሟል። በዚህ አጭር የንቃተ-ሕግ ጽሑፍ ስለ አበረታች ቅመሞች ምንነት፣ ክልከላ ስለተደረገባቸው መድሃኒቶች፣ ሊወሰዱ ስለሚችሉ እርምጃዎችና የወንጀል ተጠያቂነት የሚዳሰስ ይሆናል።

የዶፒንግ ምንነት

የአለም አቀፉ የጸረ-አበረታች ስምምነት (World anti-doping code) በአንቀጽ 1 ላይ የሚከተለውን ትርጓሜ አስፍሯል፣ “Doping is defined as the occurrence of one or more of the anti-doping rule violations set forth in Article 2.1 through Article 2.10 of the Code.” ይህም ማለት በቀላሉ “አንድ ስፖርተኛ አበረታች እፅ ተጠቀመ የሚባለው በስምምነቱ አንቀጽ 2(1-10) የሰፈሩትን ክልከላዎች ተላልፎ የተገኘ እንደሆነ ነው፣ የሚል ሲሆን ድንጋጌው በስር በርካታ ክልከላዎችን አስፍሯል።

በሌላ በኩል በኦሎምፒክ ውድድሮች የጸረ-አበረታች እፆችን የሚመለከተው ኮድ (Olympic Movements Anti-Doping Code (OMADC) የደም ውስጥ አበረታች፣ ሆን ተብለው የሚወሰዱ ዶፒንጎች፣ ሸፋኝ ንጥረ-መነገሮች (Masking Agents) ፣ወዘተ እያለ ለእያንዳንዳቸው ቃላት ትርጉም ካስቀመጠ በኋላ ስለዶፒንግ ዘርዘር ያለ ትርጉም እንደሚከተለው አስፍሯል። በዚህም Doping is:

  1. The use of an expedient (substance or method) which is potentially harmful to athletes’ health and/or capable of enhancing their performance, or
  2. The presence in the athlete’s body of a Prohibited Substance or evidence of the use thereof or evidence of the use of a Prohibited Method በማለት የተረጎመው ሲሆን ወደ አማርኛ ሲመለስም “ዶፒንግ ማለት አትሌቶችን ሊጎዳ ወይንም አቅማቸውን ባልተገባ ሁኔታ በማሳደግ ሊጠቅም የሚችል የተከለከለ ንጥረ-ነገር ወይም ዘዴ መጠቀም ወይም አንዳች የተከለከለ ንጥረ-ነገር ወይም ዘዴ በአትሌቱ ሰውነት ውስጥ መገኘቱ በማስረጃ ሲረጋገጥ ነው የሚል ይሆናል። በዚህ ትርጓሜ መሠረትም የተከለከለን ንጥረ-ነገር መጠቀም ብቻ ሳይሆን በሰውነቱ ውስጥ ጸረ-አበረታች ነገሩ ባይገኝ ነገር ግን በአንድ በሆነ ጊዜ ተጠቅሞ የነበረ መሆኑ በማስረጃ ቢረጋገጥ የዶፒንግ ጥሰትን ሊያስከትል የሚችል ስለመሆኑ ከላይ ከተመለከትነው ትርጉም ሰፋ ባለ መልኩ ተገልጿል።

ይሁን እንጅ ይህ ስምምነት ተፈፃሚነቱ በኦሎምፒክ ጨዋታዎች ብቻ የተወሰነ ነው።

በተያያዘም የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጸረ-አበረታች ባለሥልጣን ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 400/2009 አንቀጽ 2(2) ስር ዶፒንግ የሚለውን ቃል አቻ የአማርኛ ትርጉም ሳይሰጥ በቀጥታ የተረጎመው ሲሆን በዚህ መሠረት “ዶፒንግ ማለት አንድ ወይም ከአንድ በላይ የሆኑ በዓለም ዓቀፍ የጸረ-ዶፒንግ ኮድ አንቀጽ 2 ስር የተዘረዘሩ የጸረ-ዶፒንግ ሕግ መጣስ ክስተት ነው ሲል ከአለም አቀፉ ጸረ-ዶፒንግ ኮድ ጋር ተመሳሳይ ትርጓሜ አስቀምጧል። በአጠቃላይ ከእነዚህ ትረጓሜዎች መረዳት እንደሚቻለው “ዶፒንግ’ ማለት ከጸረ-አበረታች ጋር የተያያዘን የሕግ ክልከላ የመጣስ ተግባር እንደሆነ ነው።

የህጉ ዓላማ

የአለም አቀፉ የጸረ-አበረታች ስምምነት (World anti-doping code) በመግቢያው ላይ የስምምነቱን ዓላማ በግልፅ ያመላከተ ሲሆን በዚህም የስምምነቱና ይህንኑ መሠረት አድርገው የሚቀረፁ ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች የሚከተሉትን ዓላማዎች መሠረት የሚያደረጉ ናቸው።

  • አትሌቶች ከየትኛውም አበረታች መድሃኒት ነፃ ሆነው በትክክለኛ ተፈጥሯዊ ቁመናቸው የመወዳደር መብታቸውን መጠበቅ፣ በዚህም እኩልነትን መሠረት ያደረገ፣ ጤናማ እና ፍትሃዊ ዓለም ዓቀፍ ውድድር እንዲኖር ማስቻል፣
  • በየአገራቱም ይሁን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚተገበሩ የጸረ-አበረታች ቁጥጥር ስራዎች የተቀናጁና እርስ በእርስ የተጣጣሙ ሆነው እንዲተገበሩ የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን መቅረፅ፣ በዚህም የመከላከል፣ ልየታ(ምርመራ)እና የማረም ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ማስቻል የሚል ነው።

በተያያዘ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጸረ-አበረታች ቅመሞች ፅ/ቤት ሁሉም ስፖርታዊ ውድድሮች ከአበረታች ቅመሞች የጸዱና እና ነፃ ውድድርን መሠረት ያደረጉ እንዲሆን የመቆጣጠር ሥልጣን ተሰጥቶት የተቋቋመ ስለመሆኑ ከፍ ሲል ከተገለፀው የማቋቋሚያ ደንብ ላይ መመልከት ይቻላል።

ክልከላ የተደረገባቸው አበረታች ንጥረ-ነገሮች

የአለም አቀፉ የጸረ-አበረታች ኤጀንሲ (WADA) ቢያንስ በየዓመቱ የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮችን ዝርዝር እንዲያወጣ በስምምነቱ አንቀጽ 4.1 ላይ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የዚህን ዓመት (2025 እ.ኤ.አ) ዝርዝር ስንመለከት የሚከተሉትን እናገኛለን፣

  • የሰውነትን የሆርሞን ምርት የሚያሳድጉ ከ30 በላይ ሳይንሳዊ ይዘትና ስያሜ ያላቸው ንጥረ-ነገሮች
  • የፕሮቲንና አሚኖ አሲድ (Amino Acid) ይዘት ያላቸው እንክብሎች
  • የትኛውንም የሰውነት ህዋስ እድገት የሚያፋጥኑ (ህዋስ አነቃቂ እንደ ኢንሱሊንና ፕላትሌት ያሉ ንጥረ-ነገሮች)
  • የአተነፋፈስ ስርዓትን የሚያዳብሩ ተጨማሪ ንጥረ ነገሮች (Beta-2 Agonists)- በእዚህ ክፍል ስር ከ15 በላይ አይነት ንጥረ-ነገሮች በዝርዝሩ ተካተዋል።
  • ከምግብ ስርዓት ጋር ግንነነት ያላቸውና በተዘዋዋሪ ለሰውነት ተጨማሪ ኃይል የሚያስገኙ ንጥረ-ነገሮች
  • ሸፋኝ ንጥረ-ነገሮች(Masking Agents) ፣- የእነዚህ መድሃኒቶች ተግባር በዋናነት አትሌቱ/ስፖርተኛው የተጠቀመውን አበረታች እፅ በምርመራ እንዳይታወቅ (Neutralize) የሚያደረጉ ሲሆን እነዚህም በክልከላ ዝርዝሩ ክፍል S5 በግልፅ ተመላክተዋል።

በአጠቃላይ በዚህ ጽሑፍ ለማሳየት የተሞከረው የንጥረ-ነገሮቹን ዋና ዋና ምድብ (Genre) ሲሆን ሙሉውን የንጥረ-ነገሮች ዝርዝር የአለም አቀፉ የጸረ-አበረታች ኤጀንሲ በጃኑዋሪ 1/2025 (World Anti-Doping Code International Standard Prohibited List 2025) በሚል ካወጣው የተከለከሉ አበረታች እፆች ዝርዝር መመልከት ይቻላል።

የሚያስቀጡ የሕግ ጥሰት ተግባራት

በጥቅሉ ከፍ ብሎ የተመለከትናቸው በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ስፖርተኞች ሙሉ በሙሉ ወይም አንዳንድ ጊዜ በከፊል እንዳይጠቀሟቸው ክልከላ የተደረገባቸውን ንጥረ-ነገሮችን ነው። በእዚሁ መሠረት አንድ አትሌት ከእነዚህ ንጥረ-ነገሮች ጋር በተያያዘ ምን ምን ተግባራትን ሲፈፅም በሕግ ተጠያቂ ይሆናል? የሚሉትን በሚከተለው መልኩ ለማሳየት ተሞክሯል።

  • የመጀመሪያው የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮች በሰውነት ውስጥ በምርመራ መገኘት ወይም ምልክት ማሳየት ነው፣
  • የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮችን መጠቀም ወይም ለመጠቀም መሞከር፣ ይህም ንጥረ-ነገሮችን ብቻ ሳይሆን የተከለከሉ ዘዴዎችንም ይጨምራል።
  • በአትሌቱ ወይም በሌላ ሰው የሚደረግ ግብረ-አበርነት ወይም የግብረ-አበርነት ሙከራ
  • የጸረ-አበረታች ተቆጣጣሪ አካልን መደበኛ ስራ ማስተጓጎል ወይም ተባባሪ አለመሆን
  • ለተገቢ የጸረ-አበረታች ምርመራ አስፈላጊ የሆነ ናሙና ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን/ሆን ብሎ ለመሸሽ መሞከር ወይም ወቅቱን ጠብቆ ለምርመራ አለመገኘት (Whereabouts Failure)
  • የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮችን ይዞ መገኘት ወይም የተከለከለን ዘዴ ሲተገብሩ መገኘት
  • የተከለከሉ ንጥረ-ነገሮችን ማዘዋወር ወይም ለማዘዋወር መሞከር
  • የጸረ-አበረታች የሕግ ጥሰቶችን ተመልክቶ ሪፖርት አለማድረግ ወይም ጥቆማ እንዳይሰጥ ማደናቀፍ ወዘተ…… የሚሉት ይገኙበታል።

ክልከላዎችን መተላለፍና የሕግ ተጠያቂነቱ

የወንጀል ተጠያቂነት

ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ የጸረ-ዶፒንግ ስምምነቶች አባል እንደመሆኗ አበረታች የሆኑ ንጥረ-ነገሮች (Performance Enhancing substances) መጠቀም በግልፅ ወንጀል ስለመሆኑ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 526 ላይ ተደንግጎ ይገኛል። በዚህ ድንጋጌ መሠረት ማንም ሰው፣-

  • ሀ/ በተፈጥሮና በሥልጠና የተገኘው የአካል ብቃት በጊዚያዊ መልክ በይበልጥ እንዲጨምር በማድረግ በስፖርት ውድድር ጊዜ አካላዊና ስነልቦናዊ የበላይነት ለማግኘት የሚረዱ በሕግ የተከለከሉና ሰው ሰራሽ ነገሮችን ያመረተ፣ ወደ አገር ውስጥ ያስገባ፣ የሸጠ፣ በባለሙያነት ያዘዘ፣ ያከፋፈለ ወይም
  • ለ/ በፊደል “ሀ” በተመለከቱት ነገሮች በህገወጥ መንገድ የተጠቀመ ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀምባቸው ያደረገ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ወይም ድርጊቱ ከባድ ጉዳት ባስከተለ ጊዜ ከአምስት ዓመት ባልበለጠ ፅኑ እስራት ይቀጣል፣ እንዲሁም ድርጊቱ የተፈፀመው በቸልተኝነት በሆነ ጊዜ ቅጣቱ ከሶስት ወር የማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሽህ ብር የማይበልጥ መቀጮ የሚሆን ሲሆን፣ በሕግ የተፈቀደን መድሃኒት ያለአግባብ ወይም ከተፈቀደለት ዓላማ ውጭ ያዘዘ ባለሙያም በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ይቀጣል።

አስተዳደራዊ ቅጣት

የኢትዮጵያ በሔራዊ የጸረ-አበረታች ፅ/ቤት እ.ኤ.አ በ2021 ተሻሽሎ የወጣውን የዓለም ዓቀፍ ጸረ-አበረታች ኮድና ሌሎች ዓለም ዓቀፍ ስታንዳርዶችን መሠረት በማድረግ በ2014 ዓ.ም ባወጣው የጸረ-ዶፒንግ መመሪያ አንቀጽ 2 ስር በርካታ የዶፒንግ ጥሰት ተግባራትና ሊወሰዱ የሚገባቸውን እርምጃዎች በመዘርዘር አስቀምጧል። በዚህም መሠረት፣-

  • የተከለከለ ጸረ-አበረታች ንጥረ-ነገር ይዞ መገኘት- በመደበኛነት የቃል ማስጠንቀቂያ ሆኖ ነገር ግን ሰውነቱ ውስጥ ምልክት ከታየ ከ2-4 ዓመት እገዳ
  • ለምርመራ እምቢተኝነ ማሳየት- የአራት ዓመት እገዳ ቅጣት
  • በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለሶስት ወቅታዊ የምርመራ ጊዚያት በተከታታይ አለመገኘት (Whereabouts failure)- ሁለት ዓመት እገዳ
  • የተከለከለ ጸረ-አበረታች መድሃኒት ማዛወር (Trafficking)- የመጀመሪያ ሲሆን አራት ዓመት ሆኖ ሲደጋገም እስከ እድሜ ልክ አገዳ ሊደርስ ይችላል።
  • የምርመራ ሂደትን በተለያየ መንገድ ማደናቀፍ- አራት ዓመት እገዳ ያስቀጣል፣
  • ለሌሎች አትሌቶች ጸረ- አበረታች እፅ ማቀበል ወይም እንዲጠቀሙ መገፋፋት- ከሁለት እስከ አራት ዓመት እገዳ ያስጥላል። በአጠቃላይ ብሔራዊ ፅ/ቤቱ ልዩ ልዩ ዓለም ዓቀፍ መመዘኛዎችን መሠረት አድርጎ እነዚህንና ሌሎች በርካታ አስተዳደራ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል።

ማጠቃለያ

ስፖርታዊ ውድድሮች የማኅበረሰብ ጤና መሠረት፣ የመዝናኛና የሕዝብ ለሕዝብ መቀራረቢያ ሁነኛ መድረኮች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ የሚደረግ የትኛውም የስፖርት ውድድር ከተጠቀሱት ፋይዳዎች ባለፈ ከፍተኛ መጠን ያለው ፋይናንስ የሚንቀሳቀስበት ተፅዕኖው እያደገ የሚገኝ የኢኮኖሚ ዘርፍ ነው። በዚህም ምክንያት የውድድር ጥራቱ ብሎም የሥልጠና እንዲሁም የማዘውተሪያ ቦታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ የመጡ ሲሆን ከአበረታች እፅ የፀዳ፣ በንፁህ ጥረት ውድድሮችን ማሸነፍ የሚለው መርህ በአብዛኛው የሥልጠና አካል ሆኗል። ይሁን እንጅ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የተከለከሉ ጸረ-አበረታች መድሃኒቶችን መጠቀም አሁንም የዘርፉ ትልቅ ፈተና ሆኖ ቀጥሏል። ይህ ችግር በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገራችን ስፖርተኞችም ጭምር ተስተውሏል። ከዚህ አኳያ ስፖርተኞችም ሆነ የሚመለከተው የስፖርት አስተዳደር እነዚህ እፆች በአትሌቶች ላይ ከሚያስከትሉት ከባድ ቅጣት በተጨማሪ የአገርንም ገፅታ በመጥፎ ጎን የሚያጠለሹ በመሆኑ ውድድሮች ከእነዚህ መድሃኒቶች የፀዱ ሆነው እንዲካሄዱ በትኩረት ሊሰራ ይገባል።

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ