መግቢያ
የኃይል ስርቆት በሀገር ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ አገልግሎት እና በመሠረተ ልማት ላይ ከባድ ጉዳት ከማድረሱም ባሻገር በሕግ የሚያስቀጣ ከባድ ወንጀል ነው። የኃይል ስርቆት ሲባል የጋዝ፣ የእንፋሎት ወይም የወሃ ኃይልን ከሌላ ግለሰብ ማሰራጫ ወይም መስመር በመውሰድ የራስ ማድረግን እንደሚያመለክት ከወንጀል ህጉ ድንጋጌ ማለትም አንቀጽ 666 አጠቃላይ አቀራረጽ መገንዘብ ይቻላል። በሌላ በኩል የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ሲባል ከህጋዊ መስመር ውጪ በሰንሰለት መጎተት፣ የኤሌክትሪክ ቆጣሪን በማጭበርበር መጠቀምን፣ የሌላ ግለሰብን የኤሌክትሪክ ማሰራጫ መውሰድን እንዲሁም በሌሎች ህገ-ወጥ መንገዶች የኤሌክትሪክ ኃይልን መጠቀምን እንደሚያካትት በኢነርጂ አዋጅ ከተቀመጡ ድንጋጌዎች ይዘት መረዳት ይቻላል። ይህ ድርጊት በፈጻሚዎቹ ላይ ከፍተኛ የሆነ የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል ሲሆን ቅጣቶቹም የገንዘብ መቀጮ፣ እሥራት ወይም ሁለቱንም በጣምራነት የሚያካትቱ ናቸው። በዚህ አጭር ጽሁፍ የኃይል ስርቆት ምንነትና በተለያዩ ህጎች ማለትም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግና በኢነርጂ አዋጅ ላይ የተቀመጡ ተጠያቂነቶች የሚዳሰሱ ይሆናል።
የኃይል ስርቆት ምንነት
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ መሠረት የኃይል ስርቆት በንብረት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች መካከል አንዱ ሲሆን በአንቀጽ 666 ስር እንደተመላከተው የኃይል ስርቆት ሲባል ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው ከሆነ የኃይል ማሰራጫ ወይም ለሌላ ሰው ከተዘረጋ መስመር ላይ ጋዝ፣ እንፋሎት፣ ኤሌክትሪክ ወይም ሌላ ዓይነት ኃይል በመውሰድ የራስ ማድረግን የሚያካትት ሲሆን ይህን ድርጊት መፈፀም አስቀጭነቱ ተደንግጓል። በዚህ የወንጀል ሕግ ድንጋጌ መሠረት ኃይል ሲባል የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ ሳይሆን የጋዝ፣ እንፋሎት ወይም ሌላ ኃይልን እንደሚያካትት ከድንጋጌው ጠቅላላ አገላለጽ መገንዘብ ይቻላል።
ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ በኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 አንቀጽ 28 መሠረት የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ማለት ማንኛውም የኤሌክትሪክ ኃይል በህገ-ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር ማገናኘት፣ መስመሩን ማሰናከል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰረቅ፣ ከሌላ መስመር ጋር እንዲገናኝ፣ መስመሩ እንዲሰናከል ማድረግ ወይም መስመሩ የተሰረቀ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር የተገናኘ ወይም የተሰናከለ መሆኑን እያወቀ ከዚሁ መስመር ማንኛውንም የኤሌክትሪክ ኃይል ለፍጆታ ማዋል ወይም መገልገልን እንደሚያመለክት ተገልጿል።
የኃይል ስርቆት የሚያስከትላቸው የወንጀል ተጠያቂነቶች
የእስራት ቅጣት
በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ እና የኤሌክትሪክ ኃይልን የሚመለከተው ልዩ አዋጅ ማለትም የኢነርጂ አዋጅ መሠረት የኃይል ስርቆት የፈጸመ ማንኛውም ሰው በእስራት ይቀጣል። ስለሆነም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 666 ስር እንደተጠቀሰው ማንኛውም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የሌላ ሰው ከሆነ የኃይል ማሰራጫ ወይም ለሌላ ሰው ከተዘረጋ መስመር ላይ ጋዝ፣ እንፋሎት፣ ኤሌክትሪክ ወይም ሌላ ዓይነት ኃይል በመውሰድ የራሱ ያደረገ ወይም የተገለገለበት እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ በቀላል እስራት ወይም ከ5 (አምስት ዓመት) በማይበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጎ እናገኛለን። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ የወንጀል ህጉ በጠቅላላው የሌላ ግለሰብን የጋዝ፣ እንፋሎት ወይም የኤሌክትሪክ ኃይልን መውሰድን በተመለከተ የሚደነግግ ሲሆን የኢነርጂ አዋጅ ከወንጀል ህጉ በኋላ የወጣ ከመሆኑም ባሻገር በልዩ ሁኔታ ስለኤሌክትሪክ ኃይል የሚደነግግ ልዩ ሕግ መሆኑን ነው። ስለሆነም የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆትን በተመለከተ ልዩ እና በቅርብ ጊዜ/special and recent law/ የወጣው ሕግ ተፈጻሚ እንደሚሆን ከሕግ አተረጓጎም መርሆች አንጻር መረዳት እንችላለን። ከዚህ በመቀጠል የኃይል ስርቆት የሚያስከትለዉን የእስራት ቅጣት፣ የገንዘብ መቀጩ እና የፍትሐብሄር ኃላፊነቶች በአጭሩ እንዳስሳለን።
በኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 አንቀጽ 28 መሠረት፡-
- ማንኛውንም የኤሌክትሪክ ኃይል መስረቅ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር ማገናኘት፣ መስመሩን ማሰናከል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰረቅ፣ ከሌላ መስመር ጋር እንዲገናኝ፣ መስመሩ እንዲሰናከል ማድረግ ወይም
- መስመሩ የተሰረቀ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር የተገናኘ ወይም የተሰናከለ መሆኑን እያወቀ ከዚሁ መስመር ማንኛውንም የኤሌክትሪክ ኃይል ለፍጆታ ማዋል ወይም መገልገል እስከ 5 (አምስት) ዓመት በሚደርስ እስራት ያስቀጣል።
የኢነርጂ አዋጁ ከላይ ከተጠቀሱት ተግባራት በተጨማሪ በአንቀጽ 29 ስር ተከታዮቹን ድርጊቶች አስቀጭ እንደሆኑ ደንግጎ እናገኛለን። እነዚህም፡-
- ከባለፈቃዱ ስምምነት ዉጪ ባለፈቃዱ በሚያቀርብበት የኤሌክትሪክ መስመር ላይ የኤሌክትሪክ ዕቃ ያስቀመጠ፣ የዘረጋ ወይም ያገናኘ፣
- በተዘረጋ የኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን ይዞታ ውስጥ የገነባ፣ ያረሰ ወይም የቆፈረ፣ በኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ግንባታዎችን አላፈርስም፣ ዛፎችን አልቆርጥም ያለ፣
- በባለፈቃዱ የተገጠመለትን የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ያሰናከለ ወይም እንዲሰናከል የፈቀደ ወይም የኤሌክትሪክ ፍጆታን እንዳይመዘግብ ያደረገ፣
- በተዘረጋለት የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ከባለፈቃዱ ይሁንታ ሳያገኝ ለዉጥ ያደረገ፣
- የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎችን ያለያየ ወይም የሰረቀ እስከ 5 (አምስት) ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል።
የገንዘብ መቀጮ
የኃይል ስርቆት ከሚያስከትለው የእስራት ቅጣት በተጨማሪ ወይም በአማራጭነት እንደ ወንጀሉ ክብደት በገንዘብ ያስቀጣል። የገንዘብ መቀጮው የሚወሰነው በደረሰው ጉዳት መጠን እና በህገ-ወጥ መንገድ ጥቅም ላይ በዋለው የኃይል መጠን ላይ ተመስርቶ ነው። በኢነርጂ አዋጅ ቁጥር 810/2006 አንቀጽ 28 ስር እንደተደነገገው፡-
- ማንኛውም የኤሌክትሪክ ኃይል መስረቅ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር ማገናኘት፣ መስመሩን ማሰናከል፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሰረቅ፣ ከሌላ መስመር ጋር እንዲገናኝ፣ መስመሩ እንዲሰናከል ማድረግ ወይም
- መስመሩ የተሰረቀ፣ በህገ-ወጥ መንገድ ከሌላ መስመር ጋር የተገናኘ ወይም የተሰናከለ መሆኑን እያወቀ ከዚሁ መስመር ማንኛውም የኤሌክትሪክ ኃይል ለፍጆታ ማዋል ወይም መገልገል ከእስራቱ በተጨማሪ ወይም በአማራጭነት እስከ 20,000.00 (ሀያ ሺህ) ብር የሚደርስ የገንዘብ መቀጮ እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል።
በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 29 ስር እንደተደነገገው ፡-
- ከባለፈቃዱ ስምምነት ዉጪ ባለፈቃዱ በሚያቀርብበት የኤሌክትሪክ መስመር ላይ የኤሌክትሪክ ዕቃ ያስቀመጠ፣ የዘረጋ ወይም ያገናኘ፣
- በተዘረጋ የኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን ይዞታ ውስጥ የገነባ፣ ያረሰ ወይም የቆፈረ፣ በኤሌክትሪክ ኢንስታሌሽን ላይ ጉዳት ሊያደርሱ የሚችሉ ግንባታዎችን አላፈርስም፣ ዛፎችን አልቆርጥም ያለ፣
- በባለፈቃዱ የተገጠመለትን የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ያሰናከለ ወይም እንዲሰናከል የፈቀደ ወይም የኤሌክትሪክ ፍጆታን እንዳይመዘግብ ያደረገ፣
- በተዘረጋለት የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ከባለፈቃዱ ይሁንታ ሳያገኝ ለዉጥ ያደረገ፣
- የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎችን ያለያየ ወይም የሰረቀ ከእስራቱ በተጨማሪ ወይም በአማራጭነት ከ25,000(ሀያ አምስት ሺ ብር) በማይበልጥ መቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጎ እናገኘዋለን።
የፍትሐብሄር ኃላፊነት
ምንም እንኳን በአዋጁ በግልጽ ባይጠቀስም የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት የፈጸመ ግለሰብ ወይም ድርጅት በኤሌክትሪክ አገልግሎት ሰጪው ተቋም ላይ ላደረሰው የገንዘብ ኪሳራ እና የንብረት ውድመት ሙሉ ካሳ እንዲከፍል በፍትሐብሄር ተጠያቂ ይሆናል፤ ይኸውም ጥፋት የፈጸመው ግለሰብ ወይም ድርጅት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ውል ካለው ከውሉ የሚመነጭ ኃላፊነት ሲኖርበት ጥፋት ፈጻሚው ውል ያልገባ ከሆነ ከውል ውጪ ኃላፊነት በሚለው በፍትሐብሄር ሕግ አንቀጽ 2027 እና 2028 መሠረት ማንም ሰው በራሱ ጥፋት በሌላ ግለሰብ ወይም ድርጅት ንብረት ላይ ጉዳት ካደረሰ ላደረሰው ጉዳት ኪሳራ የመክፈል ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጎ እናገኘዋለን። ይህ የካሳ ክፍያ የተሰረቀውን የኤሌክትሪክ ኃይል ግምት፣ የተበላሹ ንብረቶችን መጠገኛ እና ሌሎች ተያያዥ ወጪዎችን ያጠቃልላል።
ማጠቃለያ
የኤሌክትሪክ ኃይል ስርቆት ቀላል የማይባል በሀገር ደኅንነትና ኢኮኖሚ እንዲሁም ማኅበራዊ አገልግሎቶች ላይ ከባድ ጉዳት የሚያደርስ እና በሕግ የሚያስጠይቅ ከባድ ወንጀል መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል። ስለሆነም ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል እና ለሚመለከተው አካል ጥቆማ በመስጠት እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩን የኃይል መሰረተ ልማት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ