የሙስና ወንጀል

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የሙስና ወንጀል ከባድ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ የሚያስከትል ወንጀል ነው። ይህንን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት በአገራችን ወንጀሉን ለመከላከል ሕግ ከማውጣ በተጨማሪ ተቋማትን በማቋቋምም ወንጀሉን ለመቆጣጠር ልዩ ልዩ ጥረቶች ሲያደርግ ቆይቷል። ከዚህም ባሻገር የወንጀሉ ፈጻሚዎችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ እና የተወሰደውን የመንግሥት እና የሕዝብ ሀብት ለማስመለስ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ። በዚህ አጭር ጽሁፍ በሙስና ወንጀሎች አዋጅ 881/2007 የተካተቱ የሙስና ወንጀሎች ምንነትን እና የሚያስከትሉትን የሕግ ተጠያቂነት በአጭሩ እንመለከታለን፡፡

የሙስና ወንጀል ምንነት

እንደ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ መዝገበ ቃላት የቃሉ መሠረት ግዕዝ ሲሆን ትርጉሙም ጥፋት፣ መበስበስ፣ መፍረስ፣ በመጥፎ ድርጊት መተዳደር ማለት ነው፡፡ በሌላ በኩል እንደ ታዋቂው ዓለምዓቀፍ ድርጅት ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ትርጉም ሙስና በአደራ የተሰጠን ሥልጣን ለግል ጥቅም ማዋል ማለት ነው፡፡ “ብላክስ ሎው” የሕግ መዝገበ ቃላትም ሙስና ከሕጋዊ ኃላፊነት እና ከሌሎች ሰዎች ጥቅም በመጻረር ጥቅም ለማግኘት በማሰብ የሚፈጸም ድርጊት ነው በማለት ትርጉም ሰጥተውታል፡፡

የሙስና ወንጀል አይነቶች

አዋጅ 881/2007 በርካታ የሙስና ወንጀል ተግባራት የተካተቱ ሲሆን ለዚህ አጭር ጽሁፍ ዓላማ ሲባል የተወሰኑትን ብቻ ለማሳያነት በሚከተለው አግባብ በአጭሩ እንመለከታለን።

በሥልጣን አላግባብ መጠቀም የሙስና ወንጀል

የተሰጠን የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሥልጣን አላግባብ መጠቀምን አስመልክቶ ሕጉ የሚከተሉትን ዝርዝር ክልከላዎችን በግልጽ አስፍሯል። በዚህም “ማንኛውም የመንግሥት ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት ወይም በሌላ ሰው ጥቅም ወይም መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ ለማድረግ በማሰብ፣

  • የተሰጠውን ሹመት፣ ሥልጣን ወይም ኃላፊነት በግልጽ ተግባር ወይም በግድፈት ያለአግባብ የተገለገለበት እንደሆነ፣
  • በግልፅ ከተሰጠው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፎ የሠራ እንደሆነ ወይም፣
  • ሥልጣኑ ወይም ኃላፊነቱ የማይፈቅድለትን ጉዳይ በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖረው ወይም ከሥራው ከታገድ፣ ከተዛወረ፣ ከተሻረ ወይም ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ከተወ በኋላ የሰራበት እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከአስር ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ እንደሚቀጣ ተመላክቷል። ይህ እንዳለ ሆኖ የተፈጸመው ወንጀል ያደረሰው የጉዳት መጠን፣ የወንጀል ፈፃሚው ኃላፊነት ወይም በድርጊቱ የተገኘው ጥቅም ግምት ውስጥ ገብቶ እንደወንጀሉ ክብደት ቅጣቱ ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት እስራት እና ከአስር ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ ያስቀጣል፡፡

እነዚህ ግምት ውስጥ የሚገቡ ነገሮች በተደራረቡ ጊዜ እንደነገሩ ሁኔታ የእስራት ቅጣቱ እስከ ሀያ አምስት ዓመት የገንዘብ መቀጮው ደግሞ እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር ሊደርስ ይችላል።

ጉቦ መቀበል (Bribery)

ሌላኛው በመንግሥት ወይም በሕዝባዊ ድርጅቶች ሠራተኞች የሚፈጸም የሙስና ወንጀል ጉቦ መቀበል ሲሆን በአዋጅ 881/2007 አንቀጽ 10 ላይ ወንጀሉን የሚያቋቁሙ  ፍሬ ነገሮች ተዘርዝረዋል። በዚህም “ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በኃላፊነቱ ወይም በሥራ ግዴታው ማድረግ የማይገባውን ለማድረግ ወይም ማድረግ የሚገባውን ላለማድረግ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም እንዲሰጥ የጠየቀ፣ የተቀበለ ወይም የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከአርባ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል።

እዚህም ላይ የወንጀል ፈፃሚው ኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃ፣ ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት ግምት ውስጥ ገብቶ የእስር ቅጣቱ ከሰባት እስከ አስራ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት ከፍ ሊል ይችላል። በተጨማሪም የገንዘብ ቅጣቱ እንዲሁም ከአስር ሺህ እስከ መቶ ሺህ ሊደርስ እንደሚችል ተመላክቷል። እንዲሁም እነዚህ ግምት ውስጥ የሚገቡ ነገሮች በተደራረቡ ጊዜ ቅጣቱ እስከ ሀያ አምስት ዓመት ጽኑ አስራት እና እስከ ሁለት መቶ ሺህ ብር መቀጮ ድረስ ከፍ ሊል ይችላል።

የማይገባ ጥቅም መቀበል (Acceptance of Undue advantage)

አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 11 መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ማድረግ የሚገባውን ተግባር ለማከናወን ሲል ይህንኑ ተግባር ከመፈጸሙ በፊት ወይም ከፈጸመ በኋላ ጥቅም እንዲሰጠው የጠየቀ፣ ያገኘ ወይም የተስፋ ቃል የተቀበለ እንደሆነ እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከሃያ ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል። እንዲሁም በተፈጸመው ወንጀል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የኋላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃ የወንጀሉን አፈፃጸም ከባድ አድርጎት እንደሆነ የእስር ቅጣቱ ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ ጽኑ እስራትና ከአምስት ሺህ በማያንስ ስልሳ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል።

ሥራን በማይመች ሁኔታ መምራት

በዚህ የሙስና ወንጀል ዘርፍ የሚወድቁት ድርጊቶች ደግሞ በአዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 ስር እንደተመላከተው ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ ሥልጣኑን ወይም ኃላፊነቱን ተጠቅሞ

  • በንግድ ወይም በሌላ ሥራ፣ በግዢ ወይም በሽያጭ ወይም ከሚያከናውነው ሥራ ጋር በተያያዘ በማናቸውንም የሥራ ግንኙነት ማንኛውም ጥቅም የወሰደ ወይም ይህንን ጥቅም የሚያገኝበትን ውል የተዋዋለ ወይም ሌላ ዘዴ የፈጠረ፣
  • አግባብ ባለው ባለሥልጣን ከተወሰነው በላይ ዋጋ የእቃ ማቅረብ ውል፣ የሥራ መቋረጥ፣ ወይም ማናቸውንም የሥራ ውል የተዋዋለ ወይም በውል ከተመለከተው ዕቃ ወይም አገልግሎት ውጭ የተቀበለ እንደሆነ እንዲሁም፣
  • በሥራው ምክንያት በአደራ የተቀበለውን ወይም ሊጠብቀውና ሊከላከለው የሚገባውን የመንግሥት መስሪያ ቤት፣ የልማት ድርጅት ወይም ሕዝባዊ ድርጅት ጥቅም የሚጎዳ ተግባር በማናቸውም ዘዴ የፈጸመ እንደሆነ፣

እንደነገሩ ሁኔታ ከአንድ ዓመት በማያንስ ቀላል እስራትና ከሶስት ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአስር ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራትና ከመቶ ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ የሚቀጣ ይሆናል። የጥፋተኛው ኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃ፣ ግዴታው የተጣሰበት ዓላማ፣ የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት ወይም የደረሰው ጉዳት ከፍተኛነት ግምት ውስጥ ገብቶ ቅጣቱ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራት እና ከአስር ሺህ ብር በማያንስ እና ከሁለት መቶ ሺ የማይበልጥ መቀጮ ሊደርስ ይችላል፡፡ እንዲሁም እነዚህ ግምት ውስጥ የሚገቡ ነገሮች በተደራረቡ ጊዜ ቅጣቱ ከአስር ዓመት እስከ እስከ ሀያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እና ከሀያ ሺህ ብር እስከ አራት መቶ ሺህ ብር የሚደርስ መቀጮ ይሆናል።

ከባድ እምነት ማጉደል

እምነት መጉደል አስቀድሞ የተሰጠን እምነት አለአግባብ መጠቀምን ያመለክታል፡፡ በዚህም ከባድ እምነት ማጉደል ሲባል በአዋጅ 881/2007 አንቀጽ 31 መሠረት ያልተገባ ብልጽግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ወይም በአደራ የተሰጠውን ዋጋ ያለውን እቃ ወይም ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ማድረግ፣ ለሌላ ሰው ማድረግ፣ መውሰድ መሰወር፣ ለራሱ ወይ ለሌላ ሰው አገልግሎት ማዋል እና መሰል ድርጊቶችን መፈጸም ሲሆን ከሶስት እስከ ሰባት ዓመት ጽኑ እስራት እና ከአስር ሺህ ብር እስከ ሀምሳ ሺህ ብር መቀጮ እንደሚያስቀጣ ደንግጎ ይገኛል፡፡ በሌላ በኩል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣የጥፋተኛው የሥልጣን ደረጃ፣የደረሰው ጉዳት መጠን ከፍተኛነት እየታየ ቅጣቱ ከሰባት እስከ ሀያ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እና ከሀምሳ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር መቀጮ ድረስ ሊቀጣ ይችላል።

ከባድ አታላይነት

በአዋጁ አንቀጽ 32 መሠረት ማንኛውም የመንግሥት ወይም የሕዝባዊ ድርጅት ሠራተኛ ተገቢ ያልሆነን ብልጽግና ለራሱ ማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር፣ የራሱን ማንነት በመሰወር፣ መግለጽ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቅም፣ በማድረግም ሆነ ባለማድረግ ሌላውን ሰው በማታለል የተታለለው ሰው የራሱን ወይም የሌላውን ሰው የንብረት ጥቅም የሚጎዳ ድርጊት እንዲፈጽም ያደረገው ከሆነ ከሦስት እስከ አስር ዓመት በሚድርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ በሌላ በኩል የተገኘው ጥቅም ከፍተኛነት፣ የጥፋተኛው የሥልጣን ደረጃ፣ የደረሰው ጉዳት መጠን ከፍተኛነት እየታየ ቅጣቱ ከአምስት እስከ አስራ አምስት ዓመት ጽኑ እስራት እና ከአስር እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር መቀጮ ሊቀጣ ይችላል።

ማጠቃለያ

በጥቅሉ የሙስና ወንጀል ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሶስተኛ ሰው ለማስገኘት ታስቦ በመንግሥት፣ በመንግሥት የልማት ድርጅት እና በሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ሲሆን በመንግሥት እና ሕዝብ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ወንጀል ነው፡፡ በመሆኑም ወንጀሉን ለመከላከልና ተፈፅሞም ሲገኝ አጥፊዎችን ለሕግ በማቅረብ ረገድ ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ።