የመንግስት ሰራተኞች የስነ-ምግባር ጥሰት እና የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

ድስፕሊን የሚለው ቃል ስርዎ ቃሉ እንግሊዝኛ ቢሆንም ለተመሳሳይ ዓላማ በአማርኛም ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ ከቃሉ አግባብ መረዳት እንደሚቻለው፣ ለአንድ ጥፋት የሚወሰድ የቅጣት እርምጃ መሆኑን መገመት ይቻላል። ቅጣት ያለጥፋት አይኖርም ተብሎ ይገመታል። ምንም እንኳን ሁልጊዜ ይህ ግምት ባይሠራም፣ በአመዛኙ ትክክል ይሆናል። ነገር ግን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ተፈጸመ የተባለው ጥፋት በማስረጃ መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ ይህ ጠቅላላ አስተሳሰብ እንደተጠበቀ ሆኖ ከርእሱ አጻር፣ መታየት ያለበትን ጉዳይ የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ 96 እና ተከታዮቹ የተደነገገውን ቀጥለን እንመለከታለን።

ዓላማ

የዲስፕሊን ቅጣት ዓላማ የመንግሥት ሠራተኛው በፈጸመው የዲስፕሊን ጉድለት ተፀፅቶ በአመለካከቱና በሥነ-ምግባሩ እንዲታረምና ብቁ ሠራተኛ እንዲሆን ለማስቻል ወይም የማይታረም ሆኖ ሲገኝ ለማሰናበት እንደሆነ በአዲሱ የመንግሥት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 አንቀጽ 96 ላይ ተደንግጓል፡፡ የዲስፕሊን ጉድለት የፈፀመ የመንግሥት ሠራተኛ እንደ ጥፋቱ ክብደት የቃል ማስጠንቀቂያ፤ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፤ እስከ አሥራ አምስት ቀን ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ፤ እስከ ሦስት ወር ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ፤ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በሥራ ደረጃ እና ደመወዝ ዝቅ ማድረግ፤ ከሥራ ማሰናበት ቅጣቶች ሊወሰንበት እንደሚችል በአዋጁ አንቀጽ 97 ላይ ተደንግጓል፡፡

የዲሲፕሊን ጥፋት አይነቶች

አዋጁ ሁለት አይነት የዲሲፕሊን ጥፋት አይነቶች እንዳሉ ያስቀመጠ ሲሆን ይህም ቀላል እና ከባድ የዲሲፕሊን ጥፋት ናቸው፡፡ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት ቅጣቶች ማለትም የቃል ማስጠንቀቂያ፤ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ፤ እስከ አሥራ አምስት ቀን ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ ለቀላል የዲሲፕሊን ጥፋቶች የሚጣሉ ሲሆን እስከ ሦስት ወር ደመወዝ የሚደርስ መቀጮ፤ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በሥራ ደረጃ እና ደመወዝ ዝቅ ማድረግ፤ ከሥራ ማሰናበት ቅጣቶች ለከባድ የዲሲፕሊን ጥፋቶች የሚጣሉ ቅጣቶች ናቸው፡፡ ከሥራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ በማድረግ የተቀጣ የመንግሥት ሠራተኛ የቅጣት ጊዜውን ሲያጠናቅቅ ሠራተኛው ከሚሰራበት ሥራ መደብ እና ደረጃ ቀጥታ ግንኙነት ባለው ጥፋት ምክንያት ከስራ ደረጃና ደመወዝ ዝቅ ብሎ እንድሰራ ተቀጥቶ ካልሆነ በስተቀር ከመቀጣቱ በፊት ይዞት ከነበረው የሥራ መደብ ጋር ተመሳሳይ ክፍት የሥራ መደብ ካለ ያለምንም ተጨማሪ የደረጃ ዕድገት ሥነ-ሥርዓት፣ ከመቀጣቱ በፊት ይዞት ከነበረው የሥራ መደብ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ክፍት የሥራ መደብ ካልተገኘ ክፍት የሥራ መደቡ በተገኘ ጊዜ ያለምንም ተጨማሪ የደረጃ ዕድገት ሥነ-ሥርዓት፣ በሥራ መደቡ ላይ እንደሚመደብ ተደንግጓል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 97(5) መሠረት የመንግሥት ሠራተኛ በዲስፕሊን ከተቀጣ በኋላ ቅጣቱ በሪከርድነት ሊቆይና ሊጠቀስበት የሚችለው፣ ቀላል የዲስፕሊን ቅጣት ከሆነ ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለሁለት ዓመት፣ ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ከሆነ ቅጣቱ ከተወሰነበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ዓመት እንደሆነ ተደንግጓል፡፡

ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ምን ምን እንደሆኑ በአዋጁ አንቀጽ 98 ላይ በዝርዝር ተቀምጧል፡፡ በዚህም፡-

  • ሕጋዊ ትእዛዝን ባለማክበር፣ በቸልተኝነት፣ በመለገም፣ ወይም ሆነ ብሎ የአሠራር ሥነ-ሥርዓት ወይም የመንግሥትን ፖሊሲ ባለመከተል በሥራ ላይ በደል ማድረስ፤
  • ጉዳዮችን ሆን ብሎ ማዘግየት ወይም ባለጉዳዮችን ማጉላላት፤
  • ተቋምን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር መሠማራት ወይም ሥራ እንዳይሠራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤
  • በቀላል የዲስፕሊን ቅጣት እርምጃዎች ባለመታረም ያለበቂ ምክንያት በተደጋጋሚ ከሥራ መቅረት ወይም የሥራ ሰዓት አለማክበር፤
  • በሥራ ቦታ በጠብ አጫሪነት መደባደብ፤
  • በልማዳዊ ስካር ወይም በአደንዛዥ ዕፅ ሱስ በመመረዝ ሥራን መበደል፤
  • ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ፤
  • በሥራ ቦታ ለሕዝብ ሞራል ተቃራኒ የሆነ ድርጊት መፈጸም፤
  • የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈጸም፤
  • የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፤
  • በመሥሪያ ቤቱ ንብረት ላይ ሆን ብሎ ወይም በቸልተኝነት ጉዳት ማድረስ፤
  • በሥልጣን አለአግባብ መገልገል፤
  • በሥራ ቦታ ላይ ወሲባዊ ትንኮሳ ወይም ጥቃት መፈፀም፤

ከላይ ከተዘረዘሩት ጋር ተመሳሳይ ክብደት ያለው ሌላ የዲሲፕሊን ጉድለት መፈጸም ናቸው፡፡

በሌላ በኩል አዋጁ ከባድ የዲስፕሊን ቅጣት አይነቶችን ቢዘረዝርም ቀላል የዲስፕሊን ቅጣት የሚያስከትሉ ጥፋቶች ግን ምን ምን እንደሆኑ በግልፅ አላስቀመጠም፡፡

የዲስፕሊን እርምጃዎች አወሳሰድ ሥርዓት

ይህ አዋጅ በአንቀጽ 99 ላይ የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ ሥረዓትን ያስቀመጠ ሲሆን በዚሁም መሠረት ማንኛውም የመንግሥት መሥሪያ ቤት መደበኛ የዲስፕሊን ምርመራ የሚያካሂድና የውሳኔ ሀሳብ ለመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ የሚያቀርብ የዲስፕሊን ኮሚቴ ማቋቋም እንዳለበት አዋጁ ያስቀምጣል፡፡ የዲስፕሊን ቅጣት የማንኛውንም ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይጠብቅ ወይም ሳይከተል ሊወሰን እንደሚችልም በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

በዚሁም መሠረት በተቋቋመ የዲሲፕሊን ኮሚቴ አማካኝነት ተጣርቶ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበለት የመሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ በበቂ ወይም አሳማኝ በሆነ ምክንያት የውሳኔ ሀሳቡን ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ለመቀበል ወይም ውድቅ ለማድረግ ይችላል፡፡ ነገር ግን የማንኛውም መንግሥት መሥሪያ ቤት የበላይ ኃላፊ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 98 መሠረት ተቋምን አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር መሠማራት ወይም ሥራ እንዳይሠራ ሆን ብሎ ማወክ ወይም ከሚያውኩት ጋር መተባበር፤ ጉቦ መቀበል ወይም እንዲሰጠው መጠየቅ፤ የሌብነት ወይም የእምነት ማጉደል ድርጊት መፈጸም፤ የማታለል ወይም የማጭበርበር ድርጊት መፈጸም፤ ላይ የተመለከተውን ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት መፈፀሙን ካመነ በዲሲፕሊን ኮሚቴው ከባድ የዲስፕሊን ጥፋት የፈጸመው ሠራተኛ ከስራ እንዲሰናበት የቀረበለትን ውሳኔ ሀሳብና ጉዳይ ለመሥሪያ ቤቱ የሥራ አመራር ጉባኤ በማቅረብ ማስወሰን አለበት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በዚህ መሠረት በአንድ መስሪያ ቤት የሥራ አመራር ጉባኤ አማካይነት የተሰጠ ከሥራ የማሰናበት ውሳኔ በዚህ አዋጅ ወይም በሌላ ሕግ በተቋቋመ ማንኛውም አስተዳደራዊም ሆነ መደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሊታይ አይችልም።

በአዋጁ አንቀጽ 101 መሠረት የመንግሥት ሠራተኛ ላይ የዲስፕሊን ክስ ከቀረበ ሠራተኛው ከተጠረጠረበት ጉዳይ ጋር አግባብነት ያላቸው ማስረጃዎችን በማበላሸት፣ በመደበቅ ወይም በማጥፋት ምርመራውን ያሰናክላል ወይም በመንግሥት ንብረት ላይ ተጨማሪ ጉዳት ያደርሳል፣ ከተከሰሰበት ጥፋት ክብደት አንፃር የሌሎችን ሰራተኞች ሞራል የሚነካ ወይም ተገልጋይ ሕዝብ በመስሪያ ቤቱ ላይ ሊኖረው የሚገባውን እምነት ያዛባል ወይም ተፈፀመ የሚባለው ጥፋት ከስራ ያሰናብተዋል ተብሎ ሲገመት ከስራ ታግዶ እንዲቆይ የሚደረግ መሆኑን አዋጁ ደንግጓል፡፡ በዚህም አንድ ሠራተኛ ከስራና ከደመወዝ ታግዶ ሊቆይ የሚችለው ከሁለት ወር ለማይበልጥ ጊዜ ሲሆን የመንግሥት ሠራተኛው በተከሰሰበት የዲሲፕሊን ጉድለት ምክንያት ከስራ እንዲሰናበት ካልተወሰነበት በስተቀር በእግዱ ወቅት ሳይከፈለው የቀረው ደመወዝ ያለ ወለድ ልከፈለው እንደሚገባም ተደንግጓል፡፡

መጠነ ሰፊ የዲስፕሊን ችግር ያለበት መሥሪያ ቤት ላይ የሚወሰድ ልዩ የዲሲፕሊን እርምጃ

ይህ አዋጅ እንደ አዲስ ካካተታቸው ድንጋጌዎች ውስጥ መጠነ ሰፊ የዲስፕሊን ችግር ያለበት መሥሪያ ቤት ላይ የሚወሰድ ልዩ የዲሲፕሊን እርምጃ አወሳሰድ ሥነ ስርዓትን ማካተት ነው፡፡

በአንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ መጠነ ሰፊ የሆነ የዲስፕሊን ችግር እንዳለ እና ይህም ሁኔታ ለመሥሪያ ቤቱ ተልዕኮ መሳካት ጉልህ እንቅፋት በሚሆንበት ደረጃ ላይ የደረሰ ከሆነ በመሥሪያ ቤቱ ወይም መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ሆኖ የቆየበት ተቋም ወይም በኮሚሽኑ ጥያቄ መሠረት የማጥራት፣ የሥነ-ምግባር ግንባታ ልዩ ዕቅድ እንዲዘጋጅ እና ተግባራዊ እንዲደረግ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ሊፈቀድ ወይም ሊታዘዝ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡

በዚሁ መሠርት የማጥራት እና የሥነ-ምግባር ግንባታ ሂደት ተግባራዊ እንዲደረግ ሲታዘዝ ወይም ሲፈቀድ ሂደቱን ለማስተግበር የሚያስችል ልዩ ዕቅድ የሚያዘጋጅ እና ተግባራዊ የሚያደርግ አግባብነት ከአላቸው ተቋማት የሚመደቡ ባለሞያዎችን ያካተተ ግብረ-ኃይል ኮሚሽኑ እና የመንግሥት መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ከሆነለት ተቋም ጋር በመመካከር ያቋቁማል፡፡ ግብረ-ኃይሉ ከመሥሪያ ቤቱ ተገልጋዮች፤ ከባለድርሻ አካላት እና ሌላ ከማንኛውም ምንጭ በሚሰበሰብ መረጃ መሠረት በስፋት ከባድ ዲስፕሊን ግድፈት ያለባቸውን ሠራተኞች የስም ዝርዝር ያዘጋጃል፤ ዝርዝሩም ለመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች ይፋ ይደረጋል፡፡ ኮሚሽኑ ግብረ-ኃይሉ ይፋ በሚያደርገው ከባድ የዲስፕሊን ግድፈት ያለባቸው ሠራተኞች ዝርዝር ላይ ቅሬታ የሚሰማ እና የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ሆኖ የቆየበት ተቋም ጋር በመመካከር ያቋቁማል፡፡ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ቅሬታዎችን መርምሮ መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ሆኖ የቆየበት ተቋም የበላይ ኃላፊ ወይም የሥራ አመራር ጉባዔ የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል፤ በተለዩ ሠራተኞች ዝርዝር ውስጥ የገባ ማንኛውም ሠራተኛ ዝርዝሩ ይፋ በሆነ በአስራ አምስት ቀናት ውስጥ ቅሬታውን ለቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ማቅረብ ይችላል፡፡ ግብረ ኃይሉ በጥናት ላይ ተመስርቶ በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያለውን የሠራተኞች የዲሲፕሊን ግድፈት መጠንና የግድፈቱን ስፋት እና መሰል ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ተግባራዊ መደረግ ያለባቸውን የአሠራር፣ የአደረጃጀት እና ሌሎች ማሻሻያዎችን በተመለከተ መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ሆኖ የቆየበት ተቋም የበላይ ኃላፊ ወይም የሥራ አመራር ጉባዔ ምክረ-ሐሳብ ያቀርባል፤ መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ሆኖ የቆየበት ተቋም የበላይ ኃላፊ ወይም የሥራ አመራር ጉባዔ ምክረ-ሐሳብ ያቀርባል፣ ከግብረ ኃይሉ በቀረበለት ምክረ-ሀሳብ መሠረት አስፈላጊውን የማሻሻያ እርምጃዎች ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት ተለይተው የቀረቡ ሠራተኞች ላይ የግብረ ኃይሉን ሪፖርት እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴው ያቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ መነሻ በማድረግ ከሥራ እስከ ማሰናበት የሚደርስ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሊወስን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ የግብረ ኃይሉን ሪፖርትና ውሳኔ ሐሳብ መሠረት በማድረግ መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ ሆኖ የቆየበት ተቋም የበላይ ኃላፊ ወይም የሥራ አመራር ጉባዔ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፤ የበላይ ኃላፊ ወይም የሥራ አመራር ጉባዔ ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮች በማናቸውም የአስተዳደርም ሆነ መደበኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ሊታዩ አይችሉም በማለት በአዋጁ ተደንግጓል።

የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሥርዓት

አዋጁ በአንቀጽ 103 ላይ የቅሬታ አቀራረብና አፈታት ሥርዓት ዓላማ ለቅሬታዎች አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት፣ ለቅሬታዎች መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ስህተቶችንና ድክመቶችን ማረም፣ ሁሉንም የመንግሥት ሠራተኞች በእኩልነት ለማስተናገድ የሚያስችል፣ እና ፍትሐዊ የሆነ አሠራር በማስፈን የሰመረ የሥራ ግንኙነት ማዳበር እንደሆነ ይደነግጋል፡፡ የመንግሥት ሰራተኞች የተለያዩ መብቶችን በሚመለከት እንዲሁም የዲሲፕሊን ክስ ቀርቦባቸው የተሰጡ ውሳኔዎችን በተመለከተ ቅሬታ ሲኖራቸው ቅሬታቸውን በማጣራት የውሳኔ ሃሳብ ለመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ የሚያቀርብ የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ እንደሚቋቋም ይደነግጋል፡፡ የቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ከህጎችና መመሪያዎች አተረጓጎም ወይም አፈጻጸም፤ ከመብቶችና ጥቅሞች አጠባበቅ፤ ከሥራ አካባቢ ጤንነትና ደኅንነት ሁኔታዎች፤ ከሥራ ምደባና ደረጃ አሰጣጥ፤ ከሥራ አፈጻጸም ምዘና፤ በሥራ ኃላፊ ከሚፈጸሙ ተገቢ ያልሆኑ ተፅዕኖዎች፤ ከባድ የዲስፕሊን እርምጃዎች፤ ወይም የሥራ ሁኔታዎችን ከሚመለከቱ ሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚያቀርቧቸው ቅሬታዎችን እያጣራ የውሣኔ ሀሳብ የማቅረብ ኃላፊነት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ (የአዋጅ አንቀጽ 94 እና 95 )

የአስተዳደር ፍርድ ቤት ሥልጣን

የመንግሥት ሰራተኞች የሚያቀርቡትን የስራ ክርክር አይቶ የሚወሰን የአስተዳደር ፍርድ ቤት በአዋጁ ተቋቁሟል፡፡ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ይግባኝ የተባሉ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን በማጽናት በመሻር ወይም በማሻሻል ሊወስን ይችላል፡፡ በፍርድ ቤቱ በፍሬ ነገር ክርክር የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፡፡ ሆኖም የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሕግ ስህተት አለው ብሎ የሚያምን ወገን ይግባኝ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡

አዋጁ በአንቀጽ 130 ስር በአስተዳደር ፍርድ ቤት ስለ ሚታዩ ጉዳዮች በመዘርዘር ያስቀመጠ ሲሆን የሚከተሉትን ጉዳዮች አይቶ የመወሰን ሥልጣን ይኖረዋል፤ 1ኛ ከሚከተሉት ጋር በተያያዘ በመንግሥት ሠራተኞች የሚቀርቡለትን ይግባኞች ይህም ፤ ከሕግ ውጪ ከሥራ መታገድ ወይም አገልግሎት መቋረጥ፤ ከከባድ የዲስፕሊን ቅጣት ውሳኔ፤ ከሕግ ውጪ የደመወዝ ወይም ሌሎች ክፍያዎች መያዝ ወይም መቋረጥ፤ በሥራ ምክንያት ከደረሰ ጉዳት የመነጨ መብት መጓደል፤በዚህ አዋጅ አንቀጽ 97(2) ከተመለከተው በስተቀር በቅሬታ አጣሪ ኮሚቴ ታይተው ውሳኔ ከተሰጠባቸው ጉዳዮች፤ የሥራ መልቀቂያና የአገልግሎት ማስረጃ ለማግኘት ከቀረበ ጥያቄ ማየት ይችላል፡፡

2ኛ ጊዜያዊ ሠራተኞችና በማቋቋሚያ ሕጋቸው የመንግሥት ሠራተኞች ሕግ መሠረታዊ ዓላማዎችን በመከተል በራሳቸው የውስጥ መመሪያ ሠራተኞቻቸውን እንዲያስተዳድሩ የተፈቀደላቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ ሠራተኞች የሚያቀርቧቸውን ይግባኞች ማየት ይችላል፡፡

3ኛ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ይግባኝ የተባለበትን አስተዳደራዊ ውሳኔ ከመረመረ በኋላ ውሳኔውን ለማጽናት፣ ለመሻር ወይም ለማሻሻል ይችላል፡፡ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በሰጠ በአምስት የሥራ ቀናት ውስጥ የውሳኔውን ግልባጫ ለይግባኘ ባዩ ወይም ለመስሪያ ቤቱ ተወካይ እንዲደርሰው ማድረግ አለበት፡፡ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ በፍሬ ነገር ክርክር የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ ይሆናል፤ ሆኖም የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ውሳኔ የሕግ ስህተት አለበት ብሎ የሚከራከር ወገን ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ ይችላል፡፡

የአስተዳደር ፍርድ ቤት መር የአስማሚነት ሚና እና የአፈጻጸም ሂደት

ይህ አዋጅ እንደአዲስ ከአካተታቸው ድንጋጌዎች ውስጥ የአስተዳደር ፍርድ ቤት መር የአስማሚነት ሚና እና የአፈጻጸም ሂደት አንዱ ሲሆን በአዋጁ አንቀጽ 132 መሠረት የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ የይግባኝ ቅሬታ በፍርድ ሂደት ከማየቱ በፊት የከባድ የዲሲፕሊን ጥፋትን ሳይጨምር ባለጉዳዮች በፍቃደኝነት እንዲስማሙ ጥረት ማድርግ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ባለጉዳዮችን እንዲስማሙ የሚረዱ ብቃታቸው የተረጋገጠ አስማሚዎች በኮሚሽኑ እንደሚመደቡለት እንዲሁም አገልግሎት አሰጣጥን የሚያሻሻል ተጨማሪ አማራጭ ክርክር መፍቻ የአስተዳደር ፍርድ ቤት መር አስማሚነትና የማስማማት ሂደቶች፣ መርሆች፣ የአስማሚዎች ሥነ-ምግባር እና የአሠራር ሥርዓት ኮሚሽኑ መመሪያ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

ማጠቃለያ

የመንግሥት ሰራተኞች የተሰጣቸውን ኃላፊነት፣ ተግባርና ተልዕኮ በብቃት፣ በጥራትና በውጤታማነት እንዲወጡ ተገቢውን የሰነ-ምግባር መርሆች አክብረው ስራቸውን ሊሰሩ ይገባል፡፡ ነገር ግን ይህ በመተላለፍ የሰነ-ምግባር ግድፈት የፈፀሙ እንደሆነ አስተዳደራዊ ተጠያቂነት የሚያስከትልባቸው እና በዲሲፕሊን የሚጠየቁበት ሁኔታ በህጉ ተቀምጧል፤ ይህም የዲሲፕሊን ቅጣት ከቃል ማስጠንቀቂያ እስከ ከሥራ መሰናበት ሊያደርሳቸው ይችላል፤ በመሆኑም የመንግሥት ሰራተኞች ሥራቸውን በስነ-ምግባር መከወን ይኖርባቸዋል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ