በሀይል ተግባር ማስረጃ መሰብሰብ ወይም ምርመራ ማከናወን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና በወንጀል የሚያስቀጣ ድርጊት መሆኑን ያውቃሉ?

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

መግቢያ

የዚህ አጭር ጽሑፍ መሠረታዊ ዓላማ በአንድ በኩል በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠርና ለመከላከል የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 ‘ን ለማሻሻል ሰኔ 10 ቀን 2017 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጸደቀውን አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ላይ የተመለከቱትን ልዩ የምርመራ ዘዴዎች ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም በልዩ የምርመራ ዘዴዎች የሚሳተፉ መርማሪዎች ከአቅማቸው በላይና ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ምክንያት ተገደው ወይም በተጽእኖ ስር ሆነው ከግዴታቸው ጋር በተያያዘ ወንጀል ሲፈጽሙ በዋና ወንጀል አድራጊነት ወይም በግብረ-አበርነት የማይከሰሱበት ሁኔታና ምክንያት ከዓለም አቀፍ ስምምነቶችና ሕጎች አንጻር በመዳሰስ ለአንባቢው ግልጽ ለማድረግ፤ በሌላ በኩል ደግሞ በሃይል ተግባር ማስረጃ መሰብሰብ ወይም ምርመራ ማከናወን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እና በወንጀል የሚያስቀጣ ተግባር መሆኑን ለሕብረተሰቡ ለማስታወስ ነው። 

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት የኢኮኖሚ ደኅንነት ሥጋት ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ የፋይናንስ ሥርዓቱ የተረጋጋ፤ ግልፅኝነት ያለውና ጤናማ እንዳይሆን በማድረግ የኢኮኖሚ ሥርዓቱን የሚያናጋ ከባድና ውስብስብ ወንጀል ነው። ተፅዕኖውም ድንበር ተሻጋሪና ዓለም አቀፋዊ ችግር በመሆኑ ወንጀሉን ለመዋጋት በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚደረገው ጥረት አካል ለመሆን ኢትዮጵያ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በማውጣት ተግባራዊ የማድረግ ግዴታ አለባት። ከዚህ አንጻር ወንጀሎቹን የሚመለከቱ አዳዲስ የሕግ ማዕቀፎችን በማውጣትና በተግባር ላይ ያሉ የሕግ ድንጋጌዎችን ከዓለም ዓቀፉ የፋይናንስ ግብረ ኃይል ምክረ ሃሳቦች (Reccommendations of Financial Action Task Force) እና ሌሎች ኢትዮጵያ ፈርማ ከተቀበለቻቸው ስምምነቶች (ለምሳሌም ከተባበሩት መንግሥታት ድንበር ተሻጋሪና የተደራጁ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው ስምምነት፣ ከተባበሩት መንግሥታት ጸረ ሙስና ስምምነት ወዘተ…)  ጋር የተጣጣሙ እንዲሆኑና ወቅቱን በጠበቀ መልኩ በተግባር ያጋጠሙ ክፍተቶችን ለማሟላት የሕግ ማዕቀፉን ማሻሻል አስፈልጓል።

በተለይም በነባሩ አዋጅ ቁጥር 780/2005 ላይ የተመለከቱት ግልጽነት የጎደላቸውን ድንጋጌዎች ግልጽ አድርጎ ለመደንገግ አስፈላጊ በመሆኑ ከእነዚህም መካከል በሽፋን ስር የሚደረጉ ምርመራዎችን ጨምሮ ሌሎች ልዩ የምርመራ ሥልቶችን የሚተገበሩበት አግባብ በግልጽ በማስቀመጥ እጅጉን ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር ልዩ የምርመራ ዘዴ ምንነትና አስፈላጊነት እንዲሁም ምርመራውን ለማከናወን ተልእኮ ተቀብለው ስራቸውን በሚሰሩበት ጊዜ ተገደውና ያለፍላጎታቸው ወንጀሉን ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ዋና ወንጀል አድራጊ ሆነው በሚገኙበት ጊዜ የሚኖራቸውን የሕግ ከለላ (Legal immunity) እና ተያያዥ ጉዳዮች ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር መመልከት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ልዩ የምርመራ ዘዴዎች ምንነትና አስፈላጊነት

ዓለም በዘመን አመጣሽ ሥልጣኔዎችና ቴክኖሎጂዎች እያደገችና እየተሳሰረች በምትሄድበት ጊዜ የወንጀል አፈፃፀም ዘዴዎችም እጅግ በጣም በረቀቀና በተወሳሰበ ሁኔታ ዓለም አቀፍ ባህሪ በመላበስ ይፈፀማሉ። ወንጀሎች በአፈፃፀማቸውና በባህሪያቸው በሕብረተሰቡ፣ በዜጎችና በመንግሥት ላይ የሚፈጥሩት ስጋትና የሚያስከትሉት ውጤትም ይለያያል። በረቀቀ የአፈፃፀም ሥልትና ዘዴ ዓለም አቀፋዊ ባህሪ ያላቸው፣ ከፍተኛ ማሕበረሰባዊ ጉዳት የሚያስከትሉ እጅግ በጣም የተወሳሰቡና ከባባድ ወንጀሎች ሲፈፀሙ በመደበኛ የምርመራ ስልትና ዘዴ ወንጀለኞችን መመርመር፤ መያዝ፣ ክስ መመስረትና ማስቀጣት አይቻልም። ከዚህ አንጻር ከመደበኛ የምርመራ ስልቶች ባሻገር ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን ተግባራዊ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው።

ልዩ የምርመራ ዘዴዎች ከባድ ወንጀሎችንና የወንጀሎቹን ተጠርጣሪዎች ለመለየት፣ ለመመርመርና መረጃን ለመሰብሰብ ዒላማ የሆኑ ተጠርጣሪዎች ሳያውቁ በመርማሪዎች የሚተገበሩ ዘዴዎች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል፣ ክትትል፣ ጠለፋ፣ በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ (ሰርጎ መግባት፣ የይምሰል ግንኙነት መፍጠር…)፣ በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍ ወዘተ.. ይጠቀሳሉ። እነዚህ የምርመራ ስልቶች ያስፈለጉበት ዋና ምክንያት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ  ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብን ጨምሮ በአፈጻጸማቸው ውስብስብና ከባድ የሆኑ ወንጀሎች በመደበኛ የምርመራ ስልቶች ሊደረስባቸው የማይችሉ በመሆናቸው ነው። ከዚህ አንጻር በባህሪያቸው ረቂቅ፣ ውስብስብና ከባባድ ለሆኑ ወንጀሎች ተነሳሽ (Proactive Method of Investigation) የምርመራ ዘዴን ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

እዚህ ላይ ግንዛቤ ሊወሰድበት የሚገባው መሠረታዊ ነጥብ እነዚህ ልዩ የምርመራ ስልቶች በማስገደድ ማስረጃ ከመሰብሰብና ምርመራ ከማከናወን ተግባር ፍጹም የተለየ ጽንሰ-ሐሳባዊና ሕጋዊ ልዩነት ያላቸው መሆናቸውን ነው። በመሰረቱ በማስገደድ ማስረጃን መሰብሰብ ወይም ምርመራ ማከናወን ኢ- ሕገ መንግሥታዊ ከመሆኑ በተጨማሪ የወንጀል፣ የፍትሐ ብሔርና አስተዳደራዊ ተጠያቂነት የሚያስከትል ሕገ ወጥ ተግባር ነው። ስለዚህ በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ እና  በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍ መርማሪዎች ወይም ወኪሎቻቸው በድብቅ፣ ማንነታቸውን በመቀየር ወይም ተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳስለው በመቅረብና በመቀላቀል ወንጀል ፈጻሚዎችንና የወንጀል ፍሬዎችን መከታተልና ማስረጃዎችን ማሰባሰብ የሚችሉባቸው የምርመራ ስልቶች እንጂ በማስገደድ ማስረጃ የሚሰባሰብባቸው መንገዶች አለመሆናቸው መገንዘብ ያስፈልጋል።

በሌላ በኩል ልዩ የምርመራ ስልቶች በዘፈቀደ፣ ያለምንም ዓይነት ክትትልና ቁጥጥር ሳይሆን ጥብቅ ሥርዓት በተከተለ አግባብ የሚፈጸሙ ናቸው። የወንጀል ፍሬን ተከታትሎ ለመለየት በባንክ ሂሳቦች እና በሌሎች ተመሳሳይ ሂሳቦች ላይ ክትትል ለማድረግ፤ የኮምፒዉተር ሥርዓቶችን፣ መረቦችንና ሰርቨሮችን ለመለየት፣ መገናኛዎችን በክትትል ሥር ለማዋል ወይም ለመጥለፍ፤ የደብዳቤ ልውውጦችን ለመጥለፍ እና ለመያዝ፤ በሽፋን ሥር ምርመራን ለማድረግ (Undercover operation) እና ተጠርጣሪን ወይም ማንኛውንም ዕቃ በቁጥጥር ስር ማስተላለፍን (Controlled Delivery) ጨምሮ ማከናወን የሚቻልበት አግባብ በነባሩ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 25 እና 26 ስር ተደንግገው የነበሩ ናቸው። እነዚህ ልዩ የምርመራ ዘዴዎች ነባር አዋጁን ለማሻሻል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰኔ 10 ቀን ባጸደቀው በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ (ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ላይም በተመሳሳይ ሁኔታ የተደነገጉ ሲሆን እንደሚከተለው እንዳስሳቸዋለን።

በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ (Undercover operation)

በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ እንደ ወንጀሎች አፈጻጸም ሁኔታ ትርጓሜው ሊለያይ ቢችልም በዋናነት ግን ምርመራውን የሚያከናውነው አካል በበላይ ሃላፊው አቅጣጫ ሰጭነት እና ፍርድ ቤቱ በሚሰጠው ፈቃድ መሠረት በጊዜያዊነት ማንነቱ እንዳይታወቅ በማድረግ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነት በገንዘብ መርዳት ወንጀልን፣ የአመንጪ መንጀልን፣ የወንጀሉን ተሳታፊዎች፣ የወንጀሉን ፍሬ ወይም ሌሎች ማስረጃዎች የሚሰበሰብበት የምርመራ ዘዴ ነው ተብሎ ሊተረጎም ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ የምርመራ ስልት በዋናነት ወንጀል ሳይፈጸም በፊት አስቀድሞ ለመከላከል ወይም እየተፈጸመ ሳለ ውጤት ሳያገኝ እንዲቀር የሕግ አስከባሪ አካላት ማንነታቸውን ደብቀው ማስረጃ ወይም መረጃ ለመሰብሰብ የሚገለገሉበት ምስጢራዊ ኦፕሬሽን ሲሆን በማስገደድ ማስረጃ ከመሰብሰብ ጋር ምንም ዓይነት ጽንሰ-ሐሳባዊም ሆነ ሕጋዊ ግንኙነት የለውም።  

በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍ (Controlled Delivery)

በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍ ማለት የወንጀል ድርጊትን ለመመርመርና የድርጊቱን ተሳታፊዎች ለመለየት ዓላማ፣ የወንጀል ፍሬን ወይም ሕገ-ወጥ የሆነን ወይም የሚጠረጠር ሌላ ጭነትን ወይም ጥሬ ገንዘብን አግባብ ባላቸው ባለሥልጣናት እውቅናና ቁጥጥር ስር ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲዘዋወር፣ ከኢትዮጵያ እንዲወጣ፣ የኢትዮጵያን ግዛት አቋርጦ እንዲያልፍ ወይም ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የመፍቀድ ስልት ነው። ስለዚህ የወንጀሎች ፍሰት ለመከታተል፣ እውነተኛ ምንጮቻቸውን፣ የጉዞ መንገዶቻቸውንና መድረሻቸውን ለመለየት ጥቅም ላይ የሚውል ልዩ የምርመራ ስልት ነው።  ይህ የምርመራ ስልትም በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ራሱን የቻለ ልዩ የምርመራ ስልት ሲሆን በማስገደድ ማስረጃ ከመሰብሰብ ወይም ምርመራ ከማድረግ ተግባር የሚመሳሰልበት አንድም የሕግ ሆነ የጽንሰ-ሐሳብ ምክንያት የለም።

ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን ለመተግበር የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች

ልዩ የምርመራ ዘዴዎች የተጠርጣሪዎች የነጻነትና የግላዊነት መብቶችን የሚጥሱበት ሁኔታ እንዳይኖር ለመከላከል በጥንቃቄ የሚከናወኑ ናቸው። በሌላ አነጋገር የምርመራ ምክንያት የሆኑት ወንጀሎች ከአፈፃፀም ባህሪያቸውና ረቂቅነት እንዲሁም ከሚያስከትሉት አደጋና ሀገራዊ ጉዳት አንጻር በመደበኛ የምርመራ ስልትና አካሄድ ውጤት ማምጣት የማይቻልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት አስገድሞ ሊረጋገጥ ይገባል። ስለዚህ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ ልዩ የምርመራ ቴክኒኮችንና መሣሪያዎችን መጠቀምን በሕግ ቢፈቀድም እንኳን ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ሕግ አውጭው ቢያንስ የተወሰኑ የሕግ ገደቦችን (Minimum Legal Restrictions) ማዘጋጀት ይኖርበታል። 

ለምሳሌ በተቻለ መጠን ለመደበኛ የምርመራ ስልቶችን ቅድሚያ መስጠት፣ እነዚህ ስልቶች ውጤት ባለማምጣታቸው ምክንያት ልዩ የምርመራ ስልት ተግባራዊ ማድረግ የግድ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም በአተገባበራቸው ላይ ገደቦች ማስቀመጥ፣ መቼና ለምን ያህል ጊዜ ጥቅም ላይ እንደሚውሉ መወሰን፣ ከፍርድ ቤት ወይም ከሌላ ገለልተኛ አካል የቅድመ ፈቃድ መስፈርት እንዲያሟሉ ማድረግ፣ አነስተኛ ጣልቃ ገብነት ያላቸውን ቴክኒኮችና መሣሪያዎች ለመጠቀም ቅድሚያ መስጠት፣ የሕጋዊነት፣ የተመጣጣኝነት፣ የፍትሐዊነትና የምክንያታዊነት መስፈርቶች መሟላታቸውን አስቀድሞ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። ከዚህ አንጻር በማሻሻያ አዋጁ (አዋጅ ቁጥር 1387/2017) ላይ በሽፋን ስር ምርመራ የሚደረግበት አግባብና ሂደት፣ በተለይም የፍርድ ቤት ፈቃድ አስፈላጊ ስለመሆኑ፣ በዚህ አግባብ የሚሰጥ ፈቃድም ስልቱን ለመተግበር የሚያስችል አሳማኝ ምክንያት መኖሩን በመመርመር ስለመሆኑ፤ አስቸኳይና ልዩ ሁኔታ ሲያጋጥም ለአርባ ስምንት ሰዓታት ብቻ በዐቃቤ ሕግ ፈቃድ ሊከናወን የሚችል ስለመሆኑና በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ በፍርድ ቤት ሊጸድቅ ወይም ውድቅ ሊደረግ የሚችል ስለመሆኑ፣ ልዩ የምርመራ ሥልቱ በፍርድ ቤት ከተፈቀደም ከ90 ቀናት በላይ መቆየት እንደሌለበት፣ በልዩ ሁኔታ 30 ቀናት ሊጨመር እንደሚችል በምንም መልኩ ግን ከአራት ወር በላይ መቆየት እንደሌለበት በግልጽ ተመላክቷል። ስለዚህ በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራም ሆነ በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍ መርማሪ ፖሊስ ወይም ዓቃቤ ሕግ በዘፈቀደ የሚጠቀሙባቸው የምርመራ ስልቶች ሳይሆኑ በሕግ አግባብ ገደብ የሚደረግባቸው፣ በመርህ ደረጃም ከፍርድ ቤት ትእዛዝ ውጪ የማይከናወኑ መሆናቸውንና ፍርድ ቤቱ ራሱም የሚፈቅደው አሳማኝ ምክንያት መኖሩን አስቀድሞ በማረጋገጥ መሆን እንደሚኖርበት መገንዘብ ያስፈልጋል።

ምርመራውን የሚያከናውን ሰው ያለው የሕግ ከለላ (Legal Immunity)

 እነዚህ የምርመራ ስልቶች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸረ ሙስና ስምምነት (አንቀጽ 50)፣ በተባበሩት መንግሥታት ጸረ ድንበር ተሻጋሪና የተደራጁ ወንጀሎች ስምምነት (አንቀጽ 20) እንዲሁም በሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች እውቅና የተሰጣቸው የምርመራ ሥልቶች ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሕግጋት እና የፖሊሲ ማዕቀፍ አንጻርም በወንጀል ፍትሕ ፖሊሲው፣ በነባሩ አዋጅ ቁጥር 780/2005፣ በንብረት ማስመለስ አዋጅ ቁጥር 1364/2017 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 1176/2012 ላይ እውቅና የተሰጣቸው ናቸው። 

ሆኖም እነዚህን የወንጀል ምርመራ ስልቶች እንዲያስፈጽም ተልእኮ ተሰጥቶት የሚሰራ መርማሪ ፖሊስ ወይም ወኪሉ ከኣቅሙ በላይ በሆነና ፍጹም በሆነ መገደድ ምርመራ ከሚደረግባቸው ተጠርጣሪዎች ጋር በግብረ-አበርነት ወይም በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን ወንጀል ቢፈጽም የሕግ ተጠያቂነቱን ምን መሆን አለበት? የሚለውን ጉዳይ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ከክስ ነጻ የሚደረግበትን ሁኔታ የደነገጉ ሲሆን የሀገራችን ሕጎች በዚህ አግባብ ያስቀመጡት ግልጽና በቂ ድንጋጌ አልነበረም። ይህም ማለት በ2005 ዓ.ም የወጣው (የጸረ መኒ-ላውንደሪንግ) አዋጅ በአንቀጽ 26 (1) ስር በተወሰነ ደረጃ ‘ክስ አይቀርብም’ የሚል ድንጋጌ ቢኖረውም ከአፈጻጸም አንጻር የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመፍታት ግን አያስችልም፡፡ ይህን የሕግ ክፍተት ለመሙላት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ንብረት ወይም ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ቁጥር 780/2005 ‘ን የሚያሻሽል አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ከክስ ነጻ መሆን የሚቻልበት አግባብን በአንቀጽ 26 (4) ስር እንደሚከተለው በግልጽ ደንግጓል። 

“በዚህ አዋጅ መሠረት በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ  ሰው በግዴታው ላይ እያለ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያትና ከፈቃዱ ውጭ ሆኖ ከግድያ ወንጀል በስተቀር ለሚፈጽመው የወንጀል ድርጊት የወንጀል ክስ አይቀርብበትም።”

በመሆኑም ይህ ድንጋጌ ምን ማለት ነው? የሚለውን ማየት ተገቢነት ይኖረዋል። 

ከላይ እንደተገለጸው ልዩ የወንጀል ምርመራ ዘዴ የሚያስፈልግበት ዋና ዓላማ በመደበኛው የምርመራ ዘዴ ማስረጃ ማሰባሰብ ባልተቻለበት የወንጀል ጉዳይ ላይ አስፈላጊ የሆነ ማስረጃ ለማሰባሰብና ለማደራጀት ነው። ስለዚህ ይህንኑ ምርመራ የሚያከናውን መርማሪ ወይም ወኪሉ ትክክለኛ ማንነቱን ደብቆ ከተጠርጣሪዎች ጋር ተመሳስሎ፣ ተቀላቅሎ ወይም ተዋህዶ በሚንቀሳቀስበት ጊዜና ሁኔታ ከፍላጎቱ ውጪ ወይም ተገዶ የወንጀሉ ተካፋይና ግብረ-አበር ሊሆን ይችላል። 

እነዚህን ምርመራዎች ለመፈጸም ተልእኮ የተሰጠው ሰው ተገዶ፣ በተጽእኖ ወይም ከአቅሙ በላይ በሆነ ማንኛውም ምክንያት ግዴታውን በሚፈጽምበት ጊዜ ወንጀል ከፈጸመ ወንጀሉን የፈጸመው አስቦ፣ ድርጊቱንና የሚያስከትለውን ውጤት በራሱ አስልቶና ተቀብሎ እስካልሆነ ድረስ በወንጀል እንዲጠየቅ ማድረግ ትርጉም አይኖረውም። ይህ ማለት ግን መርማሪው ወይም ወኪሉ በስውር ማስረጃ በሚሰበስብባቸው ተጠርጣሪዎች ላይ በፈለገ ጊዜ ወንጀል ይፈጽማል ማለት አለመሆኑን ይልቁንስ ማንነቱን ደብቆ ከእነዚህ ወንጀል ፈጻሚዎች ጋር ተመሳስሎ በሚንቀሳቀስበት ጊዜ የወንጀሉ ተካፋይ ወይም ግብረ አበር በመሆን ወይም በእነሱ አስገዳጅ ትእዛዝ መሠረት ወንጀል ሲፈጽም ማለት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። 

ለምሳሌ በአንድ የተደራጀ የወንጀል ቡድን ውስጥ ተቀላቅሎ (የቡድኑ አባል መስሎ) ወንጀል የሚከታተል መርማሪ የዘረፋ ተግባር እንዲፈጽም በተሰጠው ተልዕኮ ይህንን ዘረፋ አልፈጽምም ማለት በራሱ ሕይወት ላይ አደጋን የሚጋርጥ ስለሚሆን በተሰጠው ትእዛዝ መሠረት ወንጀሉን በሚፈጽምበት ጊዜ ተጠያቂነት እንዲኖርበት ማድረግ አስቀድሞ የተላከበትን ሌላኛው ዓላማ ጋር የሚጣረስ ይሆናል፡፡ በሌላ ተጨማሪ ምሳሌ ሲገለጽ በተደራጀ መንገድ የማታለል ወንጀል በመፈጸም ከተለያዩ ሰዎች የባንክ ሂሳብ ውስጥ ገንዘብ መውሰድ እንዲችል መመሪያ የተሰጠው አንድ የሰርጎ ገብ መርማሪ ወንጀሉን አስቀድሞ ለመፈጸም ፍላጎት ኖሮት ሳይሆን የተሰጠውን የልዩ ምርመራ ተልዕኮ ለማሳካት የሚያደርገው ተግባር በመሆኑ በተመሳሳይ መልኩ ከክስ ነጻ ይሆናል፡፡

ስለሆነም መርማሪው ወይም ወኪሉ በተጠርጣሪዎች ወይም በሌላ ሦስተኛ ወገኖች ላይ ወንጀል ሊፈጽምባቸው ይችላል፤ ወንጀሉን ከፈጸመባቸው በኋላም በወንጀል አይጠየቅም የሚል ሳይሆን ከተጠርጣሪዎች ጋር የወንጀል ተካፋይ ወይም ግብረ-አበር በመሆን በራሱ ፈቃድ አስቦና ፈቅዶ ሳይሆን ያለፈቃዱ፣ ተገዶ፣ በተጽእኖ፣ ወይም በተጠርጣሪዎች ሕገ ወጥ ትእዛዝ ወይም ከአቅሙ በላይ በሆነ ማንኛውንም ምክንያት ሌላ ከባድ ጉዳትን ለማስቀረት ወይም የተሰጠውን ሕጋዊ ተልእኮ ለማሳካት ሲል ወንጀል የሚፈጽምበት ሁኔታ ሲኖር ከወንጀል ክስ ነጻ የሚደረግበትን ሁኔታ ለማመላከት የተደነገገ ድንጋጌ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ይህ መርህ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 75 ላይ ከተመላከተው “አስገዳጅ ሁኔታ” (“Necessity”) ተብሎ ከሚታወቀው ጠቅላላ መርህ ጋር ተመሳሳይነት ያለዉ ነው። በዚህ የወንጀል ሕግ ጠቅላላ መርህ መሠረት  ማንኛውም ሰው አስገዳጅ ሁኔታን እንደ መከላከያ ማቅረብ የሚችለው አደጋዉን በሌላ መንገድ ማስወገድ የማይችል መሆኑን እና ከሚደርሰዉ አደጋ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ዘዴ የተጠቀመ መሆኑን ሲረጋገጥ ነው። 

ስለሆነም ይህ ሰው ወንጀሉን የፈፀመዉ ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት እና ከፍቃዱ ውጪ የፈፀመዉ ድርጊት መሆኑን ማረጋገጥ የሚጠይቅ ሲሆን ከዚህ አንጻር ድርጊቱን የፈፀመዉ መርማሪ ወይም ወኪሉም ከክስ ነፃ ለማድረግ በወንጀል ሕጉ እና በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1387/2017 ውስጥ የተቀመጡትን ቅድመ ሁኔታዎች በጋራ (Cumulatively) መሟላታቸዉን ማረጋገጥ ግዴታ ነው። ስለዚህ በማሻሻያ አዋጅ ቁጥር 1387/2017 የተመላከተው ድንጋጌ አንድ ሰዉ በዚህ ሁኔታ ዉስጥ ሆኖ በራሱ ወይም በሌላ ሰዉ መብት ላይ የሚደረስ አደጋ ለማዳን ወንጀል ከፈፀመ እንደማይቀጣ የተቀመጠ ሲሆን በዚህ አግባብ ወንጀሉን የፈጸመው ያለፍላጎቱና ተገዶ ስለመሆኑ ግን በማስረጃ የማረጋገጥ ግዴታ ይኖርበታል። ለዚህም በነባሩ አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 26 (3) ላይ የተመላከተው ድንጋጌን መመልከት በቂ ነው፡፡ በዚህ ድንጋጌ ስር በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን እንዲያስፈጽም የተመደበ ሰው (መርማሪ) ተጠርጣሪው ማንኛውንም ወንጀል እንዲፈጽም መገፋፋት የለበትም በሚል የሽፋን መርማሪው (Undercover Agent) ያለበትን ኃላፊነት በግልጽ አስቀምጧል፡፡

እዚህ ላይ በትኩረትና በጥንቃቄ መታየት ያለበት መሠረታዊ ጉዳይ በልዩ የምርመራ ዘዴ ላይ ተሳታፊ የሆነው ሰው ከአቅሙ በላይ በሆነና ያለፍላጎቱ ወይም ተገዶ ለሚፈጽመው ወንጀል እንዳይከሰስበት የሚደረግበት ሁኔታን መደንገግ ለምን አስፈለገ? የሚለውን ነው። ከላይ እንደተገለጸው በተደራጀው የወንጀል ቡድን ውስጥ ሰርገው በመግባት ምርመራውን የሚያከናውኑ መርማሪዎች ወይም ወኪሎቻቸው በወንጀል አድራጊው ቡድን ተጽእኖ ውስጥ በመውደቅ ወንጀል እንዲፈጽሙ ሊገደዱ ይችላሉ። ሆኖም በዚህ ምርመራ ውስጥ ተልእኮ ተቀብለው የሚገቡ መርማሪዎች ወይም ወኪሎቻቸው ከአቅማቸው በላይ በሆነና ያለፍላጎታቸው ለሚፈጽሙት ወንጀል እንዲጠየቁ የሚደረግ ከሆነ ፍትሐዊም ተገቢም አይሆንም፤ የሕጋዊነት መመዘኛዎችንም አያሟላም። 

ከላይ ከተገለጹት ምሳሌዎች ላይ ለመጨመር ያህል አንድ መርማሪ ፖሊስ ወይም ሕጋዊ ወኪሉ ተልዕኮ ተቀብሎ በአንድ ከባድ የሙስና ኔትዎርክ አባል በመሆን ጉቦ ከሚሰጡ ሰዎች ገንዘብ ተቀብሎ ለጉቦ ተቀባዮች ሊያቀባብል፣  ወይም በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ መርማሪ ፖሊስ ለዚህ ዓላማ በተደራጁ ወንጀለኞች ውስጥ ሰርጎ በመግባት ሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውሩን ሊፈጽም ይችላል። በዚህ አግባብ ስራውን የሚሰራ መርማሪ ፖሊስ ወይም ወኪሉ ዓላማው ወንጀል ለመሥራት ሳይሆን በሕቡዕ በተደራጀ ሁኔታ ወንጀሉን የሚፈጸሙ ዋነኛ ወንጀለኞችን (የወንጀል ድርጊቱ ዋና ተጠቃሚዎች፣ ትእዛዝ ሰጪዎች እና ውሳኔ አስተላላፊዎች) ለመለየት ነው። የተደራጁ የወንጀለኞች ቡድን ማለት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የገንዘብ ወይም የሌላ ቁሳዊ ጥቅም ለማግኘት ዓላማ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ከባድ ወንጀሎችን ለመፈጸም የተሰባሰቡና ተቀናጅተው የሚንቀሳቀሱ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎችን የያዘና ለተወሰነ ጊዜ የሚቆይ የተደራጀ ቡድን ነው።

በእነዚህ የተደራጁ ወንጀለኞች ቡድን ውስጥ ሰርጎ በመግባት እነዚህን የምርመራ ስልቶች ተግባራዊ የሚያደርጉ መርማሪዎች ወይም ሕጋዊ ወኪሎቻቸው ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን ወይም ንብረታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ሊሆን ስለሚችልና አደገኛ ውጤትም ይዘው ሊመጡ ስለሚችሉ አንደኛ እነዚህ ስልቶች በዘፈቀደ የሚከናወኑ ሳይሆን ሌሎች መደበኛ ስልቶችን መጠቀም የማይቻልበት ሁኔታ መኖሩን ሲረጋገጥ እና ፍርድ ቤት ይህን መሰል ምርመራ ለማድረግ ፈቃድ ሲሰጥ ነው (አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 26(2)። ሁለተኛ ምርመራውን ሲያከናውኑ ከቁጥጥራቸውና ከአቅማቸው በላይ በሆነ ምክንያት ሌላ ወንጀል ከፈጸሙ ይህ በማስረጃ እስከተረጋገጠ ድረስ ከወንጀል ክስ ነጻ እንዲሆኑ ማድረግ አስፈላጊ ነው። 

መገደድ ከተጠያቂነት የማያድንበት ልዩ ሁኔታ 

በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራ፣ ሰርጎ መግባት፣ በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍ፣ የይምሰል ግንኙነት መፍጠር የመሳሰሉ ልዩ የምርመራ ዘዴዎችን በመጠቀም ማስረጃ የሚሰበስብ ማንኛውም ሰው ተገዶም ቢሆን የሰው ሕይወት የማጥፋት እርምጃ ውስጥ መግባት የለበትም። አዋጁም የሌሎች ሰዎች ሕይወት ተገዶ ከሚያጠፋ በራሱ ላይ የሚፈጸምበትን አደጋ ቢቀበል የተሻለ አማራጭ አድርጎ የደነገገበት ሁኔታ በመኖሩ በማንኛውም ምክንያት የሰው ህይወት እንዲጠፋ ካደረገ በኋላ “ተገድጄ የግድያ ወንጀል ፈጽሚያለሁ፤” የሚል መከላከያ ማቅረብ የሚችልበት እድል አይኖርም።

እዚህ ላይ የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 75 ድንጋጌ ማጤን አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ያለምንም ልዩነት በሁሉም ሰዎች ላይ የሚፈጸም መርህ ሲሆን ይዘቱም እንደሚያስረዳው “የራስን ወይም የሌላ ሰውን መብት በቅርብ ከሚደርስ ከባድ ከሆነ አደጋ ለማዳን የተፈጸመ ድርጊት አደጋውን በሌላ መንገድ ማስወገድ የማይቻል ከሆነና አድራጊው ከሁኔታው ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ ዘዴዎችን የተጠቀመ ከሆነ አያስቀጣም”  በሚል የተቀመጠ ራስን የመከላከል መብት ነው። ይህ ድንጋጌ ለማንኛውም ሰው የሚሰራ እንደመሆኑ መጠን አንድ ሰው በግልጽ ሊገድለው ወይም ልጁን ለመግደል የጦር መሳሪያ ይዞ የመጣበትን ግለሰብ ከዚህ ሰው የወንጀል ድርጊት ማምለጥ የሚችልበት ሁኔታ በሌለበት አጋጣሚ ውስጥ ሆኖ ወንጀል ለመፈጸም የመጣበትን ሰው ቢገድለው በሕግ እንደማይቀጣ ነው የሚታወቀው፡፡ ይህንን ድንጋጌ አስቀድመን ካነሳነው እና የልዩ ምርመራ ስራን ከሚያከናውኑ መርማሪዎች ሥልጣን ጋር ብናመዛዝነው በወንጀል ሕግ ለሁሉም ሰው የተሰጠውን ያህል መብት ለመርማሪ አካላት እንዳልሰጠ ያሳያል። ምክንያቱም በልዩ ምርመራ ስራ የሚሳተፍ ሰው የግድያ ወንጀል ከፈፀመ ተጠያቂ እንደሚሆን በልዩ ሁኔታ የተቀመጠበት ምክንያት በዚህ አዋጅ ስር የተደነገጉት ወንጀሎች በአብዛኛው ካየናቸዉ በሽፋን ስር የሚደረግ ምርመራው ወይም በቁጥጥር ስር የሚደረግ ማስተላለፍን ሲፈጽም የግድያ ወንጀልን እንዲፈፅም የሚያስገደዱት ሁኔታዎች ውስጥ መርማሪው ወይም ወኪሉ የሚገባባት ሁኔታ ይኖራል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው። 

ማጠቃለያ

ሲጠቃለል ኢትዮጵያ እንደማንኛውም የተባበሩት መንግሥታት የጸረ-ሙስና ስምምነት (UNITED NATION CONVENTION AGAINST CORRUPTION) እና የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን ስምምነት (UNITED NATION CONVENTION AGAINST TRANSNATIONAL AND ORGANIZED CRIMES) ፈርማ እንዳጸደቀች ሀገር በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀል ለመቆጣጠር የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ በአዋጅ ቁጥር 780/2005 አዘጋጅታ በስራ ላይ ያዋለች መሆኑን ተከትሎ እንደማንኛውም የሕግ ማዕቀፍ ይህ አዋጅ በተለያየ ጊዜ በተለያዩ የሚመለከታቸው ዓለም-ዓቀፍና አህጉር አቀፍ ተቋማት ወቅቱን እየጠበቁ የሚሻሻሉ ዓለም-ዓቀፍ መስፈርቶችን ማካተቱን የሚገመግሙ እንዲሁም አፈጻጸሙም በተገቢው ደረጃ ላይ መገኘቱን እያረጋገጡ አጠቃላይ የሕግ ሥርዓቱ ያለበትን ደረጃ የሚያስቀምጡ መሆኑን ተከትሎ በዚህ አግባብ የተለያዩ የተቋማዊ አደረጃጀትና የሕግ ማዕቀፎች በሚፈለገው ደረጃ መገኘታቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት የፍትሕ ሚኒስቴር ከሚመለከታቸው (መንግሥታዊና ዓለም-ዓቀፍ ተቋማት) ጋር በመመካከር እንዲሁም ተገቢውን ጥናት በማድረግ አዋጅ ቁጥር 780/2005 እንዲሻሻል የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ በመቀጠልም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በርካታ ሕዝባዊ የውይይት መድረኮችን ተዘጋጅተው የተለያዩ ግብዓቶችን በማካተት አዋጁ ጸድቋል፡፡

በዚህ የማሻሻያ አዋጅ ስር የተካተቱ ብዙ ድንጋጌዎች ቢኖሩም በተለየ ሁኔታ የአንቀጽ 26 (4) ድንጋጌን በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ሚዲያዎችን እጅግ ውስን የሕግ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ፈርማ የሀገራችን የሕግ አካል ባደረገቻቸው ዓለም ዓቀፍ ስምምነቶችና የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት የተከለከለውን በወንጀል ምርመራ ሂደት የሚፈጸም የሃይል ተግባር የሚሽር አዋጅ ጸደቀ ተብሎ መቅረቡ በአንድ በኩል ከሙያዊ ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ ሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት ሲሆን ከዚህ ባለፈም በሕዝባችን ላይ አላስፈላጊ ብዥታና ስጋትን የሚፈጥር እኩይ ተግባር ነው፡፡