ወንጀልን ለመከላከል ከጠንካራ የፍትሕ ተቋማት በተጨማሪ የዜጎች ሁለንተናዊ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ ዜጎች የወንጀል ጥቆማ በመስጠት እና ምስክር በመሆን በቀጥታ ወይም ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለፍትሕ እርዳታ በመስጠት ይሳተፋሉ፡፡ ለፍትሕ እርዳት የሚሰጡ ምስክሮች ወይም ጠቋሚዎች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ደግሞ ህጉ ከለላ ይሰጣል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የወንጀል ጥቆማ ምንነት እና ህጉ የማስታወቅ ግዴታ የሚጥልባቸውን ወንጀሎች አለማሳወቅ የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነት እንዳስሳለን፡፡
የወንጀል ጥቆማ ምንነት እና ኃላፊነት
የወንጀል ጥቆማ ማለት አንድ ወንጀል ሲፈፀም ያየ ወይም ያላየም ቢሆንም ስለወንጀል መፈፀም መረጃ ያለው ሰው በአካል ቀርቦ ወይም ጠቋሚው ማንነቱን መግለፅ ካልፈለገ በተለያዩ ዘዴዎች ወንጀል መፈፀሙን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ መሆኑን ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀጽ 11 እና 12 ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡
ዜጎች እንደ ዜጋ ሀገራቸው ሰላም እንድትሆነ ወንጀልን የማሳወቅ የዜግነት ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም ህጉ የማስታወቅ ግዴታ የሚጥልባቸው የወንጀል አይነቶች አሉ፡፡ አለብነት የወንጀል ሕግ አንቀጽ 254፣ 335 እና 443 ወንጀልን የማስታወቅ ግዴታ የሚጥሉ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡
በአንፃሩ በግል አቤቱታ የሚቀርቡ ቀላል ወንጀሎች በግለሰቡ አቤቱታ ወይም ጥቆማ የሚቀርቡ በመሆኑ ሌሎች ሰዎች እነዚህን ወንጀሎች የመጠቆም ግልፅ የሆነ ግዴታ አልተጣለባቸውም፡፡ ይሁን እንጂ በምስክርነት ሲጠራ ቀርቦ የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ በ1996 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ሕግ አንቀጽ 212 መሠረት ወንጀሉ በግል አቤቱታ አቅራቢነት ብቻ የሚያስቀጣ መሆኑ በወንጀል ህጉ በግልፅ የተደነገገ እንደሆነ ተበዳዩ ወይም ሕጋዊ ወኪሉ የግል አቤቱታ ካላቀረበ በቀር የወንጀል ክስ ማቅረብ አይቻልም፡፡
የወንጀል ድርጊቶቹ ስለመፈፀማቸው የሚያውቅ ሰው ለባለስልጣናት ቢያሳውቅም ወንጀሉ የተፈፀመበት ሰው የግል አቤቱታ ያላቀረበ እንደሆነ የወንጀል ምርመራ ሂደት አይጀመርም (የወንጀል መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 13)፡፡ ምርመራ ከተጀመረ በኋላም ቢሆንም እንኳን ተበዳዩ ክሱን ካልፈለገ ምርመራው ይቋረጣል፡፡ ክስ ቀርቦ ጉዳዩ ፍርድ ቤት ከደረሰም በኋላም ቢሆን የግል ተበዳይ ክሱ እንዲነሳ የማመለከት መብት አለው፡፡ ስለሆነም በግል አቤቱታ የሚቀርቡ ጉዳዮች ተበዳዩ የወንጀል ድርጊት ወይም ወንጀል አድራጊውን ካወቀበት ቀን ጀምሮ እስከ 3 ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ለሕግ አስከባሪ አካላት ማቅረብ ይኖርበታል፡፡ ያለበቂ ምክንያት የዘገየ አቤቱታ ተቀባይነት አይኖረውም፡
ወንጀልን አለመሳወቅ ስለሚያስከትለው የሕግ ተጠያቂነት
አንድ የወንጀል ክስ ፍርድ ቤት ቀርቦ ከመሰማቱ በፊት በርከት ያሉ ሂደቶችን ማለፍ ይኖርበታል፡፡ የመጀመሪያ ሂደት ለወንጀል ምርመራ መነሻ የሚሆን ጥቆማ ይቀርባል፡፡ በሀገራችን በወንጀል ሕግም ሆነ በሌሎች አዋጆች የወንጀል ጥቆማ ማቅረብ ግዴታ የሚጥሉ ድንጋጌዎች ያሉ ሲሆን ይህን ኃላፊነት አለመወጣት የወንጀል ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ተደንግጓል፡፡
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 254 መሠረት በሀገሪቱ ሕገ መንግስታዊ ስርዓት፣ የፖለቲካና ግዛት ሉዓላዊነት፣ የውስጥና የውጭ ደኅንነት ላይ የተፈፀመ/ሊፈፀም የተሞከረ ወይም ወንጀሉን ለመፈፀም የመሰናዳት ተግባር መከናወኑን እያወቅ ማንም ሰው ለሕግ አካል ያላሳወቀ ከሆነ ከ5 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ሲሆን ወንጀሉ የተፈፀመው የሀገሪቱ የውስጥ ወይም የውጭ ደኅንነት በአስጊ ሁኔታ ላይ እያለ ከሆነ ቅጣቱ ከ10 ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራት ይሆናል፡፡
በወንጀል ሕግ አንቀጽ 335 መሠረት በመከላከያ ሰራዊት እና ወታደራዊ ግዴታዎች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን አለማስታወቅ በቀላል እስራት፣ ነገሩ ከባድ ሲሆን ደግሞ ከ3 ዓመት በማበልጥ ፅኑ እስራት እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል፡፡
በተመሳይ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 443 መሠረት ማንም ሰው በቂ ምክንያት ሳይኖረው በሞት ወይም በዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ ወንጀል መፈፀሙን ወይም የወንጀለኛውን ማንነት እያወቀ ለሚመለከታቸው ባለስልጣኖች ሳያስታውቅ የቀረ እንደሆነ ወይም በሕግ ወይም በሙያው ደንቦች ለሕዝብ ደኅንነት ወይም ሰላምና ስርዓት ሲባል አንዳንድ ወንጀሎችን ወይም ከባድ ሁኔታዎችን ለሚመለከተው ባለስልጣናት የማስታወቅ ግዴታ እያለበት ግዴታውን ያልፈፀመ እንደሆነ ከ1,000 ሺ ብር በማይበልጥ መቀጮ ወይም ከስድስት ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡፡
ወንጀልን የማሳወቅ ግዴታን በወንጀል ህጉ ከተመለከቱ ድንጋጌዎች በተጨማሪ በተለያዩ አዋጆች ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ የጸረ ሙስና ልዩ የሥነ ሥርዓትና የማስረጃ ሕግ አዋጅ ቁ 434/97 በአዋጅ ቁጥር 882/07 እንደተሻሻለው አንቀጽ 46፣ በተሻሻላው የፌደራል ጸረ- ሙስና ኮሚሽን ማቋቋምያ(ማሻሻያ) አዋጅ ቁጥር 883/2007 አንቀጽ 26 እና 27(መሠረት ማንኛውም የመንግሥት መስሪያ ቤት፣ የመንግሥት ልማት ድርጅት ወይም ህዝባዊ ድርጅት ባለሥልጣን ወይም ሠራተኛ በሚሰራበት መስሪያ ቤት ወይም ድርጅት የሙስና ወንጀል ስለመፈፀሙ እያወቀ የሙስና ወንጀልን ለመመርመር ሥልጣን ላለው አካል ሳያሳውቅ የቀረ እንደሆነ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ቀላል እስራት እና እስከ ብር 10 ሺህ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡
የሽብር ወንጀልን ለመቆጣጠር እና ለመከላከል የወጣዉን አዋጅ ቁጥር 1176/12 አንቀጽ 15 የሽብር ወንጀሎች ውስጥ አንዱ ሲፈፀም፣ እየተፈፀመ ወይም የተፈፀመ መሆኑን እያወቀ ወይም የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም አግባብ ላለው ሕግ አስፈፃሚ አካል ያላስታወቀ ሰው ከ1 ዓመት እስከ 3 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀምጣል፡፡ ወንጀልን አለማስታወቁ ከባድ ሲሆን በተለይም መረጃው ቀድሞ ደርሶ ቢሆን የወንጀሉን መፈፀም መከላከል ወይም መቆጣጠር የሚቻል ዓይነት ሲሆን ቅጣቱ ከ 3 ዓመት እስከ 7 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል፡፡
በሰው የመነገድና ሰዎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ቁጥር 1178/2012 አንቀጽ 13 መሠረት በሰው መነገድና ሰውን በህገ ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን የሚመለከት መረጃ ያለው ማንኛውም ሰው ወንጀሉ እየተፈፀመ ወይም የተፈፀመ መሆኑን እያወቀ ወይም የወንጀል ፈፃሚውን ማንነት እያወቀ በቂ ምክንያት ሳይኖረው ወዲያውኑ ለፖሊስ ወይም አግባብ ላለው ሕግ አስፈፃሚ አካል ያላስታወቀ ወይም ሐሰተኛ መረጃ የሰጠ እንደሆነ ከ3 ወር በማይበልጥ ቀላል እስራት የሚስቀጣ ሲሆን ድርጊቱ ከባድ ከሆነ ደግሞ ቅጣቱ ከ 1 ዓመት እስከ 5 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ሊሆን እንደሚችል ተደንግጓል፡፡ ይህ ለአብነት የተጠቀሰ እንጂ በሌሎች የተለያዩ ህጎች ጥቆማ መስጠት ግዴታ እንደሆነ እና ኃላፊነትን እንደሚያስከትል መረዳት ያስፈልጋል፡፡
የወንጀል ጠቋሚዎች በሕግ የተሰጣቸው ከለላ የማግኘት መብት
የወንጀል ምስክነትና ጥቆማ የሰጠ ሰው ጥቆማ በመስጠቱ ወይም ምስክር በመሆኑ የሚደርስበት ስጋት የሚገጥመው ከሆነ የሕግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ አዋጅ ቁ 699/2003 ጥቆማ ማቅረብና ምስክርነት መስጠት ግዴታ መሆኑን አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን የወንጀል ምስክርነትና ጥቆማ የሰጠ ሰው የሕግ ጥበቃ የሚደረግለት መነሻ ቅጣቱ ከግምት ሳይገባ 10 ዓመት እና ከዛ በላይ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ለሚያስቀጡ ወንጀሎች ጥቆማ አቅርቦ ከሆነ ነው፡፡ ይህም የሆነበት መሠረታዊ ምክንያት ከባድ ወንጀል ፈፃሚዎች ላይ ጥቆማ ሲቀርብ ወንጀል ፈፃሚዎቹ ጥቃት የማድረስ ዓቅማቸው ሰፊ ከመሆኑ የተነሳ እንጂ የትኛውንም የወንጀል አይነት የጠቆመ ሰው የሕግ ከለላ አያገኝም ማለት አይደለም፡፡ የትኛውንም የወንጀል አይነት የጠቆመ ጠቋሚ ጥቃት የሚደርስባት ከሆነ ይህንኑ ለሕግ አካል አቅርቦ ተገቢውን ቅጣት እንዲሰጥበት የማድረግ መብት አለው፡፡
10 ዓመት እና ከዛ በላይ ፅኑ እስራት ወይም በሞት ለሚያስቀጡ ወንጀሎች ጥቆማ ያቀረበ ሰው የሚደረግለት ጥበቃ ወይም የሚያገኘው መብት የአካልና ንብረት ጥበቃ የማግኘት፣ መኖሪያ ስፍራ መቀየር፣ የራስ መጠበቂያ መሳሪያ የማግኘት፣ ተከሳሽ ወይም ተጠርጣሪ እንዳይደርስበት ትእዛዝ እንዲሰጥለት የማድረግ፣ ጥቆማ ስለመስጠቱም ሆነ በችሎት የምስክርነት ጊዜ ማንነቱ እንዳይገለጥ የማድረግ፣ በመጠቆሙ ምክንያት ለደረሰ ጉዳት ነፃ ህክምና የማግኘት እንዲሁም ሥራና ትምህርት እድል የማግኘት ወ.ዘ.ተ መብትን ያጠቃልላል፡፡
በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ጥቆማ በመስጠት የሚያደርገው ተሳትፎ ለወንጀል ፍትሕ አስተዳደር እጅግ አስፈላጊ ሲሆን የማስታወቅ ግዴታ የተጣለባቸውን ወንጀሎች ማሳወቅ ደግሞ በሕግ የተጣለ ግዴታ ነው፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ