የጥቅም ግጭት

ማውጫ

ይህን ጽሑፍ ያጋሩ

በሰዎች ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ መስተጋብራቸው ውስጥ የጥቅም ግጭቶች ይፈጠራሉ፡፡ ሰዎች መንግስታዊ በሆኑ ተቋማት፤ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም በግል ዘርፉ ተሰማርተው ይሰራሉ፡፡ ተቋማት የራሳቸዉ ሕግ ወይም መተዳደሪያ ደንብ ይኖራቸዋል፡፡

በተቋማት ማቋቋሚያ ህጎች ውስጥ የሰራተኞችን እና የአሰሪዎቸቸውን ሥልጣን እና ተግባር ይወስናሉ፡፡ ነገር ግን ተቋማት ዝርዝር በሆኑ መመሪያዎችና ደንቦቻቸው ውስጥ የሰራተኞችን እና ኃላፊዎችን መብትና ግዴታዎችን፤ የተፈቀዱ እና የተከለከሉ ተግባራትን ያስቀምጣሉ፡፡ መሠረታዊ ዓላማው ተጠያቂነትና ኃላፊነትን ለማስፈን ነው፡፡ የጥቅም ግጭት ኃላፊነትን ሊያስከትል የሚችል አንዱ መሠረታዊ ፍሬ ጉዳይ ነው፡፡ በተቋምና በሠራተኛዉ እንዲሁም በተቋምና በሃላፊዉ መካከል የጥቅም ግጭት ቢፈጠሩ በሕግ አግባብና የጥቅም ግጭት እንዳይፈጠር ሊደረጉ የሚገቡ ጥንቃቄዎች ለመዳሰስ ይሞከራል፡፡

የጥቅም ግጭት ጽንሰ ሀሳብ

ጥቅም ለሚለዉ ቃል ወጥ የሆነ ትርጉም ማስቀመጥ የሚያስቸግር ነው፡፡ በተለያዩ ህጎች ውስጥ ጥቅም የተለያየ ትርጉም ተቀምጦለታል፡፡ የጥቅም ግጭት ማለት አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ኃላፊ በስራ ተግባር እና ኃላፊነቱ ዉስጥ ከሕዝብ ወይም ከመንግሥት ፤ ከሀገር ጥቅም ይልቅ የግሉን፤ የቤተሰቡን፤ የራሱን ቡድን ጥቅም ማስቀደም ማለት ነዉ፡፡ በሌላ አነጋገር የመንግሥት ሠራተኛዉ ወይም ኃላፊዉ በስራ ኃላፊነት እና ዉሳኔ ሂደት ውስጥ ገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም ሲያገኝ በዚህ ምክንያት የስራ ኃላፊነቱን ተገቢ ባልሆነ ሁኔታ ሲመራ የጥቅም ግጭት ተከሰተ ይባላል፡፡ የጥቅም ግጭት ከወንጀል ተግባር ጋር ተያይዞ የሚታይበት የሕግ አግባብ አለ፡፡ በአንዳንድ ህጎች የጥቅም ግጭትን ከገንዘብ ጥቅም፣ መብት ከማግኘት እንዲሁም መሻሻልን እንደ ጥቅም የተወሰደበት አግባብ አለ፡፡

ለምሳሌ የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13 ጥቅም ማለት በገንዘብ ወይም በማናቸውም ዋጋ ባለው መያዣ ወይም በሌላ ንብረት ወይም በንብረት ላይ ያለን ጥቅም (መብት)፤ ማንኛውንም ሹመት፣ ቅጥር ወይም ውል፤ብድርን፣ ግዴታን ወይም ማናቸውንም ዕዳ በሙሉም ሆነ በከፊል መክፈልን፣ ማስቀረትን፣ ማወራረድን፣ ወይም ከእነዚህ ነገሮች ነፃ ማድረግን፤ ከተመሰረተ ወይም ካልተመሰረተ የአስተዳደር፣ የፍትሐብሔር ወይም የወንጀል ክስ ወይም ካስከተለው ወይም ከሚያስከትለው ማናቸውም ቅጣት ወይም የችሎታ ማጣት በማዳን ወይም ይህን በመሰለ ዘዴ የሚደረግን አገልግሎት ወይም ውለታ፤ ማናቸውንም መብት ወይም ግዴታ መፈጸምን ወይም ከመፈጸም መታቀብን፤ በገንዘብ የማይተመን ማናቸውንም ሌላ ጥቅም ወይም አገልግሎት በተመለከተ የሚገኝ እንደ ጥቅም ተደርጎ ተወስዷል፡፡ በዚህ መልኩ የተገኘ ጥቅም ከጥቅም ግጭትነቱ ባለፈ የወንጀል ኃላፊነትን ጭምር የሚያስከትል መሆኑ ተደንግጓል፡፡

ይሁን እንጂ የጥቅም ግጭት እንደየተቋማቱ ህጎች የሚለያይ ሲሆን በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ በአንድ ተቋም ስር የሚተዳደሩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የተሰጣቸውን ሥልጣንና ተግባር በመጣስ የሚያስተዳድሯቸውን ተቋም ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ወይም ሊያጋጭ የሚችል ተግባር ፈጽመዉ ሲገኙ የጥቅም ግጭት የሚፈጠር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድሩ ተቋማት የሰራተኞችን ጥቅም የሚጎዳ ተግባር ፈጸመዉ ሲገኙ የጥቅም ግጭት የሚፈጠርበት ሁኔታዎች አሉ፡፡

የጥቅም ግጭትን በአይነት ለመለየት አስቸጋሪ ቢሆንም በብዛት የሚከሰቱ የጥቅም ግጭቶች አራት ሲሆኑ እነዚህም የሚከተሉት ናቸዉ፡ የገንዘብ ጥቅም ፍለጋ ግጭት፤ የውጭ ስራ ጥቅም ግጭት፤ የቀረቤታ ስራ የጥቅም ግጭት እና የስጦታ የጥቅም ግጭት ናቸው፡፡

የገንዘብ ጥቅም ፍለጋ ግጭት፡- አንድ የመንግሥት ሠራተኛ ወይም ኃላፊ በተሰጠዉ ኃላፊነት አጋጣሚዎችን በመጠቀም ለግል የገንዘብ ማግኛ አድርጎ ሲገለገልበት ነዉ፡፡ በአንድ በኩል ከተሰጠዉ የስራ ኃላፊነት ውጭ የሚሰራ የውጭ ስራ ጥቅም ግጭት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ አንድ በመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰራ የመንግሥት ሠራተኛ በመንግሥት የስራ ሰዓት ከተሰጠዉ የስራ ኃላፊነት ውጪ በግሉ ሲሰራ ሲገኝ የጥቅም ግጭት ተፈጠረ የሚያስብል ነው፡፡

በሌላ በኩል የጥቅም ግጭት በመቀራረብና በመግባባት ይፈጠራል፡፡ አንድ የመንግሥት ሠራተኛ በመንግሥት መ/ቤት ውስጥ ሲሰራ ህጋዊ ባልሆነ መንገድ በመቀራረብ፣ በዝምድና፣ በትውዉቅ በመመስረት አገልግሎት ሲሰጥ ቢገኝ በቀጥታ የጥቅም ግጭት ይከሰታል፡፡

ስጦታ ወይም ግብዣ መቀበል ወይም መስጠት አንዱ የጥቅም ግጭት መንስኤ ነው ፡፡ የመንግሥትን የአሠራር ሂደት ሊያደናቅፍ የሚችል ስጦታ መስጠት እና መቀበልን የጥቅም ግጭት ዉስጥ ያስገባል፡፡ ይህ ሁኔታ ባለጉዳዩ በሂደት ለሚፈልገዉ ቀጥተኛም ይሁን ቀጥተኛ ላልሆነ አገልግሎት ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል የጥቅም ግጭት ይፈጥራል፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች የሚፈጸሙ የሰራተኞች ወይም የኃላፊዎች የጥቅም ተግባራት የድርጅቱን ወይም መስረያ ቤቱን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ሁኔታዎች ናቸው፡፡

በጉልህ ከሚታዩ የጥቅም ግጭቶች አንዱ በውክልና ሰጭና ተቀባይ መካከል በሚደረጉ የስራ ግንኙነት አንዱ ነዉ፡፡ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች፤ የግል ድርጅቶች እና ግለሰቦች ለስራ ወይም ለማናቸውም ጉዳይ ዉክልና ሊሰጡ ይችላሉ፡፡ በወካይ ተወካይ ሂደት ውስጥ የጥቅም ግጭቶች ሲፈጠሩ ይስተዋላል፡፡ ተወካይ በተሠጠው የውክልና ሥልጣን መሠረት የወካይን መብት የማስጠበቅና የራሱን የጥቅም በማስጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ነገር ግን ዉክልናውን መሠረት አድርጎ ከውሉ ውጭ የግል ጥቅሙን የሚያራምድ ከሆነ ከወካዩ ጥቅም አንጻር ግጭት ይፈጠራል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ወካዩ ውክልናውን ማንሳት ሙሉ ሥልጣን እንዳለው በፍትሐብሔር ሕግ ሥር ተደንግጎ ይገኛል ፡፡

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 2187(1) መሠረት ተወካይ ከ3ኛ ወገን ጋር በፈፀመው ውል ምክንያት የወካዩና የተወካዩ ጥቅሞች የሚጋጩ የሆኑ እንደሆነና ይህን ውል የፈረመው 3ኛ ወገን ይህን ሁኔታ ያወቀና ሊያውቀውም የሚገባ የሆነ እንደሆነ በወካዩ ጥያቄ መሠረት ይህ በተወካይና በ3ኛ ወገን መካከል የተፈፀመው ውል ሊፈርስ ይችላል፡፡ ወካዩም ከላይ የተገለፀውን አይነት የጥቅም ግጭት መፈጠሩን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ውሉን ለማፍረስ አሳቡን ማስታወቅ እንዳለበት የፍ/ብ/ህ/ቁ 2187(2) ይደነግጋል፡፡

የጥቅም ግጭት መኖሩ ተረጋግጦ 3ኛው ወገንም ይህን የጥቅም ግጭት ያወቀው መሆኑ ሲረጋገጥና ወካዩ የፍትሐብሔር/ሕግ/ቁ 2187(1) 2187(2) መሠረት የውል መፍረስ ሃሳቡን ቢያሳውቅ እና በቁጥር 2187(3) መሠረት 3ኛው ወገን የውሉን መቀጠል መፈለጉን ቢያሳውቅ የሁለቱንም ወገኖች ጥቅም ማስጠበቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2187(1) መሠረት ፍርድ ቤት ሁኔታዎችን ተመልክቶ ውሉን ሊያፈርሰው ይችላል፡፡ ስለሆነም ወካዩ ያጣቸውን ጥቅሞች በህጉ መሠረት የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ በሌሎች ህጎች የተጠቀሱ በርካታ የጥቅም ግጭት ሊፈጥሩ የሚችሉ ሁኔታዎች እንዳሉ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

የጥቅም ግጭትን ከግል ማህበራት አንጻር መመልከት ሌላ ጠቃሚ ጉዳይ ነዉ፡፡ ማህበራት በንግድ እና እንዱስትሪ ሚኒሰቴር በኩል አስፈላጊዉን መሰፈርት ሲያሟሉ ይቋቋማሉ (አዋጅ ቁጥር 985/2009)፡፡ ማህበራት የሚተዳደሩበት የራሳቸዉ መተዳደሪያ ሕግ /memorandum of association/ አላቸዉ፡፡ የማህበራት ዝርዝር የስራ አፈጻጸሞች በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 ተመላክቷል፡፡ ስለሆነም በአንቀጽ 217 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሠረት ሌሎች የማህበሩ ሸሪኮች ካልፈቀዱ በስተቀር ማንኛውም ኃላፊነቱ ያልተወሰነ ሸሪክ ማህበሩ የሚሠራቸውን ተመሳሳይ ሥራዎች ለራሱ ወይም ለሦስተኛ ወገን ለማከናወን እንዱሁም በአንድነትና በተናጠል ኃላፊ በሚያደርግ ተመሳሳይ ዓላማ ባለው ሌላ ማህበር ውስጥ አባል መሆን አይችልም ሲል ይደነግጋል፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት አባል በሆነበት ድርጅት ጋር የጥቅም መጋጨት እንዳይፈጠር ለመከላከል ዓላማ ነው፡፡

በአጠቃላይ ማንኛውም ሠራተኛ ከተጣለበት ኃላፊነት ውጭ ለግሉ፤ ለቤተሰቡ፤ ለወዳጁ እንዲሁም ለማናቸውም ዓላማ ሲባል ከተቋሙ ጥቅም የሚጋጭ ተግባር መፈጸም የተከለከለ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ይህ የጥቅም ግጭት ተቋሙን ከመጉዳት አልፎ ተገቢ ያልሆነ ጥቅም ወይም ብልጽግና አስገኝቶ ከሆነ አግባብ ባለዉ ሕግ የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡ ስለሆነም በየትኛዉም ደረጃ ያለ ሠራተኛ ለተቀጠረበት ተቋም ተገቢዉን አገልግሎት በመስጠት ሃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል፡፡ በተቋሙ ዉስጥ እያገለገለ/ች ከስራው/ዋ ጋር በተገናኘ ለሚፈጠር ጥቅም ራሱን በማግለል ታዓማኒነቱን ሊያረጋግጥ ይገባል፡፡

በንቃተ ሕግ፣ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ