መግቢያ
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳዮቻቸውን ራሳቸው መፈፀም የማይችሉባቸው ሁኔታዎች ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ለዚህም ሲባል ሌሎች ሰዎች ጉዳያቸውን እንደነሱ በመሆን እንዲፈፅሙላቸው ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ ይህም ሕጋዊ ጉዳዮችን መፈፀምን የሚመለከት ሲሆን ይህም በሕግ የሚያስከትለው እራሱን የቻለ ሕጋዊ ውጤት ስለሚኖረው ሥራዎችን የማከናወኑ ኃላፊነት ሕግን መሰረት ባደረገ ስምምነት ላይ የተመሰረት መሆን ይኖርበታል፡፡ በዚህ ፅሁፍ ስለ ውክልና ምንነት፣ የውክልና ዓይነቶች፣ የዉክልና አስፈላጊነት፣ በአሰጣጥ ሂደት ሊሟሉ የሚገቡ መስፈርቶች፣ የወካይ እና ተወካይ መብትና ግዴታዎች እንዲሁም ውክልና የሚሻርበትን ሁኔታ እንመለከታለን፡፡
የውክልና ምንነት
የሀገራችን የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2199 እንደሚደነግገው ውክልና ወካይ የተባለው ሰው ተወካይ ለተባለው ሰው እንደ እርሱ በመሆን አንድ ወይም ብዙ ሕጋዊ ሥራዎችን በእርሱ ስም እንዲያከናውን የሚሰጥ ስልጣን ነው፡፡ በዚህም ተወካዩ ልክ እንደወካዩ በመሆን የወካዩን ሥራዎች በወካዩ ስም ለማከናወን የሚደረግ ውል ነው፡፡ ተወካይ የሚያከናውነውን ተግባራት በወከለው ሰው ስም መሆን፣ ተወካይ ወካይ በሰጠው የስልጣን ወሰን ውስጥ ብቻ ተግባሩን ማከናወን የሚጠበቅበት መሆኑ፣ ተወካይ ወካዩ ከሰጠው ስልጣን ውጪ በመውጣት ለሚያከናውነው ተግባር ሀላፊነቱን የሚወስድ መሆኑ ተወካይ በውክልና የተሰጠውን ተግባር ሲያከናውን ሊመራባቸው የሚገቡ በሕጉ የተቀመጡ መርሆች ናቸው፡፡
የውክልና አስፈላጊነት እና አሰጣጥ ሂደት
አንድ ሰው አንዳንድ ተግባሮችን በራሱ ከማድረግ ይልቅ ሌላን ሰው በመወከል ተግባሮቹ እንዲከናወኑለት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የጊዜ ጥበት፣ የቦታ ርቀት ወይም የሁኔታዎች አለመመቻቸት፣ የእውቀት ወይም የክህሎት አለመኖርና የችሎታ ማነስ ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ ሌሎችም በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
የፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2200 ወካይ ለተወካይ የውክልና ስልጣኑን በቃል ወይም በዝምታ ሊሰጥ የሚችል ሲሆን ሕጉ የውክልና ስልጣኑ በተለያየ ፎርም መሰጠት አለበት በማለት የሚያዝ ከሆነ ግን ይህ መሟላት ይኖርበታል፡፡ ለምሳሌ ተወካዩ ከተወከለ በኋላ ሊያከናውናቸው የሚችሉት ጉዳዮች ወይም የሚዋዋላቸው ውሎች በፅሁፍ መሆን ግድ የሚላቸው ዓይነት ከሆኑ ከወዲሁ የሚደረገው የውክልና ውልም በፅሁፍ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡
ውክልናው በሕጋዊ ፎርም መሠረት መስጠት በሚያስፈልግበት ጊዜ የውክልና ሥልጣን ሥልጣን በተሰጠው አካል ሊረጋገጥና ሊመመዝገብ ይገባል። ውክልናውን የሚቀበለው ተወካይ መቀበሉን በግልፅ ወይም በዝምታ ሊፈጽም ይችላል፡፡ ውክልናውን መቀበል የማይፈልግ ከሆነ ደግሞ በግልፅ እንደማይቀበል በመግለፅ ከኃላፊነት እራሱን ማግለል ይችላል፡፡ ስለሆነም ተወካይ ውክልናውን የማይቀበል መሆኑን ከወዲሁ በግልጽ ካላስታወቀ በስተቀር የተወከለበት ነገር ከሚያካሂደው ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ጉዳይ መሆኑ በግለፅ የታወቀ ከሆነ ወይም ከሙያ ሥራው አመራር ጋር የሚመሳሰል ጉዳይ ከሆነ ወይም ይህንን የመሰለውን ጉዳይ ለመሥራት ፍቃደኛ ለመሆኑ በአደባባይ ገልጾ ሀሳብ በማቅረብ አስታውቆ እንደሆነ ውክልናውን እንደተቀበለ ይቆጠራል (የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2201)።
በመሠረቱ አንድ ሰው ለቀረበለት ውል ምላሸ ሳይሰጥ ዝም ቢል የቀረበለትን የውል ሀሳብ እንደተቀበለ እንደማያስቆጥርበት የፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1682 ይደነግጋል፡፡ ነገርግን የውክልና ጉዳይ እንደ ልዩ ሁኔታ የሚወሰድ ስለሆነ አንድ ሰው በቀረበለት የውክልና ውል ላይ ግልፅ የሆነ ያለመቀበል ሀሳብ እስካላቀረበ ድረስ ዝምታው የውክልናውን ውል እንደ ተቀበለ የሚያስቆጥርበት መሆኑን በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2201(2) ደንግጓል፡፡ ውክልናው የሚሰጠው ለብዙ ሰዎች ከሆነ ግን የውክልና ስልጣኑን ሁሉም ባንድነት መቀበላቸው ካልተረጋገጠ በቀር ውክልናው እንደፀና አይቆጠርም (የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2218/1)።
ውክልና ሊያሟላ የሚገባቸው መስፈርቶች
ውክልና ከልዩ የውል ህጎች ውስጥ አንዱ እንደ መሆኑ መጠን አንድ ህጋዊ ውል ሊያሟላቸው የሚገባውን በፍትሐብሔር ህጉ በአንቀፅ 1678 ስር የተቀመጡትን መስፈርቶች ሊያሟላ ይገባል፡፡ ይኸውም፡-
- ውል ለመዋዋል ችሎታ ያለው ሰው መሆን
- ጉድለት የሌለው ፈቃድ ወይም ስምምነት መኖር
- በቂ የሆነ እርግጠኝነት ያለው የሚቻል እና ህጋዊ የሆነ ጉዳይ መሆን
- የውል አፈፃፀም ፎርም በሕግ የታዘዘ ሆኖ እንደ ትዕዛዙ ባይፈፀም ፈራሽነት የሚያስከትል ሲሆን ሕግ በሚያዘው ልዩ ፎርም መሆን ናቸው፡፡
የውክልና ዓይነቶች
በአጠቃላይ ሁለት ዓይነት የውክልና አይነቶች አሉ፡፡ እነዚህም ጠቅላላ እና ልዩ ውክልና በመባል ይታወቃሉ።
- ጠቅላላ ውክልና
ጠቅላላ ውክልና ማለት በጠቅላላ አነጋገር የተደረገ ውክልና ሲሆን የአስተዳደር ሥራዎች ለመፈፀም ብቻ ለተወካዩ የሚሰጥ ውክልና ነው፡፡ ይህ ማለት ወካይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በዝርዝር ሳይገለፅ እንዲሁ በጠቅላላ አነጋገር ወክየዋለሁ የሚል ከሆነ ተወካዩ ከአስተዳደር ሥራዎች ውጭ የመሥራት ሥልጣን አይኖረውም ማለት ነው። በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2204 መሰረት
- የወካዩን ሀብት ማስቀመጥ፣ መጠበቅ
- ከሶስት ዓመት ለማያልፍ ዘመን ማከራየት
- በብድር የተሰጠን ሀብት መሰብሰብ
- ሰብሎችን መሸጥ
- ከሀብቱ የሚመጣውን ገቢ ተቀብሎ ማስቀመጥ
- ለተከፈሉ ዕዳዎች ደረሰኝ መሥጠት
- ለሽያጭ የተመደቡ የንግድ እቃዎችን ወይም ይበላሻሉ ተብለው የሚታሰቡ ነገሮችን መሽጥ የአስተዳደር ሥራዎች ናቸው፡፡
በመሆኑም በጠቅላላ ውክልና የውክልና ሥልጣን የተሰጠው ተወካይ ከላይ ከተዘረዘሩት ሥራዎች ውጭ የመሥራት ወይንም የመከወን ሥልጣን የለውም። በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በህብረተሰቡ ዘንድ የተሳሳተ ግንዛቤ ይታያል፡፡ ይህም ስሙ ጠቅላላ ውክልና ስለሚል ብቻ ለተወካይ አጠቃላይ የወካዩን ተግባሮች የመከወን ሥልጣን የሰጠው አድርጐ የመረዳት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ወካዮች ሁሉንም ሥራዎችን መወከል ሲፈልጉ ጠቅላላ ውክልና ወይም ሙሉ ውክልና ብለው የውክልና ስልጣን የመስጠት ሁኔታዎች ያጋጥማሉ። ይሁንና ጠቅላላ ውክልና ግን ሰዎች በሚያስቡት ወይም በሚገነዘቡት መልኩ ሳይሆን ህጉ ባስቀመጠው መሠረት የአስተዳደር ሥራዎችን ብቻ የሚያካትት ነው።
2. ልዩ ውክልና
ይህ ውክልና ወካይ ለተወካይ ከአስተዳደር ሥራ ውጭ ያሉ ሥራዎችን በወኪሉ ለማሠራት የሚያስችለው የውክልና ዓይነት ነው (የፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2205(1))፡፡ ስለሆነም በልዩ ውክልና የውክልና ስልጣን የተሰጠው ተወካይ በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 2205(1) እና 2206(1) መሰረት ተለይተው በዝርዝር የተመለከቱ ጉዳዮችንና እንደ ጉዳዩ ዓይነትና እንደ ልማድ አሰራር ከጉዳዩ ጋር ተከታታይነትና ተመሣሣይነት ያላቸው ነገሮችን ማከናወን ይችላል፡፡ ከዚህ ባሻገር አንድ ተወካይ ልዩ የውክልና ሥልጣን ከሌለው በስተቀር ሊፈፅማቸው የማይችላቸው ተግባራት አሉ፡፡ እነሱም፡-
- የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ ወይም አስይዞ መበደር
- ካፒታሎችን በአንድ ማህበር ውስጥ ማስገባት
- የሀዋላ ሰነዶችን መፈረም (sign bill of exchange)
- ለመታረቅ ውል መግባት
- ስጦታ ማድረግ
- በአንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከርና የመሳሰሉ ተግባራት ናቸው፡፡
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅጽ 13 የሰበር መዝገብ ቁጥር 50985 በሰጠው ውሳኔ በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2205 መሠረት የሚሰጥ ልዩ ውክልና በይዘቱ በልዩ ውክልና የሚፈፀሙ እያንዳንዳቸውን ተግባሮች በግልጽ የሚመለከት መሆን ይገባዋል። ከዚህ አንጻር ስንመለከተው “በስማችን ውል እንዲዋዋል” በማለት የተሰጠ ውክልና በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2204 የተዘረዘሩትን የአስተዳደር ተግባራት ለመፈፀም የሚያስችሉትን ውሎች በወካዮች ስም ሊፈፅም እንደሚችል የሚያመለከት እንጂ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ ለመለወጥ የሚያስችለው ልዩ የውክልና ሥልጣን እንደተሰጠው ተደርጎ የሚተረጎምበት አግባብ የለም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የውክልና ሥልጣን የሚተረጎመው ሳይሰፋ በጠባቡ መሆን እንዳለበት በፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2181(3) የሚደነግገው ነው በማለት አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል።
የወካይ እና ተወካይ ግዴታዎች
- የተወካይ ግዴታዎች
የፍትሐብሔር ህጉ በቁጥር 2208 እና ተከታዮቹ መሰረት ተወካይ በርካታ ግዴታዎች አሉበት፡፡ በዋናነት ተወካይ ለወካይ በሚሰራበት ወቅት ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው እና በውክልና በተሰጠው አደራ ላይ ልክ አንድ የቤተሰብ አባት እንደሚያደርገው ሁሉ በትጋትና በጥንቃቄ መከወን ይጠበቅበታል፡፡ በዚህም ተወካዩ በሚሰራበት ወቅት ለወካዩ ጥቅም ማሰብ እና ወካይ በሰጠው የስልጣን ወሰን ውስጥ ብቻ ተግባሩን ማከናወን የሚጠበቅበት ሲሆን ወካዩ ሳያውቅ በወኪልነቱ ምክንያት ከሚሰራው ሥራ አንዳችም ጥቅም መውሰድ የለበትም፡፡ በተጨማሪም ተወካዩ ወካዩ በጠየቀው ጊዜ ሁሉ የሥራውን አካሄድ፣ መግለጫ እና ሂሳብ በየጊዜው ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ በውክልናው ምክንያት የሚያገኛቸውን መረጃዎችም የወካዩን ጥቅም በሚጎዳ መልኩ መጠቀም የለበትም፡፡
- የወካይ ግዴታዎች
ወካዩም ግዴታዎች እንዳሉበት ከፍትሐብሔር ህግ ቁጥር 2219 እና ተከታዮቹ መረዳት ይቻላል፡፡ በዋናነትም ወካዩ ለተወካዩ የድካም ዋጋ ለመክፈል ውል ገብቶ ከሆነ ወይም ተወካዩ በውክልና የፈፀመው በሙያ ውስጥ በተመለከተ የግል ሥራው ከሆነ ወካዩ ለተወካዩ የድካም ዋጋ መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ በተጨማሪም ተወካዩ የውክልናው ሥራ ማስኬጃ ወጪ መሸፈን የሚጠበቅበት ሲሆን ተወካዩ ለወካዩ ጥቅምና ለውክልና ሥራው መልካም አካሄድ ሲል በወኪልነቱ ከሚገባው የውል ግዴታ ነፃ ሊያወጣው ይገባል፡፡
የውክልና መሻር
ወካይ አስፈላጊ መስሎ ሲታየው የሰጠውን የውክልና ስልጣን መሻር እና ለተወካይ የሰጠውን የውክልና ውል እንዲመልስለት ሊያስገድደው ይችላል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ወካይ ተወካይ በእርሱ እና በ3ኛ ወገኖች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሰጠውን ውክልና በማንሳት ለሚመለከታቸው አካላት እና በውክልናው ምክንያት ሊጎዱ የሚችሉ ወገኖችን ስለውክልናው መሻር ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ የተሰጠው የውክልና ጊዜ ከማለቁ በፊት የውክልናው መሻር በተወካይ ላይ ኪሳራ አድርሶበት እንደሆነ ወካይ ተወካይ ላይ በውሉ መሻር ምክንያት ለደረሰበት ኪሳራ ካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት፡፡ ብዙ ወካዮች ለጋራ ጉዳያቸው የወከሉትን ተወካይ በቂ የሆነ ትክክለኛ ምክንያት ከሌለ በቀር ወካዮቹ በመላ ሳይስማሙበት አንዱ ወካይ ብቻውን ተወካዩን ሊሽረው አይችልም፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ ውክልና ጊዜን እና ገንዘብን ቆጥቦ ጉዳይን ከማስፈፀም አንፃር ትልቅ ጥቅም ያለው ሲሆን ውክልና በሚሰጥት ጊዜ በሕጉ ላይ የተቀመጡ መስፈርቶች ማሟላት እና ወካይም ሆነ ተወካይ መብትና ግዴታዎቻቸውን ጠንቅቀው ማወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡