የሽግግር ፍትሕ የሕጎች አርቃቂዎች ቡድን አባላት በሶማሌ ክልል ጅግጂጋ ከተማ በክልሉ የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን ባቀረበለት ግብዣ መሠረት የስራ ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ቡድኑ ጅግጂጋ ሲደርስ በሶማሌ ክልል የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን ኮሚሽነሮች እና ሌሎች የኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች አቀባበል ተደርጎለታል፡፡
የሕጎች አርቃቂ ቡድኑ ከኮሚሽኑ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረገው ውይይትም የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ መጽደቁን ተከትሎ የትግበራ ምዕራፉን ውጤታማነት ለማስጠበቅ የተከናወኑ ተግባራትን አስመልቶ ገለጻ ያቀረበ ሲሆን በሶማሌ ክልል የእውነት እና እርቅ ኮሚሽን በኩል ኮሚሽኑ ከተቋቋመ ጀምሮ ላለፉት 2 ዓመታት ሲያከናውናቸው ስለነበሩ ተግባራት ማብራሪያ ቀርቧል፡፡
ማብራሪዎቹን ተከትሎም የሽግግር ፍትሕ ትግበራን የማስተባበር፣ የመረጃ ልውውጥ እና በትግበራ ምእራፉ የፌዴራል እና የክልል መንግስታት ሚናን እንዲሁም በክልሉ እየተከናወኑ የሚገኙ የእውነት ማፈላለግ ስራዎች በፖሊሲው በተመላቱት መርሆዎች መሠረት የሚፈጸሙበትን ሁኔታ አስመልክቶ ጥልቅ ውይይት ተደርጓል፡፡