ሶስተኛ ቀኑን የያዘው የፌደራል አስተዳደር ሥነ-ሥርአት አዋጅ ቁጥር 1183/2012ን በተሻለ ለማስተግበር የሚያስችል ሥልጠና ለፌዴራል ተቋማት መካከለኛ እና ከፍተኛ አመራሮች በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
ነሐሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም በተጀመረው በዚህ ሥልጠና 94 የሚሆኑ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆኑ የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ሥነ-ልክ ኢንስቲትዩት፣ የኢትዮጵያ ተስማሚነት ምዘና ድርጅት፣ የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት፣ የነዳጅ እና ኤነርጂ ባለሥልጣን፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ተቋማት ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራረሮች ተሳትፈዋል፡፡
ሥልጠናውን የሰጡት በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ ወ/ት ሀወኒ ታደሰ ሲሆኑ የአዋጁን ዓላማ ለማሳካት አዋጁ የሚዳስሳቸው ጉዳዮች ላይ ግንዛቤ መፍጠር የማይተካ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በአዋጁ በተዳሰሱ ጉዳዮች ስለ መመሪያ አወጣጥ ሂደት፣ ስለ አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ፣ በውሳኔ ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎች ስለሚስተናገዱበት አግባብ እንዲሁም በአዋጁ የተቀመጡትን ግዴታዎች አለማክበር የሚያሰከትለውን ውጤትና የፍርድ ቤቶች ኃላፊነትና ሥልጣን ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ወ/ት ሀወኒ አክለውም የአዋጁ አጠቃላይ ፋይዳ ህገ መንግስቱ የተመሰረተበትን መርሆችና እውቅና የሰጣቸውን መብቶች በዝርዝር ወደ መሬት በማውረድ የህገ-መንግሥት የበላይነት የተረጋገጠበትና ብልሹ አሠራር የተወገደበት የመንግሥት አስተዳደር መፍጠር መሆኑን ግንዛቤ መውሰድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በቀረበው ገለጻ መሠረትም በሥልጠናው ተሳታፈዎች በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው በአዋጁ አጠቃላይ ዓላማ እና አተገባበር ላይ ከተስተዋሉ ክፍተቶች በመነሳት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ይህንንም ለማረጋገጥ የአዋጁ አፈፃፀም ላይ የተቋማቱ አመራሮች ያላቸውን ቁርጠኝነት አመላክተዋል፡፡
በንቅናቄው ቀሪ ቀናት በርካታ የመንግሥት ተቋማት በሥልጠናው ተደራሽ የሚደርጉ መሆኑንና በቀጣይም ማህበረሰቡን የማንቃት ዘመቻ እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡