በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሂደት ውስጥ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ተመላከተ

The Critical Role of Parliament Members in National Human Rights Protection Processes Highlighted

ይህ የተባለው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ሰብዓዊ መብቶች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር (OHCHR) እና ከጀርመን የልማት ድርጅት (GIZ)ጋር በመተባበር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ ም/ሰብሳቢዎች እና ከምክር ቤቱ ከተለያዩ የስራ ክፍሎች ለተወጣጡ የስራ ሀላፊዎች ባዘጋጀው የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና በሰጠበት ወቅት ነበር፡፡

የሥልጠና መድረኩ በዋናነት ትኩረቱን ያደረገው የሰብዓዊ መብት ሪፖርትና ሁሉን አቀፍ ወቅታዊ ግምገማ የኢትዮጵያ ተሳትፎ፤ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ምክረ-ሃሳብ መከታተያ የመረጃ ቋት አስፈላጊነት እና አጠቃቀም፣ በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በሚካሄዱ የሰብዓዊ መብቶች አጠባበቅ ሂደት ውስጥ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሚና እና እንዲሁም በነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ በተዘጋጁ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነበር፡፡

በሥልጠናው መድረክ ላይ ማብራሪያ ከቀረበባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ሁሉን አቀፍ ወቅታዊ ግምገማን የሚመለከት ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ ሀገር አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሪፖርቷን ለተባበሩት መንግስታት ያቀረበች ከመሆኑ ጋር ተያየዞ በአጠቃላይ 316 ምክረ ሀሳቦች ቀርበው ኢትዮጵያም 265 ምክረ ሀሳቦችን ሙሉ በሙሉ መቀበሏ ተመላክቷል፡፡

በተያያዘ የብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ምክረሀሳብ መከታተያ የመረጃ ቋት ትግበራን የተመለከተ ጉዳይ ቀርቧል፡፡ ይህ የሰብዓዊ መብቶች የመረጃ ቋት በተለያየ ጊዜ የሚሰጡ ምክረ ሀሳቦችን ተግባራዊ ለማድረግ እንዲሁም የተሟላ የሰብዓዊ መብት ሪፖርትን ለማዘጋጀት የሚያስችል ሲሆን፤ ብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች መከታተያ የመረጃ ቋት በተደራጀ መንገድ መዘጋጀቱ በቀጣይነት ተቋማት ከሰብዓዊ መብት ጋር በተያያዘ የሚያከናውኗቸውን ተግባራት ለማወቅ፣ ሪፖርቶችን በቀላሉ ለማዘጋጀት ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱን ጉዳይ ከዘላቂ የልማት ግቦች ጋር ለማያያዝ የሚያስችል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በሌላበኩል በመድረኩ ላይ በፍትሕ ሚኒስቴር አማካኝነት በዝግጅት ላይ የሚገኘው ነፃ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት አሰጣጥ ረቂቅ አዋጅ ማዕቀፍ ጠቅላላ ሀሳቦች ለተሳታፊዎች በማቅረብ የአዋጁን ይዘት የማስተዋወቅ ስራ ተሰርቷል፡፡

በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግ እና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በሥልጠና መድረኩ ማጠቃለያ ወቅት እንዳሉት ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው በዚህ የሥልጠና መድረክ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በተለይ ሰብዓዊ መብቶችን ለማስፈፃም የሚረዱ ህጎች እንዲወጡ ድጋፍ ከመስጠት፣ እንዲሁም ሌሎች አዳዲስ ህጎች ሲፀድቁ ወይም ነባር ህጎች ሲሻሻሉ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን ያካተቱ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማስቻል ይህ መሰሉ የጋራ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ እጅግ አሰፈላጊ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ ተግባራትን በተሻለ መንገድ ለማከናወን የጋራ መግባባት ተፈጥሮ የሥልጠና መድረኩ ተጠናቋል፡፡

Tagged Under: Capacity Building Human Rights Protection Legal Frameworks Parliament Members
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች