(ዜና ፓርላማ)፣ ታሕሳስ 28፣ 2015 ዓ.ም፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ እና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በወንጀል ስነ-ስርዓት ሕግ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
ቋሚ ኮሚቴው በሴቶች እና ሕፃናት እንዲሁም በሌሎች የወንጀል ሕግ ስነ-ስርዓት ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም፣ ከፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ነው ውይይት ያደረገው።
በውይይቱ ላይ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ብዛት ያላቸው የተለያዩ የማዳበሪያ እና የማጠናከሪያ ሐሳቦች ተንሸራሽረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከዚህ በፊት ሰፋፊ የሕዝብ መድረኮች የተደረጉ ቢሆንም ለየት ባለ ሁኔታ ከሴቶች፣ ሕፃናት እና አካል ጉዳተኞች ጋር በተያያዘ መወያየቱ በጣም አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል።
ረቂቅ አዋጁ እንዲፀድቅ 10 ዓመት የወሰደ ቢሆንም ምክር ቤቱ አዋጁን ማየት የጀመረው ጥር 2014 ዓ/ም እንደሆነ የተከበሩ ወ/ሮ እፀገነት ተናግረው ሕዝባችን እንዳይጎዳ እና እንዲረካ ጥራቱን ለማስጠበቅ ደጋግመን አይተነዋል ብለዋል።
ቀጣይም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አጠር ያለ መድረክ ሊኖር እንደሚገባ ሰብሳቢዋ አስረድተው ምክር ቤቱ ኃላፊነታችንን በአግባቡ እንድንወጣ ኃላፊነት ሰጥቶናል ሲሉ ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ኢሳ ቦሩ ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር የተነሱ ሀሳቦች ገንቢ እንደሆኑ ገልፀው፤ እንደኮሚቴ የተነሱ ሀሳቦች እንደግብዓት ተወስደው መታየት ያለባቸው በአግባቡ እና በትኩረት ይታያሉ ብለዋል።
ምክትል ሰብሳቢው አክለውም የወንጀል ስነ-ስርዓት ረቂቅ አዋጁን ጊዜ ወስደን ማየቱ የሚወጡ ህጎች ጥራት እንዲኖራቸው እና ረጅም ጊዜ እንዲያገለግሉ ታሳቢ ተደርጎ እንደሆነም በዝርዝር አስረድተዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ በሴቶች እና ሕፃናት ላይ ጾታዊ ጥቃት ሲፈፀም ማስረጃ ለማሰባሰብ ፖሊስ እና የህክምና ባለሙያዎች በአንድ መስኮት አገልግሎት የሚሰጡበት መንገድ በረቂቅ ህጉ መካተት እንዳለበት በስፋት ተነስቷል።
የወንጀል ስነ-ስርዓቱን መሻሻል አስፈላጊነት በፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ስነ ስርዐት እና ማስረጃ ሕግ ፕሮጀክት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ሀላፊ የሆኑት ወ/ሮ ትዕግስት መሀቤ በጥልቀት ማብራሪያ ሰጥተው ህጉን ለማሻሻልም 10 ዓመት እንደጨረሰ ገልፀዋል።
የስነ-ስርዓት ህጎች መብት እና ግዴታ የሚደነግጉ መሠረታዊ ህጎችን ዓላማና ግብ መምራት ሲሆን እነዚህ መሠረታዊ ህጎች ስራ ላይ የሚውሉበትን ሁኔታ የሚደነግጉ እንደሆኑም ወ/ሮ ትዕግስት አስገንዝበው፤ የወንጀል ስነ-ስርዓት ሕግ ራሱን የቻለ ሕግ ቢሆንም ዓላማው እና ግቡ በወንጀል ህጉ ላይ የተቀመጠውን ዓላማና ግብ ማስፈፀም ነው ብለዋል።
የኢፌዲሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት