በአ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የ6ወራት በህግ ጥናትና ማርቀቅ፤ በፍትሐብሄር ፍትሕ አስተዳደር ፤ በፌደራል ጠበቆች አስተዳደር፤ በሰብዓዊ መብቶች፤ በብሔራዊ ትብብር ጥምረት፤ በፌደራል ሕጎች ተፈፃሚነት፤ በወንጀል ሥነ-ሥርዓት ሕግ እና መከላለከል ፤ በይቅርታና ምህረት፤ በሕግ ጉዳዮች ዓለም ዓቀፍ ትብብር፤ የፌደራል ጠበቆች ቦርድን የተመለከቱ ዕቅድ አፈፃፀሞችን ክቡር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በተገኙበት ታህሳስ 28ቀን 2018 ዓ.ም ግምገማ ተካሂዷል::
ከህግ ጥናትና ማርቀቅ ጋር በተያያዘ በተለያዩ 7 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናቶች እንዲሁም የዳሰሳ ጥናቶች የተደረጉ ሲሆን፣ ለአብነት የፍትሐብሔር ፍትህ ፖሊሲ ዝግጅ፤ የኢኮኖሚ ነክ ድርጊቶች ከልክ በላይ ውንጀላ ዙሪያ፤ ከእስራት ውጭ ያሉ አማራጭ ቅጣቶች፤ የማረሚያ ቤቶች የታራሚዎች አያያዝና አገልግሎት አሰጣጥ የተመለከቱት ይገኙበታል፡፡ ከህግ ማርቀቅና ዕርማት አንፃር 8 ሕጎችን የማርቀቅ ስራ፤ 6 ሕጎችን በማርቀቅ ሂደት ደግሞ ለተቋማት ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፣ 102 ረቂቅ ሕጎች ላይ የማረም ስራ እንዲሁም 31 መመሪያዎች እንዲመዘገቡና ተደራሽ እንዲሆኑ ተደርጓል።
የፍታብሔር ፍትሕ አስተዳደርን በተመለከተ የመንግሥትና የህዝብ ፍትሐብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ አኳያ ተሰሩ ሰፊ ሥራዎች የቀረቡ ሲሆን፤በዚህም 22 ጉዳዮች ላይ የውል ዝግጅትና ምርመራ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን የያዙት የገንዘብ መጠን 193,284,994.37 ብር፣ 71,419,524 ዩሮ፣ 2,999,500,000 ዶላር እና 284,000,000 የጃፓን ዬን ነው፤ የተሰጠ የሕግ ምክር ብዛት 1867 ሲሆን የያዙት የገንዘብ መጠን 116,285,560 ዶላር እና 68,641,969.25 ብር ነው፤ የተደረጉ ድርድሮች 54 ሲሆኑ የያዙት የገንዘብ መጠን 831,059,317.86 ብር እና 19,599,140.44 ዶላር ነው፤ 258 ቀጥታ ክስ የቀረበ ሲሆን በጠቅላላ የያዙት የገንዘብ መጠን 6,385,332,087.1 ብር እና 2000 ዶላር እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ተጠርጣሪዎች እና በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች የስብአዊ መብት አያያዝ እና አጠባበቅ ጋር ተያይዞ በተደረጉ ጉብኝቶች የተስተዋሉ ችግሮች እንዲሁ የሪፖርቱ አካል ሲሆኑ፤ ለሃገራችን የሰብዓዊ መብቶችን በተመለከተ የተሰጡ ምክረ-ሃሳቦች ተፈፃሚነት በተመለከተ እንዲሁ የክትትል ሥራዎች መካሄዳቸው ተገልፁዋል፡፡ የንግድና ሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሃ-ግብር ዝግጅት ጋር ተያይዞ እንዲሁ የተለያዩ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮች መካሄዳቸው ተጠቁሟል ፡፡
ብሔራዊ ትብብር ጥምረት ሥራዎች ጋር በተያያዘም ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እንዲሁም መበደኛና ደህንነቱ የተጠበቀ ፍልሰትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ሥራዎች በተለይም የትብብር ጥምረቱን የማስተባበር፣ የመደገፍ እና የህግ ማስከበር፤ የድጋፍና መልሶ ማቋቋም ማዕቀፎችን የማጠናከር በተለይም ከመዳረሻ እና መተላለፊያ ሃገራት ጋር ስምምነት ከማድረግ አኳያ ሰፊ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ በዚህ ረገድም ሃገራችን ኢትዮጵያም የአፍሪካ ሕብረት የፍልሰት፣ ስደትና የሃገር ውስጥ መፈናቀል ኮሚቴ አባል በመሆን በቅርቡ መመረጧ ይታወሳል፡፡
የቀረቡ ሪፖርቶችን ተከትሎ ለቀረቡ ጥያቄና አስተያየቶች በሥራ ክፍል ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን፤ በመጨረሻም ክቡር ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ በቀጣይ መሻሻል በሚገባቸው እና ትኩረት ተደርገው ሊሰራባቸው በሚገቡ ጉዳዩች ላይ በሰጡት አቅጣጫ የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል።