በብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት አባላት ከፍልሰት ጋር በተያያዘ በሕግ የተጣለባቸውን ተግባርና ኃላፊነቶች በየተቋማት መደበኛ እቅድ፣ ምዘናና ሪፖርት ውስጥ የአካቶ መፈጸም (Mainstreaming) እና የተጠያቂነት ሥርዓት ላይ በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ላይ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም የጥምረቱ ከፍተኛ ኃላፊዎችና ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ ውይይት ተካሂዷል፡፡
የውይይት መድረኩን በንግግር የከፈቱት የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ኡመድ ኦጁሉ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ዜጎቻችንን ለተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ሞት የሚዳርግ፤ የሀገራችን ገጽታም የሚያበላሽና አንገት የሚያስደፉ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በአገራችን ይሄንን መደበኛ ያልሆነው ፍልሰት በመከላከል የዜጎችን መብት፣ ደኅንነትና ጥቅም በማስከበር ከሚደረግ መደበኛ ፍልሰት የሚገኘውን ጥቅም አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ የተለያዩ የሕግና የአደረጃጀት ማዕቀፎች ተዘርግተዋል ብለዋል፡፡
ከዚህም አንጻር ጉዳዩ ቅንጅታዊ ስራ የሚፈልግ ሀገራዊ ጉዳይ መሆኑን በማመን በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራና የሚመለከታቸውን የፌደራል ተቋማት፣ ክልሎችንና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማትን ያካተተ ብሔራዊ ምክር ቤት እንዲሁም በፌደራል ደረጃ ለምክር ቤቱ ተጠሪ የሆነ በፍትሕ ሚኒስቴር የሚመራ ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ተቋቁመዋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እንደ አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በአጠቃላይ በፍልሰት አስተዳደሩ በተለይም ወንጀሎቹን በመከላከልና በመቆጣጠር ሂደት ኃላፊነት የተሰጣቸው ተቋማት ተጠያቂነት ባለው ሁኔታ በየተቋሞቻቸው ዕቅዶች ውስጥ በአግባቡ አካቶ በመሥራት ረገድ ችግሮች እየተስተዋሉ ይገኛሉ፡፡
በዚሁ መነሻ ተቋማችን ፍትሕ ሚኒስቴር በትብብር ጥምረቱ ውስጥ የአካታችነትና የተጠያቂነት ሥርዓት ምን እንደሚመስል እና በዚህ ምክንያት እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶችን በሚመለከት ከGIZ-BMM ባገኘው ድጋፍ የዳሰሳ ጥናት አስጠንቷል ብለዋል፡፡ የዳሰሳ ጥናቱ የመጀመሪያ ሪፖርት ከተጠናቀቀ በኋላ ሁሉንም የጥምረቱን መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተወካዮችን ያሳተፈ መድረክ ተዘጋጅቶ ግብዓት በመሰብሰብ ሰነዱን የማደበር ስራ ተሰርቷል ሲሉ አክለዋል፡፡
የትብብር ጥምረቱ አባላት የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት ይህ መድረክም የጥናት ሪፖርቱን ለመጨረሻ ጊዜ በማዳበር ለማጽደቅና ቀጣይ የትግበራ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ ነው በማለት አውስተው ጥናቱ እንዲካሄድና የዛሬውን መድረክ ጨምሮ የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረኮቹ እንዲካሄዱ በማገዝ ድጋፍ ያደረገውን GIZ-BMMን ክልብ አመስግነዋል፡፡
የዳሰሳ ጥናት ሪፖርቱ በአጥኚ ባለሙያው አማካኝነት ቀርቦ በአማካሪ ሚኒስትር ዴኤታው፣ በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ክብርት ወ/ሮ ሁሪያ አሊ፣ እና በስራና ክህሎት ሚኒስተር ዴኤታ ክቡር አቶ ሰሎሞን ሶካ መሪነት ውይይት የተደረገበት ሲሆን በቀጣይ በዚህ መድረክ የተሠጡ ግብዓቶች ተካተው በዳሰሳው የተሰጡ ምክረ ሀሳቦች እንዲተገበሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል፡፡