በፍትሕ ሚኒስቴር “የሕግ ሚና ማኅበራዊ ትስስር በመፍጠር/በማጠናከር እና የሽግግር ፍትሕ( THE ROLE OF LAW IN SOCIAL COHESION AND TRANSATIONAL JUSTICE”) በሚል የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ የተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች እንዲሁም ዓቃብያነ ሕግ በተገኙበት በዛሬዉ እለት ሶስተኛዉ የፓናል ዉይይት ተካሂዷል፡፡
የፓናል ዉይይቱን መነሻ ጽሑፍ በፍትሕ ሚኒስቴር የሽግግር ፍትሕ እንዲሁም የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ሲኒየር አማካሪ፣ የሕግ ትምህርት ቤት መምህርና ዓለም ዓቀፍ ሕግ አጥኝ የሆኑት ዶክተር ታደሰ ካሳ አቅርበዋል።
የሕግ ማዕቀፍ ማኅበረሰብ እንዴት ይቀርፃል? የሕግ ማዕቀፉስ በማህበረሰቡ እንዴት ይቀረፃል?፣ በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ያሉ ፓለቲካዊና ማኅበራዊ እውነታዎች ፣ሕግ ለግጭት አስተዳደር፣ ለህብረተሰብ ክፍፍል መፈወስ እና ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ረገድ የሚያበረክተው አስተዋፆ የሚሉና ሌሎች ሀሳቦች በፅሁፉ ተዳሰዋል።
ከሽግግር ፍትሕ ጋር በተያያዘም የሽግግር ፍትሕ ምንነትን ጨምሮ የሽግግር ፍትሕ ስልቶች ያለፉትን ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶች በመቅረፅ፣ እርቅን በማጎልበት ብሎም የተገለሉ ወገኖች የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በማድረግ ረገድ የሚጫወቱት ሚና ምን እንደሚመስል በፓናል ውይይቱ ከተዳሰሱት ውስጥ ይገኙበታል።
በተጨማሪም ፍትሃዊ፣ የተረጋጋና የተቀናጀ ማኅበረሰብን በማፍራት ረገድ የሕግ አቅም ያለው ድርሻ ከፍተኛ መሆኑንና የማኅበራዊ ትስስርን ለማጠናከር እውነተኛ የሆነ ሀገራዊ ውይይት እና የፖለቲካ ሂደቶች አስፈላጊነትም ተመላክቷል።
በፓናል ውይይቱ የተለያዩ ሀሳቦች የተነሱ ሲሆን የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎችም በውይይቱ ሰፋ ያሉ ሀሳቦችን አንስተውይ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ቀጠናዊ ብዝሀነት እና የፍትሕ ሚኒስቴር ሚና እና ሕግ እና የወንጀል ሕግ ምጣኔ በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ሁለት የፓናል ዉይይቶች መካሄዳቸዉ የሚታወስ ሲሆን በቀጣይም መሰል የፓናል ዉይይቶች ወር በገባ በመጀመሪያ ሳምንት መካሄዳቸው የሚቀጥል መሆኑ ተጠቁሟል፡፡