ዐቃቤያነ ሕግ የአፈፃፀም አስተዳደር ስርዐት ወደ ስራ ሊገባ ነዉ

Public Prosecutors' Performance Management System to be Implemented

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የዐቃቢያነ ሕግ የምዘና ሥርዓትን በቴክኖሎጅ የተደገፈ የማድረግ ስራን ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስምምነት ወስዶ በጋራ ሲሰራ ቆይቶ በዛሬዉ እለት ይፋ አድርጓል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስን ጨምሮ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ የተቋም ግንባታና የሪፎርም ስራዎች ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን እና ሌሎች የፍትሕ ሚኒስቴር አመራሮች እንዲሁም በስራዉ የተሳተፉ የአየር መንገድ የስራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡

ዶክተር ጌዲዮን በመርሀ ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ዉስጥ ካሉ ተቋማት መካከል ለስኬት ተምሳሌት የሆነዉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዉጤት ካበቁት ምክንያቶች አንዱ ጠንካራ የስራ ባህልና ባለሙያዎቹን የሚያበረታታበትና የሚቆጣጠርበት ሥርዓት መሆኑን ገልጸዉ የፍትሕ ሚኒስቴርም ይህንን አሰራሩን እንደ ልምድ በመዉሰድ ከአየር መንገድ ጋር በጋራ በመተባበር ይህ ሲሰተም እንዲዘረጋ ማድረጉን አንስተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ዐቃቢያነ ሕግ በምን መልኩ መገምገምና መመዘን እንዳለባቸዉ የሚገልፅና ከዚህ በፊት የነበሩትን ክፍተቶች የሚሞላ ጥናት በማድረግ መመሪያ መዘጋጀቱን የገለፁት ሚኒስትሩ ለተቋሙ ስኬት ትልቁ ሀብት ባለሙያዎች መሆናቸዉን አስታዉሰዉ እነዚህ ባለሙያዎች ሲስተሙ በራሱ ለዉጥ እንደማያመጣ ተገንዝበዉና ዓላማዉን ደግፈዉ ያላቸዉን እዉቀት ስራ ላይ ማዋል እንደሚገባቸዉ አሳስበዋል፡፡

አያይዘዉም የተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ለስራዉ መሳካት ተምሳሌት በመሆን በቁርጠኝነትና በባለቤትነት ስሜት የተዘረጋዉን አሠራር ስራ ላይ እንዲያዉሉት አደራ ካሉ በኋላ በቀጣይ ሥልጠናዎች ተሰጥተው የተዘረጋዉ የአሠራር ሥርዓት በአዲሱ ዓመት ሙሉ በሙሉ ወደስራ የሚገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አክለውም ስራዉን ሲከታተሉና ሲመሩ ለነበሩት የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች፣በስራዉ ለተሳተፉ የአየር መንገድ እና የፍትሕ ሚኒስቴር ባለሙያዎች እንዲሁም ስራዉን በገንዘብ ለደገፈዉ ለዩኤንዲፒ /UNDP/ ድርጅት ምስጋናቸዉን አቅርበዋል፡፡

የተቋም ግንባታና የሪፎርም ስራዎች ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ኤርሚያስ የማነብርሃን በበኩላቸዉ የዐቃቢያነ ሕግ የክወና አስተዳደር ሥርዓት (PMS) መዘርጋቱ የሚኖረዉን መሠረታዊ ጥቅሞች ያብራሩ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ የግለሰብና የቡድን ግቦችን ከተቋሙ አጠቃላይ ስልታዊ ግብ ጋር በማስማማት የተቋሙን ተልዕኮ ለማሳካት እንደሚያግዝ፣ በምዘና ስርአቱም የባለሙያዎችን አፈፃፀም በተጨባጭና በቋሚነት ለመለካት እንደሚያስችልና ከዚህ በመነሳትም ጥሩ አፈፃጸም ያላቸዉን ለማበረታታት፣ክፍተት ያለባቸዉን ደግሞ ለመደገፍና የላቀ አፈፃፀም ያላቸዉን ለመሸለም ያስችላልም ብለዋል፡፡

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ የምዘና ሲስተሙ መዘርጋቱ እስካሁን ሲሰራባቸዉ የነበሩ የዐቃቢያነ ሕግ አፈፃፀም አሰራሮች ላይ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን እንደሚፈታ ያላቸዉን እምነት ገልፀዉ አጠቃቀሙን በሥልጠና በማዳበር በተገቢዉ መንገድ መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የመጡት የአየር መንገዱ ቺፍ ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር /CIO/ የሆኑት አቶ ጌትነት ታደሰ ስራዉን ለመሥራት ከፍትሕ ሚኒስቴር ጋር የአንድ ዓመት ስምምነት ወስደዉ ወደስራ መግባታቸዉን ገልጸው ይህ ሲስተም መዘርጋቱ በዋናነት በወረቀት የነበሩ የዕቅድና የትግበራ አሰራሮችን ዲጅታል በማድረግ በቀላሉ ሪፖርት ለማድረግ ከማገዙም በተጨማሪ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ግልፅ በሆነ ሁኔታ ግብረ-መልስ እንዲሰጣጡ የሚያስችል መሆኑንም አያይዘዉ ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም የበለፀገዉ Performance Management System ቴክኒካል የሆነዉን ክፍል በአየር መንገዱ የአይቲ ፕሮዳክት ማናጀር አቶ ኢሳያስ ግዛዉ አማካኝነት ገለጻ ተደርጎበታል፡፡

Tagged Under: airlines • appraisal • Capacity Building • digital • digital transformation • employee • ermias yemaneberhan • Ethiopian Airlines • fikadu tsegaye • gideon timotheos • government reform • Institutional Reform • Legal Reform • management • performance • performance appraisal • performance monitoring • Prosecutors • public • Public Prosecutors • reform • system • transformation • UNDP • workforce management
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች