በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ ከድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች ጋር የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ውጤታማነት ለማሳደግ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በድሬዳዋ ውይይት አድርገዋል፡፡
በውይይቱም ባለፉት ዓመታት በከተማው በጋራ በተከናወኑ የወንጀል ምርመራ፣ ክስና ክርክር ተግባራት ወንጀል ፈፃሚዎችን ተጠያቂ ከማድረግ ረገድ መልካም ውጤቶች የተገኙ መሆኑን እና ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ስራዎች የታዩ ጥንካሬዎችን አጠንክሮ ማስቀጠል፤ ውስንነቶችን ደግሞ በመቅረፍ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ተነስቷል፡፡
ባለፉት ዓመታት አፈፃፀሞችን በመዳሰስ የታዩ ክፍተቶችን ለማረም የጋራ የአሠራር ስርዓት መዘርጋት፤ የወንጀል መረጃ ስርዓት ማዘመን፤ የምርመራ ስራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማስደገፍ፤ የጋራ ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ስርዓት መዘርጋትና ቅንጅታዊ አሠራር ማጠናከር በውይይቱ መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በውይይቱ የፍትሕ ሚኒስቴር እና የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች ተገኝተዋል።