በሰው የመነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር በተመለከተ መረጃ መለዋወጥ የሚያስችል ብሔራዊ የመረጃና የጥሪ ማእከል 8797 በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት አስተባባሪነት በአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ድጋፍ በንፋስ ስልክ ላፍቶ የፍትሕ ሚኒስቴር ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ተገንብቶ በዛሬው እለት የማስጀመሪያ መርሀ ግብሩ ተካሂዷል።
በዋናነት የጥሪና የመረጃ ማዕከሉ ለተጎጂዎችና ለተጋላጮች እንዲሁም በአጠቃላይ ለማህበረሰቡ በሰው የመነገድና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን የተመለከቱ ጥቆማዎችን በማቅረብ የሕግ ማስከበር ሥራውን ውጤታማ የማድረግ ዓላማን የሰነቀ መሆኑን በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በማዕከሉ አገልግሎት ማስጀመሪያ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል።
አይይዘውም የጥሪ ማዕከሉ አገራዊ ተደራሽነት ያለው ሆኖ በተለያዩ ቋንቋዎች አገልግሎት የሚሰጥ ከመሆኑም በተጨማሪ እየተከናወኑ የሚገኙ አገራዊ የፍልሰት አስተዳደር ተግባራትን በእጅጉ የሚደግፍ ስትራቴጂክ መሳሪያ መሆኑንም አክለዋል።
በተጨማሪም ተጎጂዎችና በአጋላጭ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ከሚገኙበት አስከፊ ሁኔታ በመታደግ በአፋጣኝ ሊቀርቡላቸው የሚገቡ የጤና፣ የስነ-ልቡና፣ የሕግ፣ የመልሶ ማቋቋምና የክህሎት ድጋፎችን የሚያገኙበትን የመረጃ ሥርዓት በማሳለጥ ጠንካራ ቅብብሎሽ እንዲኖር በማድረግ ተቋማዊ ተደራሽነትን የሚያሰፋ ዘመናዊ መንገድ መሆኑን ያመላከቱት ሚኒስትር ዲኤታው፣ ከሁሉም በላይ በውጭ ሀገራት መደበኛ በሆነ አግባብ ለስራ መሰማራት የሚፈልጉ ዜጎች በመረጃና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ እንዲወስኑ ለማስቻል አስፈላጊ መረጃዎችን ከሚመለከታቸው ተቋማት እንዲያገኙ ለማድረግም ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
አክለውም የሆት ላይን አገልግሎቱን ማስጀመር ወሳኝ ዕርምጃ ቢሆንም ስራው በአግባቡ እንዲቀጥል ለማስቻል በግብዓትና በሰው ኃይል የበለጠ በማጠናከር ለወንጀል መከላከሉ ተጨማሪ አቅም እንዲሆን ማድረግና ደህንነቱ የተጠበቀ መደበኛ ፍልሰት እንዲሰፋ የራሱን አስተዋጽዖ እንዲያበረክት ለማድረግ በጋራና በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ግለፀዋል፡፡
የአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ማዳም አቢባቶ ዋኔ በበኩላቸው ዛሬ ስራውን የጀመረው ይህ ማዕከል ከመረጃ መለዋወጫነት በተጨማሪ የሕግ ድጋፍ፣የሰነ ልቦናና የጤና ድጋፍ ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሊያውቀውና ሊጠቀመው እንደሚገባ በመግለፅ ድርጅታቸው አይ.ኦ.ኤም በቀጣይም ከፍልሰት ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ በሰው መነገድና ሰዎችን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር እየተወሰዱ ስላሉ ዕርምጃዎች በተለይም የጥሪ ማዕከሉ አጠቃላይ ሂደትና በማዕከሉ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንዲሁም በቀጣይ ስለሚኖሩ አገልግሎቶች በፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን የጥሪ ማዕከሉ በአሁኑ ወቅት በአማርኛ፣በእንግሊዝኛ፣በአፋን ኦሮሞ እና በትግርኛ ቋንቋዎች አገልግሎት እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን በቀጣይም በሌሎች ቋንቋዎች አገልግሎቱን ለመስጠት እንደሚሰራ ተገልፆል።
በመጨረሻም የጥሪ ማዕከሉ የሚኖረው ጠቀሜታ፣ ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ መደረግ ስላለባቸው ተግባራትና መሰል የውይይት ጥያቄዎች የተነሱበትና ከተለያዩ ተቋማት የመጡ ተሳታፊዎች የተሳተፉበት የፓናል ውይይት ተካሂዶና የጥሪ ማእከሉ በይፋ ተመርቆ መርሃ ግብሩ ተጠናቋል።