የፍትሕ ሚኒስቴር ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ጋር በመተባበር ለተቋሙ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ከታህሳስ 18 እስከ ታህሳስ 20 ቀን 2017 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ሲያካሂድ የቆየው የሥልጠና መርሀ-ግብር ባዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡
ለሶስት ተከታታይ ቀናት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ ሲካሄድ የነበረው ይህ መድረክ በዛሬው ዕለት እንዲሁ ታራሚዎችን ወደ ህብረተሰቡ የመቀላቀል ሥርዓት ፅንሰ ሃሳቦች፣ ዓላማው፣ በትግበራ ወቅት ሊያጋጥሙ ስለሚችሉ ችግሮች፣ በጉዳዩ ላይ አለምዓቀፍ እና የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ምን ይመስላል እንዲሁም በሀገራችን በትግበራ ሂደቱ አሉታው ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ጉዳዮች ምን እንደሚመስል በዘርፉ የስራ ሃላፊ አማካኝነት ገለጻ ተደርጓል፡፡
በተያያዘም የአማራጭ ቅጣት አፈፃፀም የሕግ ማዕቀፍ እና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በተመለከተ በተለይም ከዓላማው እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን አስመልክቶ በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ አማካኝነት ጠለቅ ያለ ማብራሪያ ተሰቶባቸው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል እንዲሁ የኢትዮጵያን 4ኛው ዙር የሁሉንአቀፍ ወቅተታዊ ግምገማ የሰብዓዊ መብቶች ሀገራዊ ሪፖርት የማዘጋጅትና የማቅረብ ሂደትን በተመለከተ የሪፖርቱ ሰነድ በስራ ክፍሉ ሀላፊ አማካኝነት የቀረበ ሲሆን፣ ሪፖርቱ በዋናነት የስብአዊ መብቶች ሪፖርት የማቅረብ ግዴታ፣ የሪፖርቱ ምንነት እና ከሌሎች ሪፖርቶች ያለው መሠረታዊ ልዩነት፣ ለሃራችን የተሰጡ ምክረ- ሃሳቦች እንዲሁም ከሪፖርት ዝግጅቱ ጋር በተያያዘ ያሉ ተግዳሮቶች ላይ ዝርዝር ማብራሪያዎች ለተሳታፊዎች ቀርበው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ የሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ ትግበራ ጋር ተያይዞ ከፖሊሲ ዝግጅቱ ጀምሮ አሁን እሰከደረሰበት ምዕራፍ ድረሰ ስለነበረው ሂደት እንዲሁ በስራ ክፍሉ ሃላፊ አማካኝነት ገለፃ የተደረገ ሲሆን በተለይም ከሕዝብ ግንኙነት ስራዎች፣ ከመረጃ ተደራሽነት እንዲሁም ከግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የአቅም ግንባታ ስራዎች አንጻር ስለተከናወኑ ተግባራት እንዲሁም ለትግበራ ሂደቱ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር አንፃር እንዲሁም በጥቅሉ በቀጣይ ሊሰሩ በታቀዱ ተግባራት ላይ በመድረኩ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በመጨረሻም የፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን የመዝጊያ ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ በንግግራቸው ወቅት እንደገለፁት ለሶስት ተከታታይ ቀናት የዘለቀው መድረክ በዋናነት በሁለት ክፍሎች የተከፈለ ሲሆን የመጀመሪያው ለአመራሩ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮችን በማንሳት መረጃን መስጠት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሌሎች ተቋማት እንዲሁም በፍትሕ ሚኒስቴር የለሙ የቴክኖሎጂ ሲስተሞች አጠቃቀማችን እንደ ተቋም ምን ይመስላል የሚለውን ማሳየት እና በቀጣይም በሰፊው ተፈጻሚነታቸውን ለማረጋገጥ ይቻል ዘንድ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ግንዛቤ ለመስጠት እነደሆነ አውስተው፣ ይህም እውን እንዲሆን መድረኩን በማስተባበር እንዲሁም በመደገፍ ላገዙ የፍትሕ ሚኒስቴር የስራ ሀላፊዎች እንዲሁም አጋር አካላትን ማለትም ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራምን፣ የትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም ጀስቲስ ፎርኦል ፕሪዝን ፌሎሺፕ ኢትዮጵያን አመስግነው የሥልጠና መርሀ-ግብሩ ተጠናቋል፡፡