የፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን እቅድ የሶማሌ ክልል የ3ኛ አመት የስድስት ወራት አፈጻጸምን ጂግጂጋ ከተማ ገመገመ

Ministry of Justice Reviews Somali Region’s 6-Month Justice Sector Transformation Plan Implementation in Jigjiga

በፍትህ ሚኒስቴር የህግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ የተመራ ልዑክ በሶማሌ ክልል ያለውን የሦስተኛውን አመት የስድስት ወራት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አተገባበር ለመከታተል ጂግጂጋ ከተማ በመገኘት ከክልሉ ምክር ቤት የህግና ፍትሕ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ ከሚመለከታቸው የፍትሕ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

የፍትሕ ዘርፉን አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋ፣ ውጤታማ እና የኅብረተሰብ እርካታን በሚያሳድግ መልኩ በማሻሻል በዘርፉ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሶስት ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ፍኖተ ካርታ ከሐምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በፌዴራልና በሁሉም ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች እየተተገበረ ይገኛል። ዕቅዱ አስር የተለያዩ አምዶችን በመለየት ዝርዝር ዕቅድ በማውጣትና ለዚሁ ስራ የሚሆን ግብረኃይል በማቋቋም ሲተገበር የነበረ እና ዘንድሮ የመጨረሻ ዐመት ላይ የሚገኝ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም መሰረት ልዑክ ቡድኑ በሶማሌ ክልል ያለውን የሦስተኛውን አመት የስድስት ወራት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አተገባበር በተለይም ከመሰረተ ማኀበረሰብ የፍትሕ አገልግሎት፣ ከአስተዳደር ፍትሕ አስተዳዳር፣ ከፍትሐብሔር ፍትሕ አስተዳደር፣ ከወንጀል ፍትሕ አስተዳደር፣ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀሎችን ከመከላከልና መቆጣጠር፣ ምቹ የሥራ አካባቢን ከመፍጠር፣ ቅንጅታዊ አሰራርን ከማሳደግ እንዲሁም ከመረጃ አያያዝ እና ልውውጥ ሥርዓት አንጻር የተሰሩ ስራዎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በውይይቱም በበቂ ሁኔታ ለተፈፀሙ ተግባራት ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን ቀጣይ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በዚሁ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ቀሪ ስራዎች ላይ የድጋፍ እና የትብብር ጉዳዮች ተለይተዋል፡፡

በመጨረሻም ሚኒስቴር ዴኤታው እቅዱ ሊጠናቀቅ የስድስት ወራት ጊዜ ብቻ እንደቀረ በማውሳት ቀሪ ስራዎችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ የሚያስችሉ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡ ግምገማውን መጠናቀቅ ተከትሎ የልዑክ ቡድኑ በጂግጂጋ ከተማ የሚገኘውን ማረሚያ ቤት የመስክ ምልከታ በማድረግ ከታራሚዎችና አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

Tagged Under: ali appeal court ethiopia's justice sector ethiopian federal ministry of justice ethiopian justice sector formation Implementation jigjiga judiciary Justice Justice Sector Justice Sector Transformation Justice Sector Transformation Plan justice transformation plan ministry plan plan implementation region review sector somali Somali Region three-year justice sector transformation plan transformation transformation plan transformation plan implementation
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች