የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታ እና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ዶ/ር ኤርምያስ የማነብርሃን የተመራ የሱፕርቪዥን ግብረ ሃይል በሲዳማ ክልል የመጨረሻውን ዓመት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የ6ወራት አፈፃፀም ታህሳስ 24/2018 ዓ.ም የዘርፉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ገምግሟል፡፡
የፍትሕ ዘርፍ ለማሻሻል አስር የተለያዩ አምዶችን በመለየት፤ ድርጊት መረሃግብር በማዘጋጀትና ለዚሁ ስራ የሚሆን ግብረሃይል በማቋቋም በመተግበር ላይ ያለው የ3 ዓመት የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሊጠናቀቅ የወራት ዕድሜ ይቀሩታል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በሲዳማ ክልል የመሰረተ ማኀበረሰብ የፍትሕ አገልግሎት፤ የአስተዳደር ፍትሕ የህግ ማዕቀፎች ያሉበት ደረጃ፤የመንግስትና የህዝብን ፍትሐብሔራዊ ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ያሉትን በጎ ጅምሮች፤ የፍትሕ አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ለመደገፍ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን፤ የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር፤ ምቹ የሥራ አከባቢ ከመፍጠር አኳያ እንዲሁም መረጃ አያያዝ እና ልውውጥ ሥርዓትን በተመለከተ በ2018 ባለፉት 6ወራት ያለውን ዕቅድ አፈፃፀም ከአስሩ መሰረታዊ አምዶች አንፃር የተሰሩ ስራዎችን ግብረ ሃይሉ ገምግሟል፡፡
በግምገማውም የአፈፃፀሙን ጠንካራ ጎኖችና የተመዘገቡ ውጤቶችን ዕውቅና በመስጠት እና ደካማ ጎኖችን በመለየት በቀሪ ስድሰት ወራት የክንውን ጊዜ በክልሉ ትኩረት በሚሹና ርብርብ መደረግ ባለባቸው ሥራዎች ላይ በመወያየት ስምምነት ላይ መድረስ ተችሏል።
በመጨረሻም ግብረ ሃይሉ የሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ አገልግሎት አሰጣጥን፤ በሃዋሳ ከተማ ሪፈራል ሆስፒታል የሚገኘውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲሁም የክልሉን እና የከንቲባ ፅ/ቤት የደህንነት መቆጣጠሪያ ማዕከልን ጎብኝቷል፡፡