በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ስር ባሉ 12ቱም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ከ2015 የበጀት ዓመት የስራ ዕቅድ ውስጥ በግማሽ ዓመቱ አጠቃላይ ምርመራቸው ተጠናቆ ፖሊስ ዐቃቤ ሕግ ውሳኔ እንዲሰጥበት ከላካቸው 17,041 መዛግብት ውስጥ በ15,046 መዛግብት ላይ ዐቃቤ ሕግ የተለያዩ ውሳኔዎችን መስጠቱን በተቋሙ የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ጉዳዮች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ጌቱ ታደሰ ገለጹ፡፡
እንደ አቶ ጌቱ ገለጻ በግማሽ በጀት አመቱ ከባለፈው በጀት ዓመት የዞሩ መዛግብትን ጨምሮ በ12ቱም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ክርክር የተደረገባቸው መደበኛ የልዩ ልዩ ወንጀሎች መዛግብት ብዛት 19,534 መሆናቸውን አንስተው ከእነዚህ መዛግብት ውስጥ ፍርድ ቤት በ6,109 መዛግብት ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በ5,946 መዛግብት ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ የተሰጠ ሲሆን በ163 መዛግብት ላይ ደግሞ ተከሳሾች በነፃ እንደተሰናበቱ አንስተው አጥፊን የማስቀጣት ምጣኔውም 96.7 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎችን በሚመለከት በግማሽ በጀት አመቱ በ462 መዛግብት ላይ በፍርድ ቤት ክርክር ተደርጎ በ109 መዛግብት ላይ ውሳኔ የተሰጠ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም በ106 መዛግብት ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ማሰጠት መቻሉን እና በ3 መዛግብት ላይ ብቻ ተከሳሾችን በነፃ መሰናበታቸውን ዳይሬክተሩ አውስተው አፈፃፀሙም 96.9 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ከፍትሐብሔር አገልግሎት ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተም በግማሽ በጀት ዓመቱ አገልግሎት ፈልገው ለመጡ ከ798 በላይ ለሚሆኑ የገንዘብ አቅም ለሌላቸው እና ጠበቃ ቀጥረው የሕግ ምክር እያገኙ መከራከር ላልቻሉ ሴቶች፣ ሕፃናት፣ አረጋውያን እንዲሁም ሌሎች ግለሰቦች አቅመ ደካማ ዜጎች ከሚኖሩበት ቀበሌ የድህነት ማረጋገጫ ማስረጃ እንዲያመጡ ተደርጎ ጉዳያቸውን በሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሚገኙ ዐቃብያነ ሕግ እንዲይዙላቸው እና እንዲከታተሉላቸው መደረጉንም አቶ ጌቱ ተናግረዋል፡፡
የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች በተመለከተም በቀሪ የበጀት አመቱ ወራቶች በተከሳሽ እና ምስክር አለመቅረብ የሚቋረጡ መዛግብትን በተመለከተ የሚቀነስበትን ሂደት እንዲሁም የተቋረጡትን መዛግብቶች የማንቀሳቀስ ስራ እና ከምርመራ ስራዎች ጋር በተያያዘ ከፖሊስ ጋር በጋራ ዕቅድ አውጥቶ መተግበር እና ሌሎች ቀሪ በርካታ ተግባራት ይከናዎናሉ ብለዋል፡፡
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ከተማ በ10ሩ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በድሬድዋና በሀዋሳ ከተሞች ያሉትን ጨምሮ 12 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች እንዳሉት የሚታወቅ ነው፡፡