በኢ.ፌ.ዲ.ሪ.ፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤሕግ ዘርፍ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መከታተያ ዳይሬክቶሬት የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ የጠቅላይ ዐ/ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር አቶ ተስፋዬ ዳባ፤ የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እንዲሁም በፅህፈት ቤቶቹ በየደረጃው ያሉ የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተካሂዷል፡፡
በግምገማ መድረኩ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው የወንጀል ምርመራን አስመልክቶ በሙስና ፤ በኢኮኖሚ፤ በተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች፤ በልዩ ልዩ ወንጀሎች፤ በሴቶችና ሕፃናት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች በሚመለከት በአጠቃላይ ከቀረቡ 13,091 የምርመራ መዝገቦች ውስጥ በ12,978 መዛግብት ላይ ውሳኔ መሰጠቱ ተገልጿል።
የቀጥታ ክስና የይግባኝ ጉዳዮች ክርክርን በተመለከተ እንዲሁ በሁሉም ወንጀሎች የክርክር መዛግብት የመርታት ምጣኔ በአጠቃላይ ከነበሩ 17,000 መዛግብት 2,138 ውሳኔ የተሰጠባቸው ሲሆኑ፤ ከ20,420 ተከሳሾች ውስጥ 2,499ኙ ውሳኔ እንደተሰጠባቸው የቀረበው ሪፖርት ያስረዳል፡፡
በፍርድ ቤት ከሚሰጡ የገንዘብና የእስራት ቅጣት አስመልክቶ በአጠቃላይ መጠኑ ብር 1,712,250 የሆነ የገንዘብ መቀጮ በተከሳሾች ላይ የተወሰነባቸ ሲሆን መጠኑ ብር 1,161,610 መፈፀሙን ክትትል መደረጉ ተጠቅሷል።
በፍትሐ ብሔር ጉዳዮች የቀጥታ ክስ የመርታት ምጣኔን በተመለከተ የፍትሐብሔር የቀጥታ ክስ በክርክር ላይ ካሉ 140 የቀጥታ ክስ ውስጥ ፍርድ ቤት በ39 መዛግብት ላይ ውሳኔ የሰጠ ሲሆን በ39ም መዛግብት ላይ ዐቃቤ ሕግ የረታባቸው መሆኑ ተመላክቷል።
በተጨማሪም በሪፖርቱ የተጠርጣሪዎች ጉብኝት፣የዜጎች ቻርተር ትግበራ፣የቅሬታና አቤቱታ መስተንግዶ በተመለከተ እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችና መፍትሔ አቅጣጫዎች እና የቀጣይ የስራ ጊዜ ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ተዳሰው ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡