የማሕበረሰብ ዓቀፍ ፍትሕን በፌዴራልና በሁሉም ክልሎች ዉጤታማ ለማድረግ ”ወደ ተመጋጋቢነት፡ በኢትዮጵያ ባሕላዊና ዘመናዊ የፍትሕ ስርዓቶችን ማቀናጀት” በሚል መነሻ ሐሳብ የፌዴራልና የክልል የዳኝነትና የፍትህ አከላት አመራሮች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ሃገራዊ የፓናል ዉይይት መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ነዉ፡፡
በዚህ ወቅት ባሕላዊ የግጭት አፈታት ስርዓቶች ለዘመናት ማሕበረሰቡ በእለት ተእለት እንቅስቃሴዉ ሲጠቀምባቸዉ የቆዩና ለህብረተሰቡ ቅርብ የሆኑ ስርአቶች ከመሆናቸዉ በተጨማሪ ጊዜን ገንዘብንና ጉልበትን የሚቆጥቡ ስርዓቶች እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
በመሆኑም ለእነዚሀ ስርዓቶች እዉቅና በመስጠትና ከዘመናዊዉ የፍትሕ ስርዓት ጋር በማቀናጀት አጋዥ እንዲሆን ለማስቻል በሶስት ዓመቱ የፍትህ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዉስጥ በማካተትና እዉቅና እንዲያገኙ በማድረግ ባለፉት ዓመታት በርካታ ጉዳዮች በባሕላዊ ዳኝነት ስርዓት እዲፈቱ በማድረግ እስካሁን ባለዉ ሂደት ትልቅ ዉጤት መምጣቱ ተገልጿል፡፡
አገራዊ የፓናል ዉይይቱም ዓላማም ባሕላዊና ዘመናዊ የፍትሕ ስርዓቶችን አቀናጅቶ መሄድ፤የባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች ያሉበትን ደረጃና የተገኙ ዉጤቶችን ብሎም ተግዳሮቶቹ ምን እደሆኑ መለየት፤በባሕላዊዉና በዘመናዊዉ የፍትሕ ስርዓት መካከል ያሉ ግንኙነቶች ምን እንደሚመስሉ በመለየት እስካሁን ባለዉ ሂደት የታዩ ጉዳዮች ምን ያህል እንደሆኑ ማየትና የየክልሎቹን ተሞክሮ በመመልከት በግብዓትነት በመዉሰድ በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አገራዊ የፓናል ዉይይቱ ዛሬን ጨምሮ በነገዉ እለትም የሚቀጥል ሲሆን በዛሬዉ ዉሎ የመሠረተ ማሕበረሰብ ዓቀፍ የፍትሕ አገልግሎት አሁናዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ፤የኢትዮጵያን ባሕላዊና ዘመናዊ ፍትሕ በጋራ ለማስኬድ የሚመራበት ሕጋዊ መስተጋብር፤ባሕላዊና ዘመናዊ የፍትህ ስርዓት መስተጋብር በኦሮሚያ የሚሉና ተቋማዊና ቅንጅታዊ አሰራርን የሚመለከቱ ፅሁፎች ቀርበዉ ሰፋ ያለ ዉይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡
በነገዉ እለትም የሲዳማ፤የአማራ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች የባህላዊ የፍትሕ ስርዓቶች አፈፃፀምና ልምዶች ቀርበዉ ዉይይት የሚደረግባቸዉ ይሆናል፡፡
የፓናል ዉይይቱን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ከInstitue for security studies (ISS) እና ከአውሮፓ ሕብረት ጋር በጋራ በመሆን አዘጋጅቶታል፡፡