በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን (ዶ/ር) እንዲሁም በዘርፉ ስር በየደረጃው ያሉ የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት ጥር 05 /2018 ግምገማ ተካሂዷል።
ዘርፉ በ6 ወራት ለማከናወን በእቅድ የያዛቸውን በርካታ ተግባራት መካከል የተቋሙን የ5 አመት ስትራቴጂ እቅድ መሠረት በማድረግ አዲስ የስኬት መለኪያዎችን በመጠቀም በማሕበረሰብ ፍትሕ አገልግሎት ፤ በንቃተ ሕግ ሽፋንና ተደራሽነትን ፤የሲቪል ማህበረሰብ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ከማሳደግ፤ በተቋማዊ አቅም ግንባታ ፤ በስነ-ምግባር እና ፀረ ሙስና፤ ምቹ የሥራ ከባቢን ከመፍጠር፤በሴቶችና ህጻናት ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች፤ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ተደራሽነትን በተመለከተ የተከናወኑ ሥራዎች ሪፖት ቀርቧል፡፡
የተሻሻለ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጥን ከማጠናከር ጋር በተያያዘ ከተከናወኑ በርካታ ተግባራት መካከል የመሠረተ ማህበረሰብ የፍትሕ ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ በዚህም የባህላዊ የግጨት መፍቻ ስርዓትን የመገንባት ሂደት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በአማራ እና ሲዳማ ክልሎች ጋይድላየን የማዘጋጀት ሥራ የተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የንቃተ ሕግ ሽፋንና ተደራሽነትን ለማሳደግ ለ274 የሕግ ታራሚዎች የገጽ ለገጽ ሥልጠና፣ ለ3275 የተለያዩ ተቋማት ተወካዮችና የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም 1311 ዐቃብያነ ሕግ አመራሮችና ባለሙያዎች የንቃተ ሕግ ሥልጠና መሰጠቱ ተገልፁል፡፡
ተቋማዊ አቅም ግንባታን በማሳደግ ረገድም የተሻሻሉ አሰራሮችን በመከተል የተገልጋይ እርካታን የመለካት፤ የዐቃብያ ሕግ የስራ አፈጻጸም ምዘና እንዲሁም የአለባበስ ሥርዓት መመሪያ አፈጻጸም ክትትል የማድረግ፤ በስነ-ምግባር እና ፀረ-ሙስና አኳያም የቀረቡ ጥቆማዎችን ተቀብሎ የማጣራት እና የምርመራ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡
ምቹ የሥራ ከባቢን ከመፍጠር አንኳያም በዋናው መስሪያ ቤት የማስፋፊያ ግንባታ፣ የልደታ፣ ኮልፌ፣ እና ጉለሌ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የግንባታ ስራዎችን በወቅቱ ለማጠናቀቅ፤ የቁጥጥር እና ክትትል ስራዎች መከናወናቸውተ ጠቁሟል፡፡
በሴቶችና ህጻናት ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ጋር በተያያዘም በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች የመረጃ ቋት ማስጀመር፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና በህጻናት ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ላይ በአማካሪዎች በመታገዝ የሥልጠና ማንዋሎችን ማዘጋጀት መቻሉ ተወስቷል፡፡
በአጠቃላይ በዘርፉ ባለፉት 6ወራት በስራ ክፍሎች አማካኝነት የተከናወኑ ተግባራት ከተያዘው ስትራቴጂክ እቅድ አኳያ ሲገመገሙ የተሻለ ውጤት የተመዘገበባቸው እንደሆነ የተገለፀ ሲሆን፤ የግምገማ መድረኩም ሚኒስትር ዴኤታ ክቡር ኤርምያስ የማነብርሃን(ዶ/ር) በቀጣይ ትኩረት በማድረግ ሊሰራባቸው በሚገቡ ተግባራት ላይ በሰጡት አቅጣጫ ተጠናቋል፡፡