በሰው የመነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀል ጋር በተያያዘ እየተሰራ ስላለው የሕግ ማስከበር ተግባርና ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት ተካሄደ
መድረኩ ከመስከረም 13/2015 ዓ/ም ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተካሄደ ሲሆን በመድረኩ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ፣ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ አሸነፈች አበበን ጨምሮ በፌደራል ደረጃ ያሉ የወንጀል መከላከልና የሕግ ማስከበር የሥራ ቡድን አባል ተቋማት እንዲሁም የክልል ፍትሕ ቢሮዎችና የፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በአዋጅ ቁጥር 1178/2012 እንዲሁም በመመሪያ ቁጥር 563/13 መሠረት በሰው የመነገድ፣ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀል ጋር ተያይዞ ብሔራዊ የትብብር ጥምረት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር እንዲዋቀር የተደረገ ሲሆን በሥሩም የወንጀል መከላከልና የሕግ ማስከበር ሥራ ቡድንን በማድራጀት በተለይም የወንጀል መከላከልና የሕግ ማስከበር ስራ ውጤታማ እንዲሆን ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘም በ2014 በጀት ዓመት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተሰሩ የሕግ ማስከበር ስራዎች አጠቃላይ ሁኔታን በመገምገም ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ማስቀመጥ የሚገባ በመሆኑ በተለይም በሰው መነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀሎችን በተመለከተ ያሉ የሕግ፣ የፖሊሲ፣ የስትራቴጂ እና የትብብር ማዕቀፎች ዙሪያ የብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ ተወካይ በሆኑት አቶ ዮሐንስ ሲሳይ ገለጻ የተደረገ ሲሆን የአዲስ አበባና ድሬደዋ ከተማ አሰተዳደሮችን ጨምሮ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሶማሌ፣ የሲዳማና ቤኒሻጉል ጉሙዝ ክልሎች ከወንጀሉ ጋር ተያይዞ የሕግ ማስከበር ስራዎች አተገባበር ሪፖርት የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት ጀነራል ምክትል ደይሬክተር ጀነራል በሆኑት አቶ ሀብታሙ ኃይሌና በብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ በሆኑት አቶ ኢያሱ ቀለሜ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በተጨማሪም ከሳውዲ አረቢያ የሰደት ተመላሾችን ተቀብሎ ከማሰተናገድ አንጻር የታዩ ጠንካራ አፈጻጸሞችና ክፍተቶች አስመልቶ በሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የሕገ-ወጥ የሰዎቸ ዝውውር መከላከልና የተመላሽ ዜጎች ክትትልና ድጋፍ መሪ ስራ አስፈጻሚ በሆኑት አቶ ደረጄ ጠግይበሉ፣ የሱፐር ቪዠን ግኝት ሪፖርትና የአምስት ዓመት የፍልሰት ዕቅድ በብሔራዊ የትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ከፍተኛ ዐቃቤ ሕግ በሆኑት አቶ አቤል ገ/እግዚያብሄር እንዲሁም በሰው መነገድ፣ ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር እና ሰውን በሕገ-ወጥ መንገድ ለሥራ ወደ ውጭ ሀገር የመላክ ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በፌዴራል ደረጃ የተዘጋጀ ዓመታዊ ዕቅድ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዳይረክተር ጀነራል በሆነት አቶ ምሕረቱ ቁምላቸው ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት ተደርጓል፡፡በመጨረሻም በቀረቡ ሀሳቦችና በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን ቀጣይ የአተገባበር አቅጣጫ በማስቀመጥ መድረኩ በዛሬው ዕለት ተጠናቋል፡፡