የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሀ ግብር ጽ/ቤት ከኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት (CEHRO) ጋር በመተባበር የተዘጋጀና ከሁሉም ክልሎች የተወከሉ የሰብዓዊ መብት ፎካል ፐርሰኖች እና ባለሙያዎች የተሳተፉበት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና ለሁለት ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ተስቷል ፡፡
በሥልጠና በመድረኩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት በፍትሕ ሚኒስቴር ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት ድርጊት መርሀ ግብር ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ አወል ሱልጣን፣ ኢትዮጵያ ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር እንድታዘጋጅ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2019 በተባበሩት መንግስታት በተሰጠ ምክረ ሀሳብ መሠረት መንግሥት ለጉዳዩ ድጋፍ በመስጠቱ የዝግጅት ስራው መጀመሩን አስታውሰው፤ የሚመለከታቸው በፌደራል ደረጃ 22 አባላት ያሉት ቡድን ተቋቁሞ ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብቶች የድርጊት መርሀ ግብር የማዘጋጀት ስራ መከናወኑን አስረድተዋል፡፡
ሀላፊው አክለውም የክልል የፍትሕ አካላት በሥልጠና ግንዛቤ እንዲያገኙ የሚደረገው በቀጣይነት በሁሉም ክልሎች በድርጊት መርሀ ግብሩ መሠረት ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ከህብረተሰቡ ጋር የሚደረጉ የውይይት መድረኮችን ለማዘጋጀትና ለማስተባበር የባለድርሻነት ሚና እንዲኖራቸው ለማድረግና በቀጣይነት የሚከናወኑ የንግድና የሰብዓዊ መብት ስራዎችን በኃላፊነት ይዘው እንዲሰሩ ለማድረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር በመተባበር በተለይም ከብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር ዝግጅት ጋር ተያየዞ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ በማበርከት ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት (CEHRO) ኤክስኪቲቭ ዳሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ በበኩላቸው ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ስለሚደረጉ ጥረቶች እና ተያያዥ ስለሆኑ ጉዳዮች በማንሳት ገለፃ ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህም የቢዝነስ እና ሰብዓዊ መብት ጉዳየችን የሚመለከት የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ በዘርፉ ላይ ክፍተት እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅሰዋል፡፡
አያይዘውም በአሁኑ ወቅት በንግድ መስክ ከሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ጋር ተያየዞ ስማቸው የሚነሳ ተቋማትን ምርት በአሜሪካና አውሮፓ ገበያ ላይ መሸጥ የማይቻልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መምጣቱን በመጥቀስ ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር ዝግጅቱን ጨርሶ ስራ ላይ ሲውል ለቢዝነስ ድርጅቶቹ እንዲሁም ለሰራተኞች ብሎም ለህብረተሰቡ አመቺ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መሆኑን ማሳያዎችን በማንሳት አብራርተዋል፡፡
በመድረኩ የተባበሩት መንግስታት የቢዝነስ እና ሰብዓዊ መብት መመሪያዎች በሚመለከት THE DANISH INISTITUTE FOR HUMAN RIGHT የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት የምስራቅ አፍሪካ ተወካይ በሆኑት ዶ/ር ኦጆት ሚሩ አማካኝነት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2011 ጀምሮ ሁሉም አባል ሀገራት የተቀበሉትን የመንግስታቱ ድርጅት የንግድ እና የሰብዓዊ መብት ደንብና መመሪያዎች ቀርበው ገለፃ ተሰጥቶባቸዋል::
በቀጣይም ብሔራዊ የንግድና ሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሀ ግብር ለማዘጋጀት የተደረገውን የመነሻ ጥናት የሕግ አማካሪ በሆኑት ዶ/ር ኤሊያስ ኑር አማካኝነት ቀርቦ ስፋ ያለ ገለፃ ተሰጥቶበታል፡፡ በዚህም የንግድና ሰብዓዊ መብት ስለሚከተለው ሁሉም ተሳታፊ አካላት ማለትም መንግሥት፣ የንግድ ተቋሙ እንዲሁም ሠራተኛው እኩል ተጠቃሚ መሆን አለባቸው በሚለው መርህ ላይ ተመስርተው ሌሎች ተያያዥነት ያላቸውን ጉዳዩች በማንሳት ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻ ሥልጠናውን መሠረት አድርጎ በተደረገው ውይይት ላይ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፣ መድረኩ በንግድ እና ሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ እውቀትን ያገኙበትና በዘርፉ ላይ ወደ ፊት የሚኖራቸውን ስራ ለማከናወን የሚያስችል በቂ ግንዛቤን ያገኙበት መሆኑን በመግለፅ አስተያየታቸውን ሰጥተው የሥልጠና መድረኩ ተጠናቋል፡፡