በብሄራዊ የፍልሰት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ የመጨረሻው የግብዓት ማሰባሰቢያ ውይይት ተካሄደ

Final Consultation Forum Held on the Draft National Migration Policy

ከሚያዚያ 21-22 ቀን 2014 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ ጤናማነት በተሻለ ያረጋግጣል በሚል ታምኖበት በተዘጋጀው የብሔራዊ የፍልሰት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ላይ ከሚመለከታቸው ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የመጨረሻው የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ ተካሂዷል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለምአንተ አግደው እና በፖሊሲ ዝግጅት ውስጥ የተለያዩ ድጋፎችን ያደረጉ ተቋማት ተወካዮች ሲሆኑ አቶ አለምአንተ አግደው በንግግራቸው በመነሻነት ከአገር ወጥተው በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ቁጥር ከሶስት ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን በአለም ዐቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው የገለጹ ሲሆን ኢትዮጵያ የሰዎች ፍልሰት በስፋት ከሚመለከታቸው ሀገራት መካከል ግንባር ቀደም እንደመሆኗ መጠን ዜጎች መደበኛ ባልሆነ ፍልሰት የሚደርስባቸዉን ከፍተኛ የኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አካላዊ ጉዳትና ብዝበዛ ለመግታት ደህንነቱና ስርዓቱን የጠበቀ ዓለም ዓቀፍ መደበኛ ፍልሰት ቃልኪዳን ስምምነት (Global Compact on Safe Orderly and Regular Migration) ሰነድን ከመነሻው ጀምሮ እስከሚጸድቅ ድረስ ባለው ሂደት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስታደርግ እንደነበር እና ሰነዱንም ተቀብላ መፈረሟን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስትር ዴዔታው አክለውም መደበኛ ያልሆኑ የሰው ልጆችን እንቅስቃሴ ለመግታት በሰው መነገድ እና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀል ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችል አዋጅ በማውጣት ይህንኑ አዋጅ የሚያስተገብር ደንብ እና የተለያዩ መመሪያዎች አጸድቆ ወደ ተግባር እንዲገባ መደረጉን እና የፍልሰት መረጃ አስተዳደር የስራ ቡድን ተቋቁሟል ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ፍልሰት በባህሪው ዘርፈብዙ እና ከግዜው ጋር ተለዋዋጭ በመሆኑ በአንድ ተቋም ብቻ ሊከናወን የሚችል አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሁሉን አቀፍ የፍልሰት አስተዳደር በማን እና እንዴት ሊመራ ይገባዋል የሚለውን ጥያቄ የሚመልስ የፖሊሲ ውሳኔ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥትም የጉዳዩን አሳሳቢነት በመገንዘብ የፍልሰት ፖሊሲው እንዲዘጋጅ ወስኖ በተቋማችን ሰብሳቢነት የሚመራ የባለሙያዎች ኮሚቴ እንዲሁም የባለሙያዎች ኮሚቴን ስራ በበላይነት ሚከታተል ከፍተኛ አመራሮች የሚገኙበት ደግሞ አብይ ኮሚቴ በማዋቀር ፖሊሲውን በማዘጋጀት ለዛሬው ደረጃ እንዲበቃ አድርጓል ብለው በስተመጨረሻም ሰነዱን በማዘጋጀት ሂደት በቴክኒክ ኮሚቴ ውስጥ በአባልነት በመሳተፍ ፖሊሲውን ላዘጋጁ ባለሙያዎች እንዲሁም የሰነድ ዝግጅቱ እና የውይይት መድረኩ እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

መድረኩ በተቋማቱ ከፍተኛ አመራሮች እና ተወካዮች ንግግሮች መከፈቱን ተከትሎ በብሔራዊ የፍልሰት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነዱ የዝግጅት ሂደት ምን እንደሚመስል ገለጻ ያደረጉት የአለም አቀፉ የፍልሰት ድርጅት ተወካይ የሆኑት አቶ ከድረላህ ኢንድሪስ የፖሊሲ ሰነድ ዝግጅቱ ከመጀመሩ በፊት ከሰው ልጆች እንቅስቃሴ ጋር በተገናኘ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን በሚገባ ለመለየት የሚያስችል ጥናት የተደረገ መሆኑን ገልጸው እኝህን ችግሮች ለመቅረፍም ፖሊሲው ስለሚጫወተው ሚና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ጥልቅ የሆነ ውይይት በማድረግ መስማማት ላይ ተደርሶ የማርቀቅ ስራው ተጀምሮ ዛሬ ላይ የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል፡፡

ረቂቅ ሰነዱን በራስ አቅም ለማዘጋጀት በማሰብም ከባለድርሻ አካላት የተውጣጡ በዘርፉ የተሻለ ዕውቀት እና ልምድ ያላቸው ባለሙያዎችን በማዋቀር እንዲሁም ስራው በጥብቅ ስነ ምግባር እና ውጤታማ አካሄድ እንዲመራ ሚኒስትሮችን ያቀፈ የስቲሪንግ ኮሚቴ በማዋቀር ተገቢው አመራር በከፍተኛ ጥንቃቄ መካሄዱን አቶ ከድርላህ በንግግራቸው አንስተው አብራርቷል፡፡ ተወካዩ አክለውም የረቂቅ ሰነድ ዝግጅቱ ዐለም ዐቀፍ የጥራት ደረጃውን እንዲጠብቅ እና የሌሎች ሀገራትን በጎ ተሞክሮዎች ለመቅሰም እና በሰነዱ ለማካተት በማሰብም ሰፊ ልምድ ያላቸው የውጭ ባለሙያዎችን በአማካሪነት በመቅጠር ጭምር ድጋፍ መደረጉን አብራርቷል፡፡

በመቀጠልም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ፍትሕ ሚኒስቴር የብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ፈቲያ ሰይድ ብሔራዊ የፍልሰት ፖሊሲ ረቂቅ ሰነድ ዝግጅቱ ተረቆ ከተጠናቀቀ በኋላ በሰነዱ ላይ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ ተቋማትን በሙሉ በተለያዩ መድረኮች በማሳተፍ በውይይቶች የተነሱ ግብዓቶችን በመጠቀም ሰነዱን የማዳበር ስራ መሰራቱን አንስተው በፌዴራል እና ክልል ደረጃ ካሉ የባለድርሻ አካላት አመራሮች እና ተወካዮች፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅት ተወካዮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ኤምባሲዎች እና ከምሁራን እና አጥኚዎች ጋር መሰል ውይይቶች መካሄዳቸውን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ኃላፊዋ በመቀጠልም በረቂቅ ፖሊሲ ሰነዱ ውስጥ የተካተቱ መሠረታዊ ነጥቦችን በዝርዝር ለመድረኩ ተሳታፊዎች ያብራሩ ሲሆን ሰነዱ በውስጡ ከሰው ልጆች እንቅስቃሴ ጋር የሚገናኙ ጉዳዮችን በተገቢው በማጤን ረቂቅ ሰነዱ 6 ዋና ዋና መስኮች ወይም ጭብጦች ላይ እንዲያተኩር ተደርጎ መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ በረቂቅ ሰነዱ ውስጥ የተካተቱ መስኮችም ኢሚግሬሽን እና የድንበር አስተዳደር፣ የሥራ ስምሪት እና የሥራ ፍልሰት አስተዳደር፣ የፍልሰት ተጎጂዎች ጥበቃና መልሶ ማቋቋም፣ የዳያስፖራ ተሳትፎና ልማት፣ የፍልሰት መረጃ አስተዳደር እና አስገዳጅ ፍልሰትን የሚመለከቱ ጭብጦች መሆናቸውን ከወ/ሮ ፈቲያ ሰይድ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በስተመጨረሻም በፖሊሲ ሰነዱ ላይ ትኩረትን ይሻሉ በሚል በተለዩ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ አጭር ገለጻ ቀርቦ በተሳታፊዎች አስተያየት እንዲሰጥበት የተደረገ ሲሆን ለተነሱ ጥያቄዎችም አቅራቢዎች ምላሽ ሰጥተው የመጨረሻው የግብዓት ማሰባሰቢያ የውይይት መድረክ ተጠናቋል፡፡በዚህ የመጨረሻ መድረክ ላይ የተገኙ ግብዓቶችን ወደ ረቂቅ ሰነዱ በማካተት ለሚመለከተው አካል ልኮ የማጸደቅ ስራ እንደሚሰራ ከመድረኩ ተገልጿል፡፡

Tagged Under: act african charter on the rights and welfare of the child compact Consultation decree directive draft Forum global global compact for migration (gcm) judicial law legal legislation Migration Migration Policy National national consultation forum national migration policy order Policy proclamation ratio regular migration Regulation rule safe statute
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች