የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ዳይሬክቶሬት ከጂአይዜድ ኢትዮጵያ እና ከጂቡቲ ጋር በመተባበር ‘ድጋፍ ለመልካም አስተዳደር’ በተሰኘው መርሃ ግብር አማካኝነት የሰብዓዊ መብቶች መከታተያ ማብራሪያ መጽሃፍ በማዘጋጀት ለህትመት እንዲበቃ አድርጓል፡፡
ከሕገ-መንግሥቱ ጀምሮ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን ዓለምዓቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶችን እና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችን እና ሰነዶችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀው ይህ ማብራሪያ መጽሃፍ በሀገርዓቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ መብቶች ክትትል ዙሪያ ለሚከናወኑ ተግባራት ወጥ ሥርዓትን እንደሚገነባ ይጠበቃል፡፡
ሰነዱ ፍትሕ ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 943/2008 ከሰብዓዊ መብት አያያዝ እና አጠባበቅ ጋር በተያያዘ የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የራሱን ሚና እንደሚያበረክት የሚጠበቅ ሲሆን የብሔራዊ የሰብዓዊ መብቶች ድርጊት መርሃ ዓግብር ቀርጾ ተፈጻሚነቱን ስለመከታተል፣ በዓለምዓቀፍ እና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብቶች አካላት የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ስለመተግበር፣ በማቆያ እና ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ እስረኞችን መብቶች ስለመከታተል እና የመብት ጥሰቶች ሲከሰቱም ተከታትሎ ለማረም የሚያስችሉ ዝርዝር ስርዓቶችን እና አሰራሮችን በጥልቀት ይዳስሳል፡፡
የፍትሕ ሚኒስቴር የሰብዓዊ መብቶች ክትትል ማብራሪያ መጽሐፍ ዝግጅቱ መጠናቀቁ እና ለህትመት መብቃቱ በተበሰረበት ወቅት እንደተገለፀው መፅሐፉ በፌዴራል እና በክልል የሰብዓዊ መብቶችን የመከታተል ኃላፊነት ላለባቸው አካላት በሙሉ እንደሚሰራጭ እና ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራም እንደሚሰራ ተገልጿል፡፡