ኢትዮጵያ በቀጣይ በምታቀርበዉ 4ኛዉ እና 5ኛዉ የተጠቃለለ ሀገራዊ የኢኮኖሚ፤ ማኅበራዊ እና ባህላዊ መብቶች /ICESCR/ አፈጻጸም ወቅታዊ ረቂቅ ሪፖርት ላይ ግብአት ለማሰባሰብ የሚያስችል የዉይይት መድረክ ከተለያዩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ከተዉጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ሰኔ 6/2017 ዓ.ም በቢሸፍቱ ከተማ ተካሂዷል፡፡
ሀገራት የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን የሚቀበሉት እና የሚተግብሩት የዜጎቻቸዉን መብት ለማስከበር መሆኑን የገለጹት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሲቪል፤ የፖለቲካ ፤የኢኮኖሚ እና የማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጂብሪል፤ ሀገራችንም በተባበሩት መንግስታት ከጸደቁት 9ኝ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች 7ቱን ተቀብላና አጽድቃ መተግበሯ ለሰብዓዊ መብት መከበር ያላትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነዉ ብለዋል፡፡
ኮሚሽነሩ አክለዉም ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎችን ተቀብሎ መተግበር እንደተጠበቀ ሆኖ አፈጻጸሙንም ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነት አለብን፡፡ ዉይይቱም በአፈጻጸም ወቅት የነበረንን ስኬት እና የታዩ ክፍተቶችን በመለየት ለማሻሻል የሚያስችሉ ግብአቶችን ለማግኘት እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታን በመወከል በመድረኩ ንግግር ያደረጉት አቶ እያሱ ቀለሜ፤ ፍትሕ ሚኒስቴር በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት መሠረት ሀገራችን ያፀደቀቻቸውን ወይም የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍና አህጉራዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች አፈፃፀም አስመልክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር ሀገራዊ ሪፖርት በማዘጋጀት ለሚመለከታቸው አካላት ሲያቀርብ መቆየቱን ገልፀው፤ በዚህም መሠረት የፍትሕ ሚኒስቴር ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎችን በማካተት ይህን ረቂቅ አገራዊ ሪፖርት አዘጋጅቷል ብለዋል፡፡
አክለውም የአንድ ሀገር የሰብዓዊ መብቶች አፈጻፀም ክትትልና ሪፖርት ዝግጅት ሂደት ውጤታማነት የሚለካበት አንዱ መስፈርት በሂደቱ ባለው የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ መረጋገጥ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ የሪፖርቱ ግዴታ ምንጮች፤ ሪፖርቱን የማቅረብ ፋይዳ ፤ለማቅረብ የተከናወኑ ስራች፤ በሪፖርት ዝግጅቱ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮች እና ቀጣይ ስራዎችን በተመለከተ ሰፋ ያለ ገለፃ የተደረገ ሲሆን፤በመጨረሻም ተሳታፊዎቹ በረቂቅ ሪፖርቱ ላይ የቡድን ውይይት በማድግ ሪፖርቱን ለማዳበር የሚረዱ ሃሳቦችን ሰጥተዋል፡፡