የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ለማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሄደ

Discussion Held with Experts on Improving One-Stop Service Delivery Systems

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች፣ ሕፃናት እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ከጀስቲስ ፎር ኦል (justice for all) ጋር በመተባበር የሴቶችና ሕፃናት ጉዳት ማስተባበሪያ የአንድ ማዕከል የተገልጋዮች ቅሬታ አቀባበል እና በማዕከሉ አገልግሎት መስጫ መመዘኛ መስፈርቶች ዙሪያ በተዘጋጁ ሁለት ሰነዶች ላይ ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡

የውይይት መድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት በፍትሕ ሚኒስቴር የሴቶች፣ ሕፃናት እና ባለብዙ ዘርፍ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት ዳሬክተር ወ/ሮ ዳግማዊት አላምኔ የሴቶችና ሕፃናት ጉዳት ማስተባበሪያ ማዕከላት ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ ተከፍተው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ የሴቶችና ሕፃናትን ጥቃት መከላከልና ድጋፍ የመስጠት ስራው በተለያዩ ተቋማት ጥምረት የሚመራና በተለይ የሚደርሱት ጉዳቶች ውስብስብ በመሆናቸው እነዚህን ጉዳቶች ለመቀነስ የሚቻልበት የተበዳይን ፍላጎት መሠረት ያደረገ አገልግሎትን መስጠት በማስፈለጉ ሰነዶቹ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

አያይዘውም ማዕከላቱ የተቋቋሙለትን ዓላማ አሳክተዋል ለማለት፤ በተገልጋዮች ላይ ከሚደርሱት መንገላታቶች ጀምሮ፣ በመረጃ አያያዝ፣ የጤና እዲሁም የማኅበራዊ አገልግሎት ድጋፎች እንዲሰጧቸው ከማድረግ አንፃር የሚከናወኑትን ተግባራት መፈተሸና፤ የአሠራር መስፈርቶችን አዘጋጅቶ በዘርፉ አጠቃላይ አገልግሎቱን ማስተካከል ተገቢ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ የቅሬታ አቀራረብ በሚል የተዘጋጀ ሰነድ ያቀረቡት ከጤና ሚኒስቴር የሴቶችና ሕፃናት አካቶ ጉዳዮች ዳሬክቶሬት የተወከሉ ባለሙያ በተለያዩ የሐገሪቱ አካባቢዎች በመሄድ የዳሰሳ ጥናቶችን በማድረግ ከተለዩ ክፍተቶች አኳያ ተጎጂዎችን መሠረት ያደረገና መብታቸውን የጠበቀ የተቀናጀ አገልግሎትን መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የቅሬታ አፈታት አግባቦችን ያካተተ ሰነድ መዘጋጀቱን ገልፀዋል፡፡

የተቀናጀ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ ቅሬታ ሰነድ ለማዘጋጀት በተደረገው የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ ተጎጂዎች የተሟላ አገልግሎት አለማግኘት፣ ለተለያዩ ወጪዎች መዳረግ፣ ነባሩን የአሠራር ስርዓት ተከትሎ አገልግሎቱን አለመስጠጥ፣ የባለሙያዎች ስነ-ምግባር ጉድለት እንዲሁም የተቋማት ምቹ አለመሆን እና መሰል ጉዳዮች በአገልግሎቱ ላይ የሚታዩ የቅሬታ ምንጮች መሆናቸውን መገንዘብ መቻሉን አውስተው፤ በሌላ በኩል በቀጣዩ ጊዜ የማዕከቱን ገፅታ ለሁሉም ተጎጂዎች ምቹ እንዲሆኑ ከማድረግ ጀምሮ፣ የተጎጂዎችን መረጃ በአግባቡ አደራጅቶ ማስቀመጥ፣ የስነ ልቦና ባለሙያዎች በየማዕከላቱ እንዲመደቡ ማድረግ፣ በሕግና ፍትሕ አገልግሎቱ ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ማስተካከል፣ ህብረተሰቡን ስለቅሬታ አቀራረብ እንዲያውቅ ግንዛቤውን ማሳደግና እና መሰል ጉዳዮች ቅሬታን ለመቀነስ የሚያግዙ መፍትሄዎች ናቸው በሚል ተነስተዋል፡፡

የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ መመዘኛ መስፈርቶች በሚል ርዕስ ተዘጋጅቶ በቀረበው ሁለተኛ ሰነድ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ በአጠቃላይ 84 ያህል የሴቶችና ሕፃናት ጉዳት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከላት መኖራቸው የተጠቆመ ሲሆን፤ ማዕከላቱ ለተጎጂዎች የተሟላ አገልግሎት የመስጠት ዓላማቸውን እንዲያሳኩ ለማድረግ የሚጎድሏቸውን ነገሮች ለይቶ ማስተካከልና በሚቀመጥላቸው መስፈርት መሠረት እያስተካከሉ መሄድ የሚያስችሉ ጉዳዮችን የያዘ ሰነድ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡

በመጨረሻም በቀረቡት ሰነዶች ዙሪያ የመድረኩ ተሳታፊዎች በስራ ላይ ከሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች አንፃር ባደረጉት የቡድን ውይይት ያነሱት አስተያየትና ጥያቄዎች ለሰነዶቹ ማጠናከሪያነት በግብረ-መልስነት ተሰብስበዋል፡፡

Tagged Under: Justice Reform • One-Stop Service • Women and Children
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች

ተመሳሳይ ዜናዎች