የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በንቃተ ሕግ፤ ትምህርትና ሥልጠና ዳሬክቶሬት የተዘጋጀና ከፌደራል ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች እና ተጠሪ ተቋሞቻቸው እንዲሁም ከፍትሕ ሚኒስቴር ተጠሪ ተቋማት ለተወጣጡ መካከለኛ አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሞያዎች የሚሳተፉበትና ትኩረቱን በፌደራል የአስተዳደር ስነ ሰርዓት ሕግ ላይ ያደረገ ሥልጠና በመሰጠት ላይ ይገኛል፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የንቃተ ሕግ፤ ትምህርትና ሥልጠና ዳሬክቶሬት ዳሬክተር አቶ እንዳልካቸው ወርቁ እንዳሉት የፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 የመንግሥት አስተዳደር ላይ ስርዓትን የሚያበጅ፤ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር እንዲኖር የማድረግ ባህሪ ያለው ሲሆን፣ በየተቋማቱ የሚኖሩ ጉዳዮችን ለማስፈፀም የሚያገለግል እንዲሁም በመንግሥት አሠራር ላይ ገደብ የሚያስቀምጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ዳሬክተሩ አያይዘውም የፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ የህብረተሰቡን ቅሬታ ለመፍታት የሚያስችል ከመሆኑ በተጨማሪ የመንግሥትን አሠራር ግልፅነትና ተጠያቂነት የተሞላበት እንዲሆንና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን የሚያስችል ቢሆንም፣ በርካታ ተቋማት አዋጁን በሚጠበቀው ልክ እየተገበሩት አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የፌደራል ሥነ ሥርዓት ህጉ የተቋማትን የመመሪያ አወጣጥ ስርዓት፣ በተቋማት ውስጥ አስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ስርዓትን ለማበጀት እንዲሁም በተቋማት የአስተዳደር ውሳኔ እና መመሪያ አወጣጥ ላይ ፍርድ ቤቶች ክለሳ የሚያደርጉበትን ስርዓት ማኖር በሚሉ ሶስት አበይት ጉዳየች ላይ የሚያተኩር ሲሆን፣ በሌላም በኩል ይህ አዋጅ የህብረተሰቡን ጥቅም በማስጠበቅ ግልፀነትና ተጠያቂነትን የማስፈን እንዲሁም ሠራተኛው ሀላፊነቱን አውቆ በመሥራት እራሱን ከተጠያቂነት እንዲያወጣ የማድረግ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን ይታወቃል፡፡
በሁለት ቡድን ተከፍሎ ለሁለት ቀናት በሚቆየው ሥልጠና ላይ የፌደራል የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ ዓላማ፣ ተፈፃሚነት፣ መመሪያ ሲወጣ ለዚህ ጉዳይ ብቻ የተቋቋመ ችሎት በመመሪያዎች ላይ ክለሳ ስለሚያደርግበት ሁኔታ፤ በአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ህጉ መሠረት የተቋማት ተግባርና ኃላፊነት፣ ተጠሪነታቸው እንዲሁም ከሌሎች ተቋማት ጋር ያላቸው ግንኙነት የተለያዩ ተግባራትን ማን? መቼ? እንዴት? እና የት፣ ይፈፀማሉ በሚሉ ጉዳዮች ዙሪያ አተኮሮ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና የሚሰጥ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡