የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ ጀነራል ባለፉት 6 ወራት ውስጥ ከመሬት ወረራ፣ ከፍትህና ፀጥታ፣ ከፋይናንስ እንዲሁም ከገቢ ዘርፍ አኳያ በ197 መዝገቦች ላይ ክስ መመስረቱ ተገለጸ

Anti-Corruption Prosecutor General Filed Charges in 197 Cases Over the Past Six Months Involving Land Grabbing, Justice and Security, Finance, and Revenue Sectors

በኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ ጀነራል ባለፉት 6 ወራት ከባድና ወቅታዊ በሆኑ የሙስና ወንጀሎች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግና በምርመራ ስራዎች ላይ በመሳተፍ ከፍትሕ ዘርፍ ሙስና፣ ከመሬት ወረራ፣ ከባንኮች ብድር አስተዳደርና ገንዘብ ምዝበራ ጋር በተያያዘ በ197 መዝገቦች ላይ ክስ መመስረቱ የዳይሬክቶሬቱ ዳይሬክተር ጀነራል የሆኑት አቶ ገብሩ ገበየሁ ገለጹ፡፡

እንደ አቶ ገብሩ ገለጻ ከጉቦ፣ ሀሰተኛ ሰነዶችን ከማዘጋጀትና ከመጠቀም እንዲሁም በአደራ የተረከቡትን የመንግሥት ንብረት ለግል ጥቅም ከማዋል ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ ወንጀሎች ጭምር ክስ መመስረቱን እና ከ197 መዝገቦች ውስጥም በ28ቱ ላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ማስተላለፉን በ26ቱ መዝገቦች 44 ተከሳሾች ጥፋተኛ መባላቸውን በ2 መዝገቦችም 3 ተከሳሾች በነጻ መሰናበታቸውን ተገልጧል፡፡

የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል የፌደራል መንግስቱን የሙስና ወንጀል ህጎች ተፈፃሚነት በማረጋገጥ፣ ወንጀልን በመከላከል፣ የፍትሕ አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋና ፍትሀዊ በማድረግ፣የሕዝብ ዓመኔታን ያተረፈ የፍትሕ አገልግሎት በመስጠት የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 የተቋቋመው የቀድሞው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የአሁኑ የኢ.ፌ.ድ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ዋነኛ የስራ ክፍል ነው ሲሉም የዳይሬክቶሬቱን ተግባር ጠቁመዋል፡፡

ባለፉት 6 ወራትም ከመሬት ወረራ፣ ከካሳ ክፍያና ከመንግሥት ቤት ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች (በተለይም በቦሌ፣ ንፋስ ስልክና ለሚኩራ ክፍለ ከተሞች) በተሰራው የሕግ ማስከበር ስራ ከ100 በላይ ተከሳሾችን የያዙ ከ10 በላይ መዝገቦች ምርመራቸው ተጠናቆ ክስ መስርተናል ያሉት ዳይሬክተር ጀነራሉ ሌሎች ከ50 በላይ መዛግብት በምርመራ ሂደት ላይ እንደሚገኙ በመግለጫቸው ላይ አንስተዋል፡፡

ከ14ኛ ዙር የኮንደሚኒየም እጣ አወጣጥ ጋር ተያይዞ በተፈፀሙ የማጭበርበር ወንጀሎች ላይ እንዲሁም የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥን በተመለከተም ከመሬትና የመንግሥት ቤት አግልግሎት ጋር በተያያዘ እስከ 3.5 ሚሊየን ብር ድረስ ጉቦ ጠይቀው በተቀበሉ የመሬት አስተዳደር ሰራተኞችና ተባባሪዎቻቸው ላይ በከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን የተናገሩት አቶ ገብሩ፤ የአርሶ አደር እና የአርሶ አደር ልጅ እንደሆኑ በማስመሰል በ23 ካርታ መብት በመፍጠር 7754 ካ.ሜ የሆነ የመንግሥት መሬት በህገ-ወጥ መንገድ በሰጡና በወሰዱ የለሚ ኩራ ክ/ከተማ አመራሮች፣ ሠራተኞችና ተጠቃሚዎች በድምሩ 43 ተከሳሾች ላይ ምርመራ ተጠናቆ ክስ መመስረቱንም አክለው ተናግረዋል፡፡

የልማት ተነሺ ሳይሆኑ እንደሆኑ በማስመሰል በህገ-ወጥ መንገድ 11 የኮንደሚኒየም ቤቶችን ወስደዉ በሸጡ የቤቶች አስተዳደር አመራሮች፣ ሠራተኞችና ደላሎች በድምሩ 24 ተከሳሾች ላይ ፤በቂርቆስ ክ/ከተማ ወረዳ 02 በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት የይዞታ መጠኑ 1122 ካ.ሜ የሆነውን ስም ለማዞር አገልግሎት ከጠየቁት ግለሰብ ላይ 3.5 ሚሊዮን ብር በመጠየቅ 1.5 ሚሊዮን ብር በተቀበሉ የቂርቆስ ክ/ከተማ መሬት አስተዳደር የመሬት ዝግጅት ባለሙያ እና ግብረአበሮቹ ላይ ምርመራዎቹ ተጠናቀው በሁለቱም ጉዳዮች ላይ ክስ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ እንዲሁም ከቤተመንግሥት ግንባታ (በተለምዶ ጫካ ፕሮጀክት እየተባለ የሚጠራ) ልማት ጋር ተያይዞ የልማት ተነሺ በማስመሰል ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ በከፈሉና የካሳዉ ተጠቃሚ በሆኑ ተጠራጣሪዎች ላይ መዝገብ ተከፍቶ ምርመራ እየተደረገ ይገኛል ሲሉ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከፍትሕና ፀጥታ ዘርፍ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ሥልጣን ተገን በማድረግ የባለሀብቶችን እና ድርጅቶቻቸውን የባንክ ሂሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃዎችን በመውሰድ በማስፈራራት ከባለሀብቶቹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ብሮች ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ምርመራ አድርጎ ጉዳዩን ለፖሊስ የሚያስተላልፍ መሆኑን በመናገር ከባለሀብቶች በርካታ ሚሊዮን ብሮችን በመቀበል ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ የፋይናንስ ደኅንነት ሰራተኞች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ መመስረቱን እንዲሁም በተያያዙ ጉዳዮች ላይ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ዳይሬክተር ጀነራሉ አውስተዋል፡፡

ከፋይናንስ ዘርፍ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተም በህይወት የሌሉና ውጪ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በባንክ ያላቸውን ለረጅም ጊዜ ሳይንቀሳቀስ የቆየ ሂሳብ ደንበኞቹ እንዳሉና እንደቀረቡ በማስመሰል፣ሀሰተኛ ቼኮችን፣ ውክልናዎችን፣ መታወቂያዎችን፣ ሲፒኦዎችን በመጠቀምና የይለፍ ቃል ስርቆት በመፈፀም በተለያዩ ባንኮች ውስጥ የሚገኝ ከ80 ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብረው በወሰዱ የባንክ ሰራተኞች፣ ግለሰቦችና ተባባሪዎቻቸው ላይ ምርመራ ተጣርቶ አብዛኞቹ ላይ ከባድ የሙስና ወንጀል ክሶች መመስረቱን በመግለጫው ላይ ተመላክቷል፡፡

ከገቢ ዘርፍ ጋር ተያይዞ የተሰሩ ስራዎችን በተመለከተም ምንም አይነት የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ ሳይኖራቸው ከውጭ ሀገራት የውጭ ሀገር ገንዘብ ይዘው እንደመጡ በማስመሰል ገንዘቡን እያሳወቁ/ዲክላራሽን ሰነድ ላይ በመመዝገብ በሀገር ውስጥ በህገ- ወጥ መንገድ የተገኘን የውጭ ሀገር ገንዘብ ህጋዊ በማድረግ ከ5ሚሊዮን ዶላር በላይ መንግሥትን ጥቅም ባሳጡ 39 የጉሙሩክ ኮሚሽን ቦሌ ኤርፖርት ቅ/ፅ/ቤት ሰራተኞችና ግለሰቦች ላይ ላይ ምርመራ ተጠናቆ ተከሳሾችን የመያዝና የክስ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ እንዚህና በርካታ ተግባራት መከናዎናቸውን አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክቶ ኤልሻዳይ የልማት ተራድኦ ድርጅት እና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በፈፀሙት በሌሎች ተረጂዎች ስም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ የእርዳታ እህል፣ ቁሳቁስና ገንዘብ በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው ባዋሉ 13 ተከሳሾች ላይ ከባድ የሙስና ወንጀልና ህገ-ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ተመስርቷል ሲሉ ዳይሬክተር ጀነራሉ የገለጹ ሲሆን ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ በርካታ ወንጀሎች ላይ ክስ መመስረቱንና በምርመራ ሂደት ላይ ያሉ ጉዳዮችም መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ 6 ወራትም የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል በከባባድ የሙስና ጉዳዮች እና በሌሎች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እንደሚሰራ ተናግረው መግለጫቸውን ቋጭተዋል፡፡

Tagged Under: addis ababa • Anti-Corruption • attorney • Bank Fraud • bole • bribery • Criminal Charges • customs commission • embezzlement • federal • federal attorney general • Financial Crimes • Forgery • Fraud • general • grabbing • illegal enrichment • land • land grabbing • lemi kura • misuse of public funds • Prosecutor • Prosecutor General
የቅርብ ጊዜ ዜናዎች