የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሶስት ዓመቱን የፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን የ2018 የ6ወራት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ በፍትሕ ሚኒስቴር የመንግሥት ሕግና ፍትሕ አገልግሎት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ክቡር አቶ በላይሁን ይርጋ በተገኙበት ጥር 6/2018 ዓ.ም በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል፡፡
በዚህም ወቅት በክልሉ ከፍትሕ ዘርፍ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ጋር ተያይዞ ባለፉት 6 ወራት የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት የቀረበ ሲሆን፤ በመሠረተ ማኅበረሰብ የፍትሕ አገልግሎት፤ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር፤ በአስተዳደር ፍትሕ፤ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፤ በጥብቅና ፍቃድ አሰጣጥ፤ ከማረም እና ማነጽ አንጻር እንዲሁም ከፖሊስ እና ሌሎች ባለድርሻ አካለት ጋር ተቀናጅቶ በመሥራት የተሻለ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡
ክልሉ አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ተግዳሮቶች እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን፣ ተከታታይነት እና ቀጣይነት ያለዉ የሠዉ ኃይል አቅም ግንባታ ሥራዎችን ከማጠናከር እና የለሙ ቴክኖሎጂዎችን በማጋራት ረገድ የፍትሕ ሚኒስቴር ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
በመጨረሻም በቀጣይ በዕቅድ ትግበራ ወቅት የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት እና ከፖሊስ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በሚሠሩ ሥራዎች ላይ ይበልጥ በመናበብ ዉጤታማ የወንጀል መከላከል ሥራ መሥራት እንደሚገባ ክቡር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡