ቀን: ጥር 2016 ዓ.ም.
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ
Addis Ababa City Administration Revenues Bureau

የፌዴራል አስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 አፈፃፀም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ

ይህ የክትትል ሪፖርት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የገቢዎች ቢሮ የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አፈጻጸም የሚዳስስ ነው። በአዋጁ አንቀጽ 2(1) ላይ እንደተመለከተው የአስተዳደር ተቋም ማለት የፌዴራል መንግስቱ ተቋማትና የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተቋማትን የሚጨምር ስለመሆኑ በተገለጸው አግባብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ የአዋጁ አፈጻጸም ክትትል እንዲደረግበት ተመርጧል። ከዚህ አንጻር መመሪያ ለማውጣትና አስተዳደራዊ ውሳኔ ለመስጠት ለቢሮው ስልጣን ሰጪ የሆኑ ሕጎች ለመለየት የኢፌዴሪ ሕገ መንግስት፣ የከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1996፣ የከተማ አስተዳደር አስፈጻሚ አካላት ስልጣንና ተግባር ለመወሰን የወጣው አዋጅ ቁጥር 74/2014 እና በፌዴራል መንግስቱ የወጡ የታክስ ሕጎች ታድሰዋል። እንዲሁም ከክትትሉ ዓላማ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የቢሮው የስራ ሂደት ኃላፊዎች ቃለ-መጠይቅ በማድረግና በቢሮው የተለያዩ የስራ ሂደቶች የተሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔ ናሙናዎች ምልከታ የመረጃ ምንጭ አካል ናቸው።

ከመመሪያ ማውጣት ጋር በተያያዘ በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008፣ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008፣ የፌዴራል የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 እና የኤክሳይዝ አዋጅ ቁጥር 1186/2012 መመሪያ የማውጣት ስልጣን ለአዲስ አበባ እና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚሰጡ ቢሆንም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቻርተሩ የተሰጡት ግብርና ታክስ የመወሰንና የመሰብሰብ ስልጣን በ2003 ዓ/ም ለገቢዎች ሚኒስቴር (በቀድሞ ስያሜው ለገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን) ውክልና ሰጥቶ የነበረ በመሆኑ የገቢዎች ሚኒስቴር በሚያወጣው መመሪያ መሰረት ሲፈጸም የቆየ መሆኑ ይታወቃል። ይህ ውክልና በ2010 ዓ/ም የተነሳ ቢሆንም የከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ የታክስ ሕጎችን የሚያስፈጽም መመሪያ ያላወጣ በመሆኑ በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ አንጻር የቅድመ መመሪያ አወጣጥ አፈጻጸም ማየት አልተቻለም። ከአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁ የተቀመጡት መርሆዎች ማለትም አቤቱታን በጽሁፍ ስለመቀበል፣ ጉዳዩን ስለመስማት፣ በተገቢው ጊዜ መወሰን፣ የአስተዳደር ውሳኔን ለተገልጋዩ መስጠት፣ የቅሬታ አፈታት ስርዓት ስለመዘርጋት የሚሉት አንኳር ጉዳዮች በፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2008 የተካተቱና የቢሮውም አሰራር በዚሁ አግባብ የተቃኘ መሆኑን ተመልክተናል። ከታክስ ውጪ በአገልግሎት ላይ የሚቀርቡ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች አልፎ አልፎ በቃል የሚቀርቡ መሆኑና ምላሽም በቃል የሚሰጥ መሆኑ እና ጥቂት የማይባሉ የታክስ ኦዲት ውሳኔዎች ከተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በላይ የሚዘገዩ ስለመሆኑ ታይቷል።

የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጁና የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጁ ድንጋጌዎች በአብዛኛው ከውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎች ጋር የሚጣጣም በመሆኑና የቢሮውም አሰራር በዚሁ አግባብ የተቃኘ በመሆኑ ይህንኑ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባና አልፎ አልፎ ቢሆን በተወሰኑ ጉዳዮች አቤቱታና ምላሽ በቃል የሚሰጥበት አሰራር በጽሁፍ ስለሚሆንበትና ውሳኔዎች ሳይዘገዩ በተገቢው ጊዜ እንዲያልቁ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ተጠቁሟል።

ሪፖርቱን ያውርዱ

ተጨማሪ ሪፖርቶች