አስተዳደራዊ ተቋማት የመንግስት ተግባራትን ለመፈጸም ስልጣን የሚያገኙት ከሀገሪቱ ሕገ-መንግስትና እርሱን ተከትለው በተዋረድ ከሚወጡ ሕጎች ነው። የአስተዳደራዊ ሕጎች አንዱና ዋነኛው ዓላማ አስተዳደራዊ ፍትህን ማምጣት ነው። አስተዳደራዊ ፍትህ የሕግ የበላይነት የመኖር አንዱ መገለጫ በመሆናቸው አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን በሚወሰኑበት ጊዜ ወይም አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በሚወሰዱበት ጊዜ የመንግስት ተቋማት እና ባለስልጣናት የፍትህ አሰራር መርሆዎችን በማክበር ሊሆን ይገባል። ለዚህም ሲባል አገራት በሕግ ማዕቀፋቸው እንደ አንድ ዋና መርህ አድርገው የሚያስቀምጡት የመንግስት አሰራር ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚፈጥር ስርዓት መዘርጋት ነው።
በአንድ ሀገር ውስጥ የዲሞክራሲ ስርዓት ለማስፈንና የሕግ የበላይነት እንዲከበር ለማድረግ የመንግስት አሰራር ግልጽነት ሲኖረውና ለሰሩትም ስራ ባለስልጣናትና ውሳኔ ሰጪ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት የሕግ ስርዓት ሲኖር እንደሆነ ይታወቃል። ዜጎች የመንግስት አሰራር በግልጽ ሊከታተሉበት የሚችሉበት፤ በመንግስት አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ሊሳተፉበት የሚችሉበት መንገዶች እንዲሁም ዜጎች መብቶቻቸው ሲጠቀሙ የሚገጥሟቸውን የመብት ጥሰትን የመንግስት አካላትን ውሳኔዎቻቸውን የመቃወምና ከዚያም አልፈው በመደበኛው ወይም ለዚሁ ዓላማ በተቋቋሙ የፍርድ ሂደት የመብት ጥሰቶችን የሚታረሙበት የሕግ ስርዓት ሲፈጠር አስተዳደራዊ ፍትህ ማስፈን ያስችላል። ለዚህም ሲባል አስተዳደራዊ ፍትህ እንዲሰፍን አስተዳደራዊ ሕጎች የሚፈጸሙበት መንገድ ማስቀመጥ ያስፈጋል። ይህን መንገድ የሚያስቀምጥልን የሕግ ክፍል የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕግ ነው።
በኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 12 ስር የመንግስት አሰራርና ተጠያቂነት በተመለከተ የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን አለበት እንዲሁም ማንኛውም ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂ ይሆናል በሚል ተደንግጎ ይገኛል። የአስተዳደር ተቋማት በተለያዩ ሕጎች የተለያየ ስልጣንና ተግባራት የተሰጠ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን የመስጠትና መመሪያዎች ማውጣት ዋናዎቹ ተግባራት ናቸው። በሀገራችን ደረጃ የሚወጡ መመሪያዎችና የሚሰጡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ሕግና ስርዓት የተከተሉ ስለመሆናቸው የሚረጋገጥበት መንገድ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕግ ሲኖር መሆኑ እሙን ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕግ ያልነበረ በመሆኑ የመንግስት አሰራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከወኑን እና ኃላፊና የሕዝብ ተመራጭ ኃላፊነቱን ሲያጓድል ተጠያቂነት የሚረጋገጥበት መንገድ በተሟላ ሁኔታ ተዘርግቷል ማለት አይቻልም። ከጊዜያት በኋላ አስፈላጊነቱ ታምኖበት መጋቢት 29/2012 ዓ.ም የፌዴራል የአስተዳደር ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1183/2012 እንዲጸድቅ ተደርጎ ስራ ላይ ውሏል።
በዚህ አዋጅም የአስተዳደር ተቋማት በሰዎች መብቶችና ጥቅሞች ላይ የሚያስከትለውን ጣልቃ-ገብነት በሕግ የሚመራና ለሕግ የሚገዛ መሆኑን ለማረጋገጥና የአስተዳደር ተቋማት የውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት እንዲሁም በአስተዳደራዊ ውሳኔዎችና መመሪያዎች ቅር የሚሰኝ ሰው የውሳኔዎቹንና የመመሪያዎቹን ሕጋዊነት በፍ/ቤት የሚያስመረምርበት ሥነ-ሥርዓት በመደንገግ አስተዳደራዊ ፍትህ ማስፈን አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የወጣ እንደሆነ በአዋጁ መግቢያ ተቀምጧል።
ማንኛውም የአስተዳደር ተቋም በሕግ በተሰጠው የውክልና ስልጣን መሰረት መመሪያ ማውጣት የሚችልና መመሪያ ሲያወጣም በዚሁ አዋጁ አንቀጽ 4/2/ እንደተመለከተው በአዋጁ በተቀመጠው ሥነ-ሥርዓት መሰረት ብቻ ስለመሆኑ ተደንግጓል። በተጨማሪም ማንኛውም ሰው የአስተዳደር ተቋሙ መመሪያ ያላወጣ ቢሆንም የአስተዳደር ውሳኔ እንዲሰጠው የመጠየቅ መብት ያለው እንደሆነና ተቋሙም ሊያወጣ የሚገባውን መመሪያ አለማውጣቱ በሕግ ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት ላለመስጠት ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ተደንግጎ ይገኛል። በአዋጁ በቅድመ መመሪያ አወጣጥ ሥነ-ሥርዓት ስለሚከናወኑት ተግባራት በዝርዝር ተቀምጧል። የአስተዳደራዊ ውሳኔን በተመለከተም ስለአጀማመሩ፣ ስለአስተዳደር ውሳኔ አሰጣጥ መርሆዎች፣ ጉዳዮች ስለሚሰሙበት አግባብ፣ ውሳኔዎች ለተገልጋይ የሚሰጡበት አግባብ እና በውሳኔው ላይ ስለሚቀርብ ቅሬታ በተመለከተ በዝርዝር ተደንግጎ ይገኛል።
ተቋማችን በፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ህግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 የፌዴራል ጠቅላይ ዓ/ህግ ስልጣንና ተግባራት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 6 ስር የፌዴራል መንግስቱ ሕጎችን ተግባራዊ መደረጋቸውን እና አተገባበራቸውን ወጥነት ያለው መሆኑን ያረጋግጣል እንዲሁም አስፈጻሚ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ስራቸውን በሕግ መሰረት ማከናወናቸውን ያረጋግጣል በሚል ከዋና ዋና ኃላፊነቶች ውስጥ አንዱ ነው።
በዚህም መሰረት ተቋማችንም ይህን ኃላፊነት ለመወጣት በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ በዳይሬክቶሬት ደረጃ የፌዴራል ሕጎች ተፈጻሚነት መከታተያ ዳይሬክቶሬት በማደራጀት የፌዴራል ሕጎች የአፈጻጸም ክትትል ዳሰሳ ጥናት በማድረግ ሕጎችን በማስፈጸም ረገድ ያሉ ክፍተቶች እና ጥንካሬዎችን በመለየት፤ ሕጎች እየተፈጸሙ ካልሆነ ምክንያታቸውንም ጭምር በማጥናት ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ምክረ-ሀሳቦችን የመስጠትና መተግበራቸውንም የማረጋገጥ ስራ ይሰራል። በዚህ አግባብ ተቋማችን ባለፉት ዓመታት በርካታ ተቋማት ላይ የክትትል ስራ በማድረግና የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በመፍጠር ያከናወነና እያከናወነ ይገኛል።
ስለዚህም ተቋማችን በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት በእቅድ ከያዘው ተግባራት ውስጥ የፌዴራል አስተዳደር ስነ-ስርዓት ሕግ አፈጻጸም ላይ ክትትል ማድረግ ሲሆን በበጀት ዓመቱ በ1ኛው አጋማሽ ዓመት ለክትትል ከተመረጡት ተቋማት ውስጥ የማዕድን ሚኒስቴር አንዱ ነው። በመሆኑም የፌዴራል አስተዳደር ስነ ስርዓት አዋጅ አፈጻጸም ተቋሙ ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት በመነሳት የአስተዳደራዊ ውሳኔ አሰጣጥና የመመሪያ አወጣጥ ተግባራቱ ላይ ክትትል በማድረግ ይህ የክትትል ሪፖርት ተዘጋጅቷል።