በሀገራችን የተጀመረውን ትምህርትና ሥልጠና ጥራትና ተገቢነት ማረጋገጥ ለምናስበው ሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ በመሆኑ፣
የትምህርትና ሥልጠና ጥራትን ለማረጋገጥ የተማሪዎችና ሠልጣኞች የተግባር ሥልጠና (ኢንተርንሽፕ)፣ የመምህራንና አሠልጣኞች የኢንዱስትሪ ተሞክሮና ጉድኝት (ኤክስተርንሽፕ)፣ የኢንዱስትሪ ሙያተኞች በትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የሚያበረክቱት የተግባር ትምህርትና ሥልጠና አስፈላጊ በመሆኑ፣
ከፍተኛ ትምህርት፣ቴክኒክና ሙያ ተቋማት እና የምርምር ተቋማት ከኢንዱስትሪ ጋር በመተሳሰር ምርምር፣ ቴክኖሎጂ ሽግግርና የማማከር አገልግሎት ሥራዎችን ማከናወን ስለሚጠበቅባቸው እና ተወዳዳሪ ኢንዱስትሪ ለመገንባት ለኢንዱስትሪው ብቁ የሰው ኃይል፣ ችግር-ፈቺ ምርምር የማካሄድና ቴክኖሎጂ የማመንጨት ተልዕኮ ስላላቸው፣
የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ ምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪ ትስስር በጋራ ተጠቃሚነትና የትስስር አካላትን ንቁ ተሳታፊነት ስለሚጠይቅ እንዲሁም በሀገራችን ብሔራዊ የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ፖሊሲ ላይ የተመላከቱ የትስስር ቁልፍ ጉዳዮችን በሕግ መደንገግ በማስፈለጉ፣
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 55 (1) መሠረት የከፍተኛ ትምህርት፣ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና፣ የምርምር ተቋማት እና ኢንዱስትሪ ትስስር አዋጅ ወጥቷል፡፡
•