የኢትዮጵያ የጤናና ሥነ ምግብ ምርምር ኢንስቲትዩት የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት እና ዓላማውን ከግብ ማድረስ ይጠበቅበታል፡፡ ይህንንም ማድረግ እንዲችል የሰው ኃይል አቅሙን ማጎልበትና ዋና ተግባሩ አድርጎ ይወስዳል፡፡
ይህ ይሆን ዘንድ ሠራተኛውን በሰው ኃይል ልማት በሚቀየሱ ልዩ ልዩ የአቅም ግንባታ ትምህርትና ሥልጠናዎች በማሳተፍ ከመ/ቤቱ ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማ ጋር የተጣጣመ የሥራ ብቃት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች የትምህርት ደረጃቸውን ማሣደግና ከአዳዲስ የአሠራር ዘዴዎችና ቴክኖሎጂዎች ጋር አብረው እንዲራመዱና የተጠናከረ የመተግበር አቅም በመገንባት የሥራ ተነሳሽነት እንዲኖራቸው በማድረግ መ/ቤቱ የተጣለበትን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጣ ማድረግ ይቻላል፡፡
በመሆኑም የሰውኃብት ልማትን በተገቢው መንገድ ለማሳደግ ከሚረዱ ስልቶች መካከል ለሠራተኞች በልዩ ልዩ ደረጃ አቅም ለማሳደግ የሚረዱ የአጭር ጊዜ ሥልጠና፣ የውጪና የሀገር ውስጥ ከፍተኛ ትምህርት እንዲሁም የተልዕኮ ትምህርት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ትምህርትና
ሥልጠና በአግባቡ ከተመራ ተቋማዊ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ከዳር ለማድረስ አይነተኛ የመገልገያ ዘዴ ነው፡፡
በዚህም መሠረት የኢንስቲትዩቱን ዓላማ ሊያሳካ የሚችል የሰውኃይል ለማፍራት የሚያግዝ በዕቅድ ላይ የተመሠረተ ሥልጠና ለመስጠት ወጥ የሆነና በአሁኑ ወቅት ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የሚራመድ መመሪያ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህ የትምህርትና ሥልጠና መመሪያ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡
ስለሆነም ይህን የትምህርትና ሥልጠና መመሪያ ለማዘጋጀት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን የትምህርትና ሥልጠና መመሪያ ተሞክሮ ለመውሰድ ጥረት ተደርጓል፡፡ በዚህ መመሪያ ውስጥ በተባዕት ጾታ የተገለፁት ሁሉ ለሁለቱም ጾታዎች ያገለግላል፡፡