በዩኒቨርሲቲ ማህበረሰቡ ቅቡልነት እና የስራ ተነሳሽነት ለመጨመር ብሎም ተቋማዊ ብቃትን ለማሳደግ መልካም አስተዳደደርን ማስፈን የሚያስችል የአመራር እና የአስተዳደር አሰያየም ብቃትን መሰረት ያደረገና ውድድር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን አሳታፊ እና ግልፅ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፤
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለውን የከፍተኛ አመራር የኃላፊነት ቦታዎች ብዝሀነትና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ውድድርና ምደባ ማካሄድ አስፈላጊ በመሆኑ፤
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሪፎርም ስራዎች በመከናወን ላይ በመሆናቸው በሙያቸው የሰለጠኑ ብቃትና ችሎታ ያላቸው እንዲሁም እምነት የሚጣልባቸውን አመራሮች ወደ አመራርነት በማምጣት የትምህርት ጥራት እና ተገቢነትን ለማሻሻል ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ ትምህርት ሚኒስቴር በከፍተኛ ትምህርት በአዋጅ ቁጥር 1152/2011 አንቀጽ 52 ንዑስ አንቀጽ 5 በተሰጠው ስልጣን መሰረት ይህ መመሪያ አውጥቷል፡፡