መግቢያ
ቅጣት በማኅበረሰብ ላይ ወንጀል የፈፀመን ወንጀለኛ መበቀያ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የለም ሰው ሁል ጊዜ ወዶ ወንጀል ስለማይሰራ የቅጣት ዓላማ ጥፋት ያጠፋን ወንጀለኛ አርሞ አምራች ዜጋ በማድረግ ወደ ማህበረሰቡ መመለስ ነው እስከሚሉ ድረስ በቅጣት ዓላማ ላይ የተለያዩ ሀሳቦች ይሰማሉ፡፡ የተለያዩ ሀገሮች የተለያዩ የቅጣት ዓላማዎች በተናጥል ወይም በጣምራ በወንጀል ህጋቸው ውስጥ የሚያካትቱ ሲሆን በሀገራችንም የቅጣት ዓላማ በወንጀል ሕግ ውስጥ ተካቶ ይገኛል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ አጠቃላይ የወንጀል ቅጣት ዓላማን እና በኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ የተካተቱ የቅጣት ዓላማዎችን ከወንጀል ህጉ ጠቅላላ ክፍል ድንጋጌዎች ጋር በማገናዘብ እንመለከታለን፡፡
የቅጣት ዓላማዎች በጠቅላላ
ቅጣት ሊያሳካ ከተነሳለት ዓላማ በመመስረት የተለያዩ ሀገሮች የተለያዩ ዓላማዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ እነዚህ ዓላማዎች በወንጀል ቅጣቶች ውስጥ በተናጥል ወይም በጣምራ ተካተው የሚገኙበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ ቅጣት የሚከተሉት ዓላማዎች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡
ቅጣት እንደ በቀል ማስፈፀሚያ (Retribution)
የዚህ የቅጣት ዓላማ አራማጆች ወንጀለኛው ማህበረሰቡ ተው አታድርግ ያለውን ነገር ተላልፎ በማህበረሰቡ ህይወት፣ አካል፣ ጤና፣ ሞራል፣ ኢኮኖሚ፣ ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ፋይዳ ላይ ጥቃት ስለፈፀመ ለዚህ ተገቢ ያልሆነ ድርጊቱ የጁን ማግኘት አለበት የሚል መነሻ ያላቸው ሲሆን መሠረቱም የሀሙራቢ አይን ያጠፋ አይኑ ይጥፋ መርሆ ነው፡፡ የዚህ ቅጣት ዓላማ ተቃዋሚዎች ቅጣት እንደዚህ ከሆነ ለሁሉም ወንጀሎች ተመሳሳይ አቻ ቅጣት ልናገኝላቸው አንችልም ለምሳሌ በሀገር ክደት ወንጀል ጥፋተኛ የተባለ ወንጀለኛ አቻ ቅጣት ምንድ ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ እንዲሁም እንዲህ አይነቱ አካሄድ ዓለምን የአይነ ስውራንና የአካል ጉዳተኞች መነሃሪያ ያደርጋታል የሚል መከራከሪያ አላቸው፡፡ ይህ አይነቱ የበቀል አስተሳሰብ በዘመናዊው አለም የጎለበተውን ሰብዓዊ መብት የሚቃረን በመሆኑ በአሁኑ ዘመን በአንዳንድ ሀገሮች ካልሆነ በስተቀር እንምብዛም አይገኝም፡፡
ቅጣትን እንደ ወንጀል መከላከያ (Deterrence)
በሌላ በኩል ደግሞ የቅጣት ግብ ወደ ፊት ሌላ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል እንጂ ወንጀለኛውን መበቀል ሊሆን አይገባውም፡፡ የፈሰሰ ውሃ ስለማይታፈስ ወንጀለኛው ላደረገው ነገር የምንቀጣው ላደረገው ነገር እንደ ቅጣት ሳይሆን ወደ ፊት ቅጣት ፈርቶ ተመሳሳይ ወንጀል እንዳይፈፅሙ ለመከላከል ነው የሚል ነው፡፡ ይሁን እንጂ ወንጀለኛው ወንጀል እንዲፈፅም ያነሳሳው ምክንያት ከቅጣት ፍርሃቱ ሊበልጥ ስለሚችል እንዲሁም ሰዎች ወንጀል በሚፈፅሙበት ቅፅበት ቅጣት ትዝ ስለማይላቸው ቅጣት ሁል ጊዜ ይህን ግቡን ላይመታ ይችላል የሚል መከራከሪያ የሚያቀርቡ አሉ፡፡ በተጨማሪም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን ወንጀልና የወንጀለኞችን ደጋጋሚነት በማውሳት ቅጣት የማስተማር ግቡን እንዳልተወጣ ያሳያል የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡
ቅጣት እንደ ወንጀለኛውን ማግለያና መለያ (Incapacitation)
በዚህኛው ዓላማ ደግሞ ቅጣት ወንጀለኛውን ለተወሰነ ጊዜ ወይም ለዘላለሙ (በሞት ቅጣት) ወንጀል ከሚፈፀምበት ማኅበረሰብ በማግለል ወይም በመለየት በማህበረሰቡ ላይ ድጋሜ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ይቻላል የሚሉ ወገኖች ያሉ ሲሆን ወንጀለኛው እስር ቤት በሚሆንበት ጊዜ ማህበረሰቡ ከወንጀል ይገላገላል፤ እንደ ሞት ያሉ ቅጣቶች በሚጣልባቸው ወንጀሎች ደግሞ ወንጀለኛው በድጋሜ ወንጀል የመፈፀም እድል ስለሌለው ማህበረሰቡ ከወንጀለኛው ድጋሚ ጥፋት መታደግ ይቻላል የሚል ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ ቅጣት ሁሉ በዚህ የቅጣት ዓላማ ላይም ትችቶች ያሉ ሲሆን ከሞት ቅጣት ውጭ ባሉ ቅጣቶች ላይ ወንጀለኛው እስር ቤትም ሆኖ እንደ ስርቆት፣ ግብረሰዶም፣ ግድያና የአካል ጉዳትን የመሳሰሉ ወንጀሎችን መፈፀሙ አይቀርም ወይም ከእስር ሲፈታ ጠብቆ መልሶ ወንጀል ሊሰራ ይችላል፣ እንዲያውም በእስር ቤት ቆይታው ወንጀል ተምሮ እንዴት በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ እንደሚፈፅመው፣ እንዴት የመያዝ እንድሉን እንደሚቀንስ ተምሮ ሊወጣ ስለሚችል ይህ የቅጣት ዓላማ ብዙ ርቀት አያስጉዝም፣ እንዲሁም የቅጣቱ ግብ እስረኛውን በማህበረሰቡ ላይ ይበልጥ በቀለኛ ስለሚያደርገው በወንጀል ተግባሩ የመግፋት ዝንባሌ ሊኖረው ይችላል የሚል ክርክር ያቀርባሉ፡፡
ቅጣት ወንጀለኛውን እንደ ማረሚያ (Rehabilitation)
የዚህ ቅጣት ግብ መሠረት አጥፊውን ከመረዳት የሚጀምር ሲሆን ወንጀለኛው ወንጀል ውስጥ የገባው ውስጣዊና ውጫዊ ምክንያቶች ወንጀል እንዲፈፅም ገፍተውት ስለሆነ እነዚህ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች በማከም ወንጀለኛውን ከድጋሜ ጥፋት ማረም ይቻላል የሚል ነው፡፡ ወንጀለኞች ተወልደውም ይሁን ተሰርተው ወንጀለኛ እንዲሆኑ ያደረገ ሳይኮሎጂካል፣ ባዮሎጂካል፤ ኢኮኖሚካል ወይም አካባቢያዊ አሊያም ማኅበራዊ ምክንያት ስለሚኖር ወንጀለኛው ወንጀል ለመፈፀም ያነሳሳውን ምክንያት በመመርመር ምክንያቱ አክሞ በማዳን ወንጀለኛውን ጤነኛ አምራች ወንጀልን የሚጠየፍ ለማህበረሰቡ ርህራሄ የሚያሳይ አድርጎ መመለስ ስለሚቻል የቅጣት ግብ ይህ መሆን አለበት የሚል መደምደሚያ ያለው ነው፡፡
የቅጣት ዓላማና ግቦች በኢ.ፊ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ
የወንጀል ህጉ ዓላማና ግቦች በህጉ አንቀጽ 1 እንደዚሁም በመግቢያው ላይ በዝርዝር ተገልፀው ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሠረት የወንጀል ሕጉ ዓላማ ስለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግሥት፣ የህዝቦቹን፣ የነዋሪዎችን፣ ሰላም፣ ደኅንነት፣ ስርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ሲሆን የሕጉ ግብ ደግሞ ወንጀል እንዳይፈፀም ለመከላከል የሚያስችል ስለወንጀሎችና ስለሚያስከትሉት ቅጣት በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ይህ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀለኞቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡ፣ ለሌሎችም ማስተማሪያ እንዲሆኑ፣ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፅሙ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሆነ በወንጀል ህጉ አንቀጽ አንድ ተገልፀዋል፡፡ በዚህ መሠረት የወንጀል ህጉ ከላይ ከተዘረዘሩት የቅጣት ዓላማና ግቦች ውስጥ በተለይ ችሎታ ማሳጣትን፣ ማስጠንቀቂያ መስጠት እና እርማትን ወይም መልሶ ማቋቋምን አዋህዶና አካቶ ይዟል ለማለት ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የወንጀል ሕጉ የቅጣት ዓላማና ግቦች በሕጉ በጠቅላላም ሆነ ልዩ ልዩ ክፍሎች ውስጥ ስለቅጣት አወሳሰን በሚደነግጉት አንቀፆች ስር ተንፀባርቆ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም በተለያዩ የወንጀል ዓይነቶች ላይ ተፈፃሚ እንዲሆኑ የተደነገጉት የቅጣት አይነቶችና መጠን ተቀባይነት ያላቸውን የቅጣት ዓላማና ግብ ለማሳካት የተደነገጉ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በወንጀል ህጉ ጠቅላላ ክፍል በአንቀጽ 117 የተደነገገው የሞት ፍርድ፣ በአንቀጽ 123 ስር የተደነገገው ከቤተሰባዊ፣ ሙያዊና ተመሳሳይ ከሆኑ መብቶች የመሻር ቅጣት፣ በአንቀጽ 127 ስር የተገለፀው ከወታደራዊ መዓረግና የሥራ ገበታ መቀነስ ወይም ማስለቀቅ እንዲሁም ከአንቀጽ 142-150 የተገለፁት የተለያዩ ፍቃድ የመንጠቅ ቅጣቶች የወንጀል ሕጉ የቅጣት ዓላማ ወንጀል የመፈፀም ችሎታን ማሳጣት እንደሆነ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ እንዲሁም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 98 ስር እንደተደነገገው የፅኑ እስራት ግብ ተቀጪው እንዲታረምና ወደ ማኅበራዊ ኑሮው እንዲመለስ ከማድረግ በተጨማሪ በተለይ ለህብረተሰቡ ደኅንነት ጥብቅ ቁጥጥር ሥር እንዲቆይ ማድረግ ነው፡፡
በሌላ በኩል ከአንቀጽ 157-167 በተገለፀው መሠረት በወጣት ጥፋተኞች ላይ የሚወሰዱ የጥንቃቄና አያያዝ እርምጃዎች፣ ከአንቀጽ 129-133 በተገለፀው መሠረት ከፊል የወንጀል ኃላፊነት ባለባቸው ጥፋተኞች ላይ የሚወሰዱ የጥንቃቄና የአያያዝ ሁኔታዎች፣ በአንቀጽ 190 እና ተከታታይ ድንጋጌዎች መሠረት ወንጀለኞችን ቅጣትን በገደብ ማቆየት፣ እንዲሁም በአንቀጽ 134 እና ተከታታይ ድንጋጌዎች መሠረት የሚወሰዱ አጠቃላይ የወንጀለኞች አያያዝና የጥንቃቄ እርምጃዎች በእርማት ወይም ወንጀለኛን መልሶ በማቋቋም ዓላማ ላይ የተመሰረቱ ናቸው፡፡ በተለይ ከባድና አሰቃቂ ወንጀል በሚፈፅሙ ወንጀለኞች ላይ ከፍተኛው ቅጣት እንዲወሰንባቸው መሠረታዊ የሆኑ የቅጣት ማክበጃ ድንጋጌዎች እንደዚሁም በልዩ ልዩ የህጉ ድንጋጌዎች መገለፁ የቅጣቱ ዓላማና ግብ ማስጠንቀቂያ ጭምር ሊሆን እንደሚገባው ያስገነዝባል፡፡
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ የወንጀል ህጉ ዓላማ የህብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ እንዲሁም በህብረተሰቡ ላይ ወንጀል እንዳይፈፀም መከላከል ሲሆን ይህን ግብ ለመምታትም አንዱና ዋናው መንገድ ቅጣት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡
በንቃተ ሕግ ትምህርትና ሥልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ